Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኤርታሌ እሳተ ገሞራ በየአቅጣጫው እየፈሰሰ ነው

0 1,616

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍንዳታው ያስከተለው ክስተት ለጨው አምራቾች ስጋት፣ ለቱሪስቶች መስህብ ሆኗል
ከቀድሞው የበለጠ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ ተፈጥሯል

በኣፋር ክልል የሚገኘው የኤርታሌ የቀለጠ አለት ሃይቅ ባልተለመደ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ በመንተክተክና ሃይለኛ ፍንዳታ አስከትሎ፣ ከቀድሞው የበለጠ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ በመፍጠር በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት መፍሰስ መጀመሩን “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ድረገጽ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ኤርታሌ ከዚህ በፊትም እየተንተከተከ መጠኑን በመጨመር፣ ለሁለትና ለሶስት ቀናት ከፍና ዝቅ ይል እንደበር፤ አልፎ አልፎም ከጉድጓዱ ወጥቶ በመፍሰስ፣ ተመልሶ ወደነባሩ ሁኔታው ይመለስ እንደነበር  ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሰሞኑ ግን ያልተለመደ ከፍተኛ ፍንዳታና ፍሰት መፍጠሩን ገልጧል፡፡
“በኦሪጅንስ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል” የቱር የኦፕሬሽን ማናጀር የሆኑት የስነ-ምድር ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ በተለይ ለአዲስ አድማስ ትናንት እንደገለጹት፣ ከጥቅምት መጨረሻ አንስቶ ለተራዘመ ጊዜ ከነባሩ ጉድጓድ እስከ አስር ሜትር ከፍታ በመውጣትና በመውረድ፣ አልፎ አልፎም ከጉድጓዱ አልፎ ሲፈስ የቆየው ኤርታሌ፣ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ግን ባልተለመደ ሁኔታ ተፈጥሮውን ቀይሮ፣ ከፍተኛ ፍንዳታ በመፍጠር ብዛት ያለው የቀለጠ አለት በሁሉም አቅጣጫ መፍሰስ ጀምሯል፡፡
ይህ አዲስ ክስተት ከቀለጠ አለቱ የፍሰት ፍጥነት፣ መጠንና ከአለቱ የመረጨት ወሰን አንጻር እጅግ ያልተመለደና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት አቶ እንቁ፣ ኤርታሌ እስከ 20 ሜትር ከፍታ እየዘለለ በመረጨት፣ በሰከንድ 50 ሜትር ኪዩብ የቀለጠ አለት እያወጣ በሁሉም አቅጣጫ በሰዓት 55 ኪሎ ሜትር ፍጥነት መፍሰሱንና 3 ሜትር ውፍረት ያለው ይህ የአለት እሳት ወንዝ በአራት ቀናት ቆይታው ጉድጓዱ እስከ 700 ሜትር ርቆ መጓዙን ተናግረዋል፡፡
ክስተቱ ለአራት ቀናት ያህል በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ፣ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ደቡብ አቅጣጫ “አቶሚክ ኤክስፕሎሲቭ” የተባለ ሃይለኛ ፍንዳታ መፍጠሩን የጠቆሙት አቶ እንቁ፣ ይሄን ተከትሎም በኤርታሌ የነበሩት ሁለት የቀለጠ አለት ሃይቆች በመካከላቸው ሰፊ ስንጥቅ በማስከተል ሌላ አዲስ የቀለጠ አለት ሃይቅ ጉድጓድ መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
አዲስ የተፈጠረው ጉድጓድ ከነባሮቹ በስፋቱ የበለየና ብዛት ያለው የቀለጠ አለት የያዘ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፤ ከአዲሱ ጉድጓድ እየገነፈለ በየአቅጣጫው ለቀናት ሲፈስ የቆየው የቀለጠ አለት ከትናንት በስቲያ መብረድ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች መሰል ተፈጥሯዊ ክስተቶች ከሚታዩባቸው አካባቢዎች ሰዎች በ150 ኪ.ሜትር ያህል መራቅ እንዳለባቸው ይመከራል ያሉት ባለሙያው፣ የአፍዴራ የጨው ማምረቻ ከኤርታሌ በ50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው፣ ተመሳሳይ ሁለት እና ሶስት ክስተቶች ቢከሰቱ በጨው አምራቾች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ከኤርታሌ በሌላ አቅጣጫ እስከ 50 ኪ.ሜትሮች ርቀው በሚገኙ ትንንሽ የአፋር መንደሮች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም፣ የአደጋ ስጋት ክልል ውስጥ በመሆናቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ይህ ክስተት ለጨው አምራቾችና ለአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ስጋት ቢሆንም፣ ለቱሪዝሙ ግን አዲስ ተጨማሪ መስህብ መፍጠሩ ተነግሯል፡፡  በርካታ አለማቀፍ የቱሪዝምና የተፈጥሮ ክስተቶችና አደጋዎች ላይ የሚሰሩ ድረ-ገጾችና ተቋማት ያልተመለደውን የሰሞኑ የኤርታሌ ክስተት በስፋት መዘገባቸውን ተከትሎ፣ ወደ አካባቢው የሚያቀኑና ለመጎብኘት ያቀዱ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ የሆነውና በአብዛኛው ከመስከረም እስከ መጋቢት ባሉት ወራት በቱሪስቶች የሚጎበኘው  ኤርታሌ፣ በእነዚህ ወራት በቀን በአማካይ እስከ 40 በሚደርሱ ቱሪስቶች እንደሚጎበኝ ይገመታል፡፡

admassnews

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy