Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ጽንፍ ረግጣችሁ ጽንፍ አታውጡን!

0 917

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወንድይራድ ሃብተየስ 01-02-17

የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ጽንፍ ረግጣችሁ ጽንፍ አታውጡን! ወንድይራድ ሃብተየስ 01-02-17 ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የዓለም ህብረተሰብ ኢትዮጵያ የሚመለከታት በተደጋገጋሚ በድርቅ የምትጠቃና በጦርንት የደቀቀች አገር አድርጎ ነበር። በእርግጥም ስር የሰደደ ድህነት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የአገሪቱ መገለጫ ተደርገው ቢወሰዱ ሃሰት ናቸው ብሎ መሞገት አይቻልም። በእኩልነት እጦት ሳቢያ ለረጅም ዓመታት የተካሄደውን የእርስ በርስ ግጭት የአገሪቱን ገጽታ ክፉኛ ጎድቶታል። ይሁንና ይህን አስከፊ ገጽታ ለመቀየር የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባደረጉት መራራ ትግል ከፍለዋል። የደርግ ስርዓት ከወደቀ ብኋላ ወደስልጣን የመጣው የሽግግር መንግስት የአገሪቱን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችል በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ከዚህ ውስጥ አንዱ እና መሠረታዊው ጉዳይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ህገ-መንግስት ማርቀቅና ህብረተሰቡን ማወያየት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ረቂቅ ህገ-መንግስት ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በወቅቱ የነበሩ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አያሌ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራትን በእያንዳንዱ አንቀጽ ላይ መክረውበታል። በተወካዮቻቸውም አማካኝነት እንዲጸድቅ አድርገዋል። ይህ ህገመንግስት የአገሪቱን የቆዩና የአብዛኛውን የህብረተሰብ የገነገኑ ችግሮች መቅረፍ አስችሏል። በእርግጥ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል መብት ማስጠበቅ እንጂ የሁሉንም አካል መብት እኩል ማስጠበቅ አይቻልም። በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ህገመንግስት በመልካም የማይመለከቱ ጥቂት አካሎች መኖራቸው አልቀረም። እነዚህ በቀድሞው ስርዓቶች የተሻለ መብትና ጥቅም አግኝተው የነበሩ አካሎች የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ መልካም ነገር ሲያወሩ አይደመጡም። በእርግጥ ማንም ጥቅሙ አሊያም ቁስሉ ሲነኩበት አርፎ የሚቀመጥ አካል አይኖርም። እንኳንስ ሰብዓዊው ፍጡር ይቅርና እንሰሳትም አርፈው አይተኙም። በየትኛውም አሰራር ቢሆን የብዙሃን ድምጽ የበላይነት እንዲኖረው ማደረግ ትክክልኛና ተገቢ አሰራር ሊሆን የግድ ነው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም የብዙሃኑን መብትና ጥቅም የማስጠበቅ አሰራርን ይተገብራል። በመሆኑም የኢፌዴሪ ህገመንግስትም የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ማስጠበቅ ችሏል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መሰረታዊ ችግሮች መቅረፍ በማስቻሉ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማግገኘት ችላለች። የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሮች ተብለው ይጠቀሱ ከነበሩት ችግሮች መካካል ግንባር ቀደሞቹ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት መነፈጋቸው፣ ባህላቸውና ማንነታቸው መደፍጠጡ በተለይ ቋንቋቸውን መጠቀም ባለመቻላቸው ሳቢያ አንዳንድ ቋንቋዎች ሲሞቱ አንዳንዶች ደግሞ እጅግ ተዳክመው ነበር። ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ፍትሃዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማግኘት ባለመቻላቸው የህብረተሰቡ ኑሮ እጅግ የከፋ ነበር። የኢፌዴሪን ህገመንግስት ከጸደቀ ከ1987 ዓ.ም በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት 22 የህገመንግስት አመታት በርካታ ለውጦችን ማግኘት ችለዋል። ዛሬ በተጨባጭ አገራችን ውስጥ ያለው እውነታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዳያፍሩ ሆነዋል፣ ይወክሉናል በሚሉት አካል እየተዳደሩ ናቸው፣ በቋንቋቸው መማርና መዳኘት ችለዋል፣ በማንነታቸው መሸማቀቅ ቀርቷል፣ በፌዴራል መንግስቱ ተገቢውን ውክልና አገኝተው ከሌሎች እኩል በጋራ ጉዳያቸው ላይ ይመክራሉ እንዲሁም አካባቢያቸውን በሚፈልጉት መልኩ ማልማትና መለወጥም ችለዋል። ይሁንና የኢፌዴሪን ህገመንግስት የአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ለውጥና ጥቅም መረጋገጥ ቢያስችልም በቀድሞ ስርዓቶች ተጠቃሚ የነበሩ የጥቂቶችን የተለመደ የበላይነት በማስቀረቱ እነዚህ አካሎች አልተደሰቱም። በዚህም ሳቢያ እነዚህ አካላት በኢፌዴሪ ህገመንግስት ላይ በተለያየ መልክ የማያቋርጥ ዘመቻቸውን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። ህገመንግስቱ አገራችን ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት ከነበረችበት የቁልቁለት ጉዞ እንዲያበቃ አድርጓል። በመሆኑም አሁን ላይ በሁሉም መስክ ሊባል በሚችል መልኩ ለውጦች መመዝገብ ጀምረዋል። እኩልነት ተረጋግጧል። የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጠብቀዋል። ይሀንና የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የተለያዩ መርዞችን አሁንም በመርጨት ላይ ናቸው። እንደእኔ እንደኔ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መወያያ አጀንዳ መሆን ያለበት የዴሞክራሲ ስርዓታችንን እንዴት እናጎልብተወ? ዘላቂ ሰላም እንዴት እናረጋግጥ? መልካም አስተዳደር እንዲት ይጎልብት? ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ፍተሃዊ ተጠቃሚነትን እንዴት እናረጋግጥ? ወዘተ አገራዊ ጉዳዮችን ማንሳት በተገባ ነበር። ዛሬ ላይ ተመልሰን ስለእክልነትና ነጻነት የምናወራበት ጊዜ አልነበረም። ምክንያቱም የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎች ህገመንግስትችን ሲጸድቅ በ1987 ምላሽ አገኝተዋል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማንኛውም ብሄር የበላይነት እንዳይኖር ተደርጎ ተደፍቋል። የበላይም ይሁን የበታች ብሄር ወይም ብሄረሰብ እንዳይኖር የፌዴራል ስርዓቱ የመጨረሻ እልባት ሰጥቶታል። የፌዴራል ስርዓታችን ትልቁና ዋንኛው የህገመንግስታችን ቱሩፋት ነው። መልካም አስተዳደር ሂደት ነው። በቀጣይም በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ለውጦች ሳቢያ የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። ሲጀምር መረዳት ያለብን ጉዳይ የዴሞክራሲ ስርዓታችን ገና መጎልበት የሚፈልግ ጅምር መሆኑን ነው። አንዳንድ አካላት በግለሰብ የሚፈጸሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደአጠቃላይ የዴሞክራሲ ስርዓቱ መገለጫ አድርገው ማቅረባቸው አግባብነት የጎደለው ፍረጃ ይመስለኛል። የአሜሪካ ነጭ ፖሊሶች በጥቁሮች ላይ የሚፈጽመት የገነገነ በደል የአሜሪካ መንግስት የዴሞክራሲ መገለጫ ወይም ማሳያ ሆኖ ሲቀርብ አልተመለከትንም። በእኛ አገር ግን አንድ የቀበሌ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ የሚፈጽመው በደል በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በተለይ በዳያስፖራ ፖለቲከኞች እንደስርዓቱ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድበት አሰራር ተገቢ አይመስለኝም። ለዴሞክራሲ ስርዓቱም መጎልበት ለአገራችንም ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚበጅ አይደለም። እውነታንና ስሜትን ለየቅሉ እንመልከት። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓቱ ጅምርና ያልጎለበተ ይሁን እንጂ ለአገራችን በርካታ ለውጦችን ማስገኘት ችሏል። ይህን የአገራችንን መለወጥ ያመላከተንን ስርዓት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መወረፉ የሚያመጣውን መዘዝ ካለማሰብ ይመስለኛል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንሰሳ ማሰብ ተገቢ አይመስለኝም። የአገራችን ህገመንግስት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን አረጋግጦልናል። ይሁንና አገርን የሚያፈርስ ህዝብን ከህዝብ ያሚያጋጭ ቅጥ ያጣ አካሄዶችን መከተል ግን ከተጠያቂነት አያስመልጥም። በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በቅርቡ የተፈጸሙ ድርጊቶች ሁላችንም አፍረናል። ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦችን ማጋጨት እጅግ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። መንግስታት ይሄዳሉ ይመጣሉ፤ አገርና ህዝብ ግን ሁሌም ይኖራሉ። እነዚህን ለማፍረስ መስራት ግን ተገቢ አይደለም። ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ላያሸንፍ ይችል ይሆናል። ይሁንና ኢህአዴግን በመጥላት ብቻ አገርን ለበመተን መነሳት ሃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች እየፈጸማችሁ ያለው ይህን ተግባር ነው። ሁለት ቤት ያላት አይጥ ጥቃት አይደርስባትም እንደሚባለው እናንተ በተሻለ አገር እየኖራችሁ የኛን የደሃ ጎጆ እባካችሁ አትበትኑብን። ይህን ስል በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ችግር የለም ማለት አይደለም። ችግሮችን በመነጋገር መፍታት የሚቻልበት ስርዓት ግን ተዘርግቷል። ማንም አገሩን ወዳለሁ የሚል ዜጋ ወደ አገሩ የመለስና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መንግስትን በሃሳብ ይሞግት፣ ይታገል። ህዝብ ዳኛ ይሁን። ቀልቡን ለገዛው ድምጹን ይስጥ። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ከዚህ ባሻገር ግን በኢሳት፣ ኦኤምኤንና ፌስቡክ በምታሰራጯቸው መርዘኛ መልዕክቶች ወጣቱን ለጥፋት አትዳርጉት። ያለፈው ይብቃ። እናንተ ከዚያ እኛ ከዚህ ስንጓተት በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓትና ልማት አይጓተት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy