Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጉባ አበባዎች

0 4,016

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጉባ አበባዎች

አሜን ተፈሪ 01-06-17 ወደ ጉባ በሄድኩ ጊዜ፤ ‹‹ሳድል ዳም›› የሌለው የስሜት ግድብ ገጥሞኛል፡፡ በስሜት ኃይል የተሞላው ግድብ ለወትሮው በደንብ የሚያገለግለኝን ‹‹ዲያፍራም ወል›› ሰርስሮ የስሜት ሱናሚ ፈጥብኛል፡፡ አባይ እየተገደበ እያየሁ፤ የእኔን የስሜት ግድብ ‹‹በጌት›› –‹‹አን-ጌትድ ስፒል ኦቨር›› መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 500 ሜትር ወርዶ የተሰራው የስሜት ግድብ፤ ‹‹በሮለር ኮምፓክትድ ኮክሪት›› ሙሌት መገንባቱ አላዋጣኝም፡፡ ፈሰሰ፡፡ አሁን ከስሜት ሌላ ንጉስ የማይሻ የስሜት ህዝብ በውስጤ ነግሷል፡፡ ‹‹ስሜት ውስጤ ነው፡፡›› የጃፓንን ሱናሚ አይታችኋል፡፡ ውሃ እጅግ ኃይለኛ ነው፡፡ እንደ ውሃ ኃያል ነገር አመኖሩን የምታውቁት ያን የሱናሚ ትዕይንት ስትመለከቱ ብቻ ነው፡፡ አዎ፤ በእነዚህ ዐ. ነገሮች የምናገረውን ነገር ከነሙሉ ኃይሉ ለመረዳት የፈለገ ሰው ሱናሚ ብሎ ኢንተርኔቱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ጉድ ነው፡፡ አሁን በድረ ገጽ እንደምትመለከቱት የሱናሚ ትዕይንት ከባድ ስሜት በውስጤ ተነስቷል፡፡ ስለዚህ ሐሳቦች እንዲሸሹ መለከት ከመንፋት በቀር ሌላ ምርጫ የለኝም፡፡ በስሜት ሱናሚ ተጥለቅልቋል፡፡ በስሜት ኃይል ተውጧል፡፡ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ባለ ኢዩር ገጣሚ የምናብ ኃይል በቀር ሊመጠን የማይችልን የስሜት ማዕበል ነው፡፡ አሁን የተቀመጥኩበት የስሜት ፈረስ፤ እንደ ሰልዳው ጊዮርጊስ ያለ ሰማዕት እንጂ እንደኔ ያለ መዋቲ ፍጡር ሊቀመጥበት የማይችልበት ፈረስ ነው፡፡ በእኔ በምስኪኑ ክንድ ወደ ኋላ ሊሳብ የማይችል ኃያል ነው፡፡ እንደ ምስኪኗ ብሩክታዊት ለስሜት ደራጎን መስዋዕት ከመሆን የሚታደገኝ አልፈልግም፡፡ ስሜቱን ወድጄዋለሁ፡፡ ከጉባ ኮረብታ ሆኜ የዋናው ግድብ ግንባታ ወለል ብሎ ይታየኛል፡፡ ከዚያም ወደ ኮርቻ ግድቡ አሻግሬ ማየት እችላለሁ፡፡ የሳክስፎን ተጫዋቹ የጌታቸው መኩሪያ ሽለላ፤ (እባካችሁ ለመስማት ሞክሩ) በህሊዬ ጀርባ ባለው የስሜት መድረክ ተለቋል፡፡ ስሜቴ ጎንበስ ቀና እያለ ይሸልላል፤ ያቅራራል፡፡ የጉባ ተአምር፤ በጌታቸው መኩሪያ ሳክስፎን ታጅቦ፤ ለዓመታት የተሰራሁትን የስሜት ግድብ አፈረሰው፡፡ በኢትዮጵያዊ ሰው የደም ስር የሚዘዋወረው ደም አይደለም፡፡ ነጻነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ትከሻ ያረፈው ከሐር ከጥጥ ከድር-ከማግ የተሰራ ደርከኖ አይደለም፡፡ የአትኩኝ ባይነት የጀግንነት ጃኖ ነው፡፡ ልቡ የሚረጨው የጠንካራ እምነት ኃይል ነው፡፡ ሞትን ከፊቱ አቁሞ በእምነትቱ ጸንቶ ለመኖር የሚችል ነው፡፡ እንደ ጣሊያን እንደ ፋሽስት ጀነራል፤ እንደ ግራዚያኒ ያሉ ጨካኞችን፤ የጭካኔ ጉልበት የሚያብረከርክ ወኔ ነው፡፡ እንኳን ለህዝቧ ለመሬቷም እንዳትገዛችሁ ገዝቻለሁ የሚሉ የነጻነት መንፈሳዊ አርበኞች ሀገር ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ይኸው ነው፡፡ እጅህን ስጥ ሲሉት ሞትን እንደ መናኛ ትንኝ ቆጥሮ ምን እጅ አለው የእሣት ሰደድ ብሎ ለወገኑ ክብርን አውርሶ የሚሞት ጀግና የበቀለበት ምድር ነው፡፡ ድህነትን ተገን አድርጎ ፈቃዱን እንድንፈጽም የሚያስገድደን ሲመጣ ‹‹ተውት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን መራብን እናውቅበታለን›› ብሎ በነጻነቱ የሚጸና ህዝብ ምድር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ ምድር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚልሰው የሚቀምሰው አጥቶ፤ በረሃብ በጠኔ እጅ ከፍንጅ እንዲታሰር ከሞት ደጃፍ ሳለ፤ ዘማች አሞራ በዚያ እያንዣበበ ‹‹የለም የፍስክ አልበላም›› ብሎ እምነቱን በነፍሱ ቋጥሮ፤ እምነቱን በህይወት ክፍያ እንደ ቀሺ ገብሩ ህይወቱን ለመለወጥ የሚፈቅድ ትውልዶች የተመላለሱበት ምድር ነው፡፡ እንዲህ ያለ ህዝብ የጌታቸው መኩሪያን ሽለላ ሲሰማ፤ በዘር ማንዘሩ ውስጥ በታሪክ የደም ስር የሚዘዋወር ለነጻነት የመቅናት ስሜት ያጥለቀልቀዋል፡፡ በኦሮሞ ጌረርሳ እና በባሮ ዜማዎች የሚመላለሰው የስሜት ማዕበል ያንገላታዋል፡፡ በትግሬ እምቢልታ፣ በወላይታ ጭፈራ፣ በጋምቤ ቶም ወዘተ ወዘተ ……… ያለው ደም የሚያሞቅ ኃይል ይንጠዋል፡፡ አሁን ከተቀመጥኩበት ሥፍራ ሆኜ፤ የሚሰማኝ የድንጋይ መፍጫ ግሬደር፣ የድንጋይ መጫኛ አስትራ እና የድማሚት ወዘተ ድምጽ ነው፡፡ እነዚህ ድምጾች በልዩ የስሜት ማቀነባበሪያ (ሚክሰር) ተቀነባብረው ከእዝነ-ህሊናዬ ሲደርሱ፤ ከጌታቸው መኩሪያ ሳክስፎን አንደበት የሚወጡ የሽለላ እና ቀረርቶ ዜማዎች ይሆናሉ፡፡ ማህሌት የቆመ ባለቅኔ ካህን በቅኔው ምስጢር ከስሜት ግድቡ ቁመት ባለፈ የስሜት ኃይል እንደሚናጥ፤ እኔም በጉባ ግድብ የስራ ወረዳ ሆኜ ኮረብታውን ቁልቁል እያየሁ፤ ከየሸለቆው የሚነሳውን ድምጽ እሰማለሁ፡፡ ከዚያ ሸለቆ የሚወጣው ድምጽ ከሽለላ ዜማ የተለየ ሆኖ አልታየኝም፡፡ ‹‹እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን›› የሚል ኃይለ ቃለ ያለበት ቲ-ሸርት የለበሱ ሾፌሮች ምድር ግቢውን የአቧራ ጅራት እያስነሱ ጎዳናውን ሲሰነጥቁት ይታየኛል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሁሉም ክልሎች የመጡ ኢትዮጵያውያን (ሆነ ተብሎ) ሠራተኞች የሚሰሩበት ፕሮጀክት ነው፡፡ በሁሉም የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ጉባ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመውጣት በየመስኩ የሚያደርጉት ትግል፤ በአንድ ሥፍራ በሚካሄድ አንድ ፕሮጀክት ተምሣሌት፤ ለዓይን የሚታይ ሆኖ ከፊቴ ተደቀነ፡፡ ይህ ሥራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ በከባድ የአየር ሁኔታ ውስጥ የሚሰሩት ኢትዮጵያውያን በዚህ ግድብ መሥራታቸው ያኮራቸዋል፡፡ ልዩ ስሜት ይሰጣቸዋል፡፡ በጉባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ የተጫነው ከባድ የህዝብ አደራ ነው፡፡ ሸክሙም ከባድ ነው፡፡ እረፍት የሚነሳ የህዝብ አደራ በተሸከሙት የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ቅናት የአደረብኝን ያህል፤ በኃላፊነታቸው ክብደት ሥጋት አድሮብኛል፡፡ 24 ሰዓት ያለ ማቋረጥ የሚሰራ ግድብ ነው፡፡ ጉባ የሐይማኖት ይዘት ያለው ሥፍራ እንጂ፤ ፍጥረተ አዳም የሚሰራው ተራ አዳማዊ ግብር የሚከናወንበት ሥፍራ አይመስልም፡፡ በአጠቃላይ፤ በጉባ የሚታየው የስራ መንፈስ ድህነት ከነሠራዊቱ በጉባ ተራራዎች መሽጎ ከኢትዮጵያውያን ጋር ጦርነት የገጠመ መስሎ ይታየናል፡፡ በአድዋ ጦርነት አንድ አርበኛ ከጠላት ጋር ሲፋለም ብንመለከት ሊፈጠርብን የሚችለው ስሜት ያድርብናል፡፡ በእያንዳንዱ የግድቡ ሠራተኛ ገጽ የሚታየው መንፈስ፤ በአድዋ ጦር በአርበኞች ላይ ሊታይ ከሚችለው መንፈስ የሚለይ አይመስለኝም፡፡ በጉባ በሠራተኞች ገጽታ ላይ የሚታየው ወኔ እና ቁርጠኝነት በአድዋ ጀግኖች ገጽታ ላይ ከሚታየው የተለየ አይሆንም፡፡ በአድዋ ጦርነት ደም፤ በዚህኛው ጦርነት ላብ የሚፈስስ ከመሆኑ በቀር፤ ሌላ ልዩነት ያለ አይመስለኝም፡፡ በአድዋ ጦርነት የጸረ ቅኝ አገዛዝ የትግል መንፈስ የቀሰቀሰው ያ ታላቅ ድል፤ የጥቁር ህዝቦችን መንፈስ እንደ አላዛር ከተስፋ መቁረጥ መቃብር አስነስቶ፤ በርካታ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን ለፀረ- ኮሎኒያሊስት ትግል እንዲነሱ ማድረግ እንደቻለ፤ በህዳሴው ግድብ ግንባታ የምዕራባውያን የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መስራት አይቻልም የሚለውን ስሜት ከአፍሪካውያን አዕምሮ ሊፍቅ ይችላል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር ህዝብ ሲሦ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በአባይ ተፋሰስ ነው፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን ሐገራት ህዝቦች ሁሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብጽ ህዝብ ልብ ከዚህ ሥፍራ ነው፡፡ ይህ ግድብ መብራት ብቻ ሳይሆን የፍቅር እና የትብብር መንፈስ የሚያመነጭ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመንፈስ ትንሳዔ መፍጠር የሚችል ግድብ ነው፡፡ ጉባ የተከተመው የኢትዮጵያ የልማት ሠራዊት፤ ከአድዋው የተለየ ነገር አለው፡፡ የጉባ ሠራዊት ምርጥ ቴክኖሎጂን በብቃት የታጠቀ ሠራዊት ነው፡፡ በጉባ የጸረ – ድህነት ትግል ደጀን የሆነው እና የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በአማካይ ስሌት በቀን አንድ የጎብኚ ቡድን ፕሮጀክቱን ለመጎብኘት ወደ ጉባ ይመጣል፡፡ ጉባ እና ሲርባባ በተባሉ ሁለት ኮረብታዎች መካከል የሚገነባው ዋናው ግድብ በማታ በጉልህ ይታያል፡፡ ከግድቡ ግራ እና ቀኝ በተተከሉት ትላልቅ የመብራት አምፑሎች (ባውዛዎች) ሥር አንበጣ ወይም ተርብ የመሰሉ በራሪ ነፍሳት ሞተው ይታያሉ፡፡ ማታ – ማታ የሚበራው ይህ ከፍተኛ ኃይል ያለው ብርሃን ሲበራ፤ በብርሃኑ እየተሳቡ እንደ እሣት ራት እየበበረሩ የመጡ በርካታ ነፍሳት፤ ከመብራቱ ምሰሶ ሥር ሞተው ይታያሉ፡፡ ለአፍንጫ የሚከረፋ መጥፎ ጠረን ተሰማኝ፡፡ ነፍሳቱ፤ ከዛፍ ሥር የወደቀ ቅጠል መስለው ይታያሉ፡፡ ይህ ነገር የተምሣሌት ማዕረግ ይዞ ታየኝ፡፡ ለኢትዮጵያ የተስፋ ብርሃን ሆኖ በቆመው በዚህ ግድብ ላይ አፍራሽ ዓላማ ይዘው ውር-ውር ከሚሉ ወገኖች፤ ከእነዚህ ነፍሳት ጋር ተመሳስለው ታዩኝ፡፡ ቀና ብለው ሲመለከቱት ሰማዩን የሚኮለኩል መስሎ ከሚታየው እና ታላቅ የብርሓን ጎርፍ ከሚያፈሰው ግዙፍ ምሰሶ እግር ሥር የወደቁ የሬሳ ክምሮች ሆነው ታዩኝ፡፡ ከእነሱ ወዲያ ማዶ የጉባ አበባዎች ታዩኝ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy