NEWS

ህገመንግስታዊ ስርአቱ በአለት ላይ እንደተገነባ ቤት ነው

By Admin

January 19, 2017

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሳምንት ሁለት ግዜ ለህዝብ ቀርበዋል፤ አንድ የሃገሪቱ የግልና የህዝብ ሚዲያዎች እንዲሁም የውጭ ሃገር ሚዲያዎች በተሳተፉበት ጋዜጣዊ መገለጫ፣ ሁለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ምክር ቤት ቀርበው። የህዝብ ውክልና ያለው መንግስት አፈጻጸሙን ለህዝብ ይፋ ማድረግ የጠበቅበታል፣ የህዝብንም አሰተያየት ጥያቄ መቀበል ይኖርበታል፤ የመንግስት ግልጽነት አንዱ መገለጫ ይህ ነው። የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ሰአት በላይ ለሆነ ግዜ ለህዝብ ጥያቄና አሰተያየት ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው የመንግስት ግልጽነት አካል ነው። ይህ መሪዎች ሚዲያና የህዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡበት መድረክ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መገለጫ ነው። ብዙዎቻችን መሪዎች ሚዲያ ፊት ቀረበው ሲፋጠጡ እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ እንደራሴዎች ከወካዮቻቸው ተቀብለው ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ጋር መጋፈጥ በለፉ ሃያ አምስት ዓመታት የተለመደ በመሆኑ ብዙም ዋጋ አንሰጠውም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በዘውዳዊና ወታደራዊ ስርአት ለኖሩ፣ ለኖሩ ብቻ ሳይሆን ያኔ የነበረውን ለሚያስታውሱ ግን ትልቅ ለውጥ አለው። በዘውዳዊው ስርአት ዘመን ዜጎች ንጉሰነገስቱ ሚዲያዎች ፊት ቀርበው ባጋዜጠኞች ሲፋጠጡ ወይም ፓርላማው ሲሞገታቸው አይተው አያውቁም። ስለንጉሱ ሲያስታውሱ፣ ከእለታት በአንዱ ለጉብኝት ወደከተማቸው ወይም መንደራቸው መጥተው ነጭ ሽንግሎች ለህዝብ ሲያድሉ ማየታቸውን፣ ለታቦት ንግስት ቤተክርስቲያን ሄደው እዚያ እንደተመለከቷቸው፤ ከኮሌጅ ሲመረቁ ዲፕሎማቸውን ከንጉሱ እጅ መቀበላቸውን ወዘተ ከመናገር አያለፉም። በወታደራዊው ደርግም እንዲሁ ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም አብዮት አደባባይ ረጅም ንግግር ሲያደርጉ፣ በኢሰፓአኮ ወይም ኢሰፓ ጉባኤ ላይ ጠዋት ጀመሮ ምሽት ላይ የሚያበቃ ሪፖርት ሲያቀረቡና መፈክር ሲያሰሙ ከማስታወስ አያልፉም። ሁለቱም ስርአቶቸ የህዝብ ውክልና ስላልነበራቸው እንደራሴዎች ፊት ቀርበው አይሞገቱም። ራሳቸው ከሚመሩት ሚዲያ ውጭ የግል ሚዲያዎች ስላልነበሩ በሚዲያዎች አይጠየቁም። በሆነ አጋጣሚ የማይፈቅዱትን የጠየቋቸው ሰዎች ወይም ሊሞግቷቸው የሞከሩ ሰዎች ቢኖሩ የእድሜ ምእራቸው እዚያው ላይ ነበር የሚዘጋው። አናም የመሪዎቻቸውን በእንደራሴዎች መሞገትና በሚዲያ ፊት መፋጠጥ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መገለጫ ነው። የአሁኑ ትውልድ መሪዎቹን የሚያውቀው ፓርላማ ፊት ቀርበው ማብራራያ ሲሰጡ አለያም በሚዲያ ሲፋጠጡ ነው። ልብ በሉ ዴሞክራሲያችን አድጎ በቅቶታል እያልኩ አይደለም፤ ዳዴ ጀመሯል እያልኩ እንጂ። ገና ብዙዙዙ… ይቀረናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ሰሞኑን ለህዝብ መቅረብ የቆሰቆሰብኝን ስሜት ይህን ያህል ገልጬ፣ በእንደራሴዎች ፊት ቀርበው ካነሷቸው ጉዳዮች መሃከል በተለይ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የሚመለከቱ ጉዳዮች በመጠኑ ልመለከት ወድጃለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል። እርግጥ ነው የአስቸኳይ ገዜ አዋጁ የህዝቡ ሰላማዊና የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት እንዲቀጥል አድርጓል። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ያለፈው ዓመት የሰሜኑ፣ የምዕራብና የምስራቁ በኋላም የደቡቡ የሃገራችን ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት ርቆት ነበር። የዚህ ሰላምና መረጋጋት መጥፋት ቀስቃሽ የመንግስት የህግና ፖሊሲ አፈጻጸም ችግር በህዝብ ላይ ያሳደረው ቅሬታ ቢሆንም፣ ህዝቡ አውዳሚው ሁከት እንዲቀሰቀስ የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። 2 ህዝብ ከመንግስት ይጠብቅ የነበረውን አገልግሎት ባለማግኘቱ እንዲሁም የደረሰበትን መጎዳት የሚሽር መላ ጠብቆ በማጣቱ ተስፋ በመቁረጥ ምንግስት እንዲሰማው ነው ተቃውሞ ቀመስ አቤቱታ ያቀረበው። ይሁን እንጂ፣ በተለይ የመንግስት አፈጻጻም ችግር ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የነበረው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል አቤቱታውን ለማሰማት አደባባይ ሲወጣ፣ ሃገሪቱን ለማተራመስ የሚያስችል አጋጣሚ ሲጠብቁ የኖሩት የኢትዮጵያ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው በማህበረዊ ሚዲያ የአውዳሚ ሁከት ክተት አውጀዋል። ይህ የማህበራዊ ሚዲያ ከተት ወጣቱን በተለያየ ፅንፍ – ገሚሱን በትምክህተኝነት፣ ሌላውን በጠባብነት አመለካካት ውዥንብር ውስጥ በመክተት አቤቱታውን ከማሰማት ይልቅ በስሜታዊነት ለውድመት እነዲነሳሳ አድርጎታል። ይህ አካሄድ መንገድ በመንግስት የአፈጻጸም መዛነፍ ለደረሰበት ችግርና ላነሳው ጥያቄ ምላሽ ማስገኘት የሚችል አልነበረም። ተገቢ ጥያቄውን ጠልፈው ወደአውዳሚ ሁከት ያስገቡት የሃገሪቱ ጠላቶችና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ተላላኪዎቻቸውም ለጥያቄው ምላሽ የመስጠት ፍላጎት፣ አቅምም የላቸውም። የሃገሪቱ ጠላቶችም ሆኑ የተላላኪዎቹ መድረሻ ያሀገሪቱን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ ያኖረውን ህገመንግስታዊ ስርአት በመናድ ሃገሪቱን ማፈረስ ነው። ህገመንግስታዊ ስርአቱ ከተናደ ሃገሪቱ እንደምትፈርስ ያውቁታል። ይህን ራሳቸው በቀጥታ ሊያደርጉ ያልቻሉትን የጥፋት ዓላማ በሃገሪቱ መፍረስ ቀዳሚ ተጎጂ በሆኑ ዜጎች አማካኝነተ ለማሰፈጸም ነበር የሞከሩት። ባለፈው አመት ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት አሳዛኘ የሚያደርገው ይህ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ጠላቶችና በተላላኪዎቻቸው አዝማቸነት፣ ውዥንብር ውስጥ በገቡ ዜጎች አማካኝነት የተፈጸመ ሁከት የንጹሃንን ህይወት – በአዋኪዎቹም በሰላም አሰከባሪዎቹም ወገን እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴዎች እንዲገደቡ አድርጓል። በእለት ስራ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ ሁከት የተቀሰቀሰባቸው ከተሞች ነዋሪዎች የእለት ጉርሳቸውን አጥተዋል። ለህዝብ የንጹሀ መጠጥ ወሃ አቅርቦት የሚሰጡ ተቋማት፣ የህክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ ተደርጓል። በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዲወድሙ ተደርጓል። ይህ በቀዳሚነትና በዘላቂነት የጎዳውና የሚጎዳው ህዝቡን ነው፣ በማወደሙ ላይ የታሰተፉትን ጭምር። እንግዲህ የአስቸኳይ ግዜ ሁኔታው የታወጀው፣ ይህ ህዝቡ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሃገሪቱን የማፈረስ ዘመቻ በተለመደው ህግን የማሰከበር አካሄድ መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። አዋጁ መንግስት በዘፈቀደ ያወጀው ሳይሆን ህገመንግስታዊ መሰረት ያለውና የዜጎች ሰብአዊ መበቶች ላይ ጥሰት እንዳይፈጸም መቆጣጣር የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ያለው ነው። በሁከቱ በድንገት ያልጠበቀው ጉዳት የደረሰበትና የዘላቂ ሰላም እጦት ስጋት ያደረበት፣ የሰላምን ፋይዳ ላለፉ ሃያአምስት አምስት አመታት ሲያጥጥም የኖረው ህዝብ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋት በማስፈኑ ደስተኛ ሆኗል። ቀድሞውኑ ሰላምና መረጋገቱን የሚመልስ እርምጃ እንዲወስድ መንግስትን ሲወተውት ነበር። እርግጥ አሁንም ሃገሪቱን የማፍረስ ሁከት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪዎች ጥረት እያደረጉ ነው። ሰሞኑን የኤርትራ መንግስት የፌስ ቡክ ገጾች በጎንደር ከተማ በድምቀት የሚከበረውን የጥምቀት በአል እንደ ኢሬቻው ደም የሚፈስበት ለማድረግ የሚያካሂዱትን ቅስቀሳ ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ የቻላል። የጎንደር ህዝብ እነዚህ የኤርትራ ቡደኖች ለጥያቄው መልስ ሊሰጡ እንደማይችሉና ይህን የማድረግ ዓላማም እንደሌላቸው፣ ከዚያ ይልቅ በገዛ እጁ ሃገሩን እንዲያፈርስ እየተጠቀሙበት መሆኑን ተገንዝቦ ሰላሙን ለመጠበቅ ሊቆም ይገባዋል። አስተዋይ አንዴ ነው የሚሳሳተው። ሁለቴ የሚሳሳተው ምንም የማያውቅ ቂል ብቻ ነው። እናም ጎንደሬ እንዳትሞኝ። 3 ያም ሆነ ይህ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ ብዙ አስረጂ ሊቀርብለት የሚገባ ጉዳይ አይደለም። አሁን በመላ ሃገሪቱ ሰላምና መረጋገት ሰፍኗል። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንደወትሮው እየተከናወኑ ነው። አርሶ አደሩ የመኸር ሰብሉን እየሰበሰበ ነው። በብዙ የሃገሪቱ አካባቢዎች የመኸር ሰብል ተሰብስቦ እያበቃ ነው። ይህ ከ80 በመቶ በላይ የሃገሪቱ ህዝብ የተሰማራበትና በሃገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የግብርና ኢኮኖሚ በዚህ አኳኋን መከናወን የቻለው የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወደነበረበት በመመለሱ ነው። ያም ሆነ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ማስቀጠል ችሏል ሲሉ የገለጹት ይህንን ነው። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የተመለከተም ጥያቄ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተነሰቶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት መቀልበስ አስቸሏል ብለዋል። እርግጥ ነው የባለፈው ዓመት ሁከት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተቋማት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ውድመትና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሳርፎ የነበረውን ገደብ የሚያስታውሱ ዜጎች፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት በምን ያህል መጠን እንዳቃለለ መገመት ይችላሉ። ምናልባት ከጥቅምት ወዲህ ባሉት የሁለተኛው ሩብ አመት ሶስት ወራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እድገት መቀዛቀዝ የሚያሳዩ አሃዞች ሊኖሩ ይችላሉ። እድገቱ እንደተጠበቀው አይሁን እንጂ ባለፈው አመት ከነበረው ግን አላሽቆለቆለም። ለምሳሌ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፤ በ2007 በጀት አመት ከጥቅምት እሰከ ታህሳስ ባሉት ሶስት የሁለተኛው ሩብ አመት ወራት ወደ ሀገሪቱ የመጡ ቱሪስቶች ቁጥር 207 ሺህ 600 የተገኘውም ገቢ ደግሞ ከ777 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነበር። በ2008 ተመሳሳይ ወቅት የቱሪሰቶች ቁጥር ወደ ከ243 ሺህ 879፣ የተገኘው ገቢ ደግሞ ወደ 913 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አድጓል። ይህ የቱሪዝም ዓመታዊ እድገት በያዝነው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አልተመዘገበም። የዘንድሮው 2ኛ ሩብ አመት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ተመጣጣኝ ነው። ከአንድ በመቶ በታች ማለትም 0.84 በመቶ ብቻ ነው የቀነሰው። ይህ የእድገት መቀዛቀዝ የተፈጠረው ግን በአስቸኳይ ገዜ አዋጁ ምክንያት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአሰቸኳይ ገዜ አዋጁ ቀደም ሲል በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው ሁከተና ግርግር ምክንያት ነው። አስቸኳይ ግዜ አዋጁ ይህን ሁከትና ግርግር በማስወገድ፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሰይ ወቅት ጋር የሚመጣጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ውጤት ማግኘት አስችሏል። የአስቸካይ ግዜ አዋጁ ባይታወጅና ሁከቱ በነበረበት ቢቀጥል ኖሮ፣ እንኳን ከባለፈው አመት ጋር ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው የውጭ ቱሪስቶች ወደሃገራችን ለመጡ እኛም ለአለት እንጀራችን ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ አንችልም ነበር። ሃገራችንም በታሪክ ብቻ የምትታወስ ሆና ለመፍረስ ጠርዝ ላይ ትደርስ ነበር። በአጠቃላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት መልሶ አስቀጥሏል። በሀዝቡ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ውዥንብር በማጥራት የሁከቱን ቀጣይነት እድል አጥብቧል፤ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ወደነበረበት መልሷል። በዚህ አኳኋን የኢትዮጵያ ህገመንግስታዊ ስርአት በአሸዋ ላይ የተገነባ ሳይሆን ሳይሆን በአለት ላይ የተገነባ በሁከትና ግርግር በቀላሉ የማይናወጥ ጽኑ መሆኑን አሳይቷል።