Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሚዲያና መልካም አስተዳደርን የመደገፍ ተግባሩ

0 868

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሚዲያና መልካም አስተዳደርን የመደገፍ ተግባሩ

ቶሎሳ ኡርጌሳ 1-10-17

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ተግባሩን በማረጋገጥ ብቻ የሚገለፅ አይደለም— የህልውና ጉዳይ እንደሆነም ተደጋግሞ ተገልጿል። ለዚህም በማሳያነት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ የህዝብ እርካታንና አመኔታን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ውጥን መያዙን መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል። ይህም ሀገራችን ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው። እናም በየደረጃው መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የግልፅነትና የተጠያቂነት ስርዓትን በሁሉም መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ዕውን ለማድረግ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው። ለነገሩ መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሰረት ነው። እናም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ መረባረብ ወሳኝ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል የኢፌዴሪ መንግስት ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ጀምሮ ዛሬ ላይ የሚገኘው። በእኔ እምነት እነዚህ የመልካም አስተዳደር ጥረቶች የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙና የመንገስትን ስልጣን የግል ኑሮ ማደላደያነት የሚጠቀሙ ግለሰቦች ሳቢያ የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልተቻለም። እርግጥ መልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ ከህዝቡ ባሻገር፤ በዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋምነት የተገራጁ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዴሞክራሲ ተቋምነት ተመዝግበው እዚህ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመንግስትም ይሁን በህዝቡ ዘንድ የሚጠየቀውን የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን በመፍታት እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሚኖራቸው ሚና የሚናቅ አይደለም። ከእነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት ውስጥ ሚዲያ አንዱ ነው። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የማስተማር፣ የማሳወቅና የማዝናናት ሚናን ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሚዲያ፤ የመልካም አስተዳደርን ምንነት ከማስተማር ባሻገር፣ በሀገራችን ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማሳየትና ችግሮቹን በማረም ረገድ የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሚዲያ አግባብ ባልሆነና ከራሱ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ የሚያስከትለውን ችግር ያህል፤ በአግባቡና ስነ ምግባሮቹን ጠብቆ ከሰራ የሚያበረክተው ማህበራዊ ኃላፊነት (Social Responsibilty) ከፍተኛ ነው። በተለይም የሚዲያ ሙያ እምብዛም ባልዳበረባቸው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ ሚዲያ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ከሰራ የሚጠበቅበትን ተግባር በበቂ ሁኔታ የሚወጣ ይመስለኛል። እናም እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ተግባሮችን የማስተማርና የማሳወቅ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን በመመርኮዝ ተግባሩን ከተወጣ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱ አይቀርም። በእኔ እምነት ሚዲያው በቅድሚያ በግርድፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመንቀስ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ማስተማር ይኖርበታል። ይህም በተለያዩ ወገኖች መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን የተለያየ አስተሳሰብ በተቻለ መጠን ወደ አንድ ለማምጣት ያግዛል ብዬ አስባለሁ። መልካም አስተዳደር የሂደት እንጂ የአንድ ጀምበር ስራ አለመሆኑን ማስተማር ይገባል። እንኳንስ እንደ እኛ ያለ የዴሞክራሲ ጀማሪ ሀገር ቀርቶ፤ ተግባሩን ዕውን በማድረግ ከሁለት ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩት ምዕራባውያንም 2 ቢሆኑ ዛሬ የደረሱበት የመልካም አስተዳደር አፈፃፀም የተሟላ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ይህ ሃቅም በአንዳንድ ወገኖች ውስጥ ‘መልካም አስተዳደር ለምን አሁን ሙሉ ለሙሉ ዕውን አልሆነም?’ በማለት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን ብዥታንም የሚያጠራ ይመስለኛል። ይህን ማለቴ ግን ‘መልካም አስተዳደር ጊዜ ስለሚያስፈልገው ምንም ዓይነት የማስተካከያ እርምጃ አይወሰድ አሊያም በደፈናው እዚህ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም’ እያልኩ አይደለም። ልልም አልችልም። መንግስትም ቢሆን የሚክደው ሃቅ አይደለም—በግላጭ ችግሩን ከማመን ጀምሮ፣ በችግሩ ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎችን እስከመውሰድ የደረሰበት አስቸጋሪ ክስተት ነውና። እናም ሚዲያው ስለ መልካም አስተዳደር ሲያስተምር ስለ ምንነቱ፣ አፈፃፀሙና ተግዳሮቶቹ በተገቢውና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ በማንሳት ጭምር መሆን ይኖርበታል። ይህ ሲሆንም በመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት የሚፈጠሩ የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ወንጀሎችን በተጨባጭ ማስረጃዎችና መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ በማሳየት ህዝባዊ ኃላፊነቱን ይወጣል። ሚዲያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማነት የህዝብን ተሳትፎ የሚያጎለብት አጀንዳ በመንደፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት አሰራር ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳወቅ ከፍ ሲልም በማጋለጥ ሀገራዊ ሚናውን መወጣት ያለበት ይመስለኛል። ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሳውን የህግ የበላይነትን ማስተማርና ህፀፆች ሲኖሩም የመጠቆም ስራዎች ከሚዲያ ይጠበቃል። ይህን በመመስረትም ሚዲያው የህግ የበላይነት ለሁሉም ዜጎች የተሰጠና ምንም ዓይነት ልዩነት የማይደረግበት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሆኑንም ማሳወቅና ማስተማር ይገባዋል። ይህም አንዳንድ ወገኖች ውስጥ ያለን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ ያግዛል። እርግጥ የመንግስት አካላትና ኃላፊዎች ፖሊሲዎቻቸውን በየቀኑ የሚቀያይሩ ከሆነ ህዝብ የጣለባቸውን አደራ ይወጣሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። ለነገ ብለው የሚያቅዱት ነገርም ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። እናም የህግ የበላይነት ሲኖር፤ ህጎች በምክር ቤት ውይይት አማካኝነት ፀድቀው ካልሆነ በስተቀር በየቀኑ አይቀያየሩም። ማንኛውም ሰው በእነዚህ ህጎች ስር ሆኖ ስለሚሰራና ህጎቹንም የሚተላለፍ ተጠያቂ ስለሚሆን ከህግ ውጪ እንዳሻው የሚሆን ዜጋ ሊኖር አይችልም። በመሆኑም የህግ ልዕልና ይረጋገጣል ማለት ነው። ታዲያ ከዚህ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ውጪ በመንግስት ስራ አስፈፃሚዎችም ይሁን በተቃዋሚዎች ዘንድ መኖሩ አይቀርም። ለዚህ አባባሌ በተለያዩ ወቅቶች ሲነሱ የቆዩ ሁለት ፅንፎችን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፤ በሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎችና በመንግስት አስፈፃሚ አካላት መካከል። ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል አባሎቻቸው በተለያዩ መንገዶች ከሀገሪቱ ህጎች ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ “የህግ የበላይነት የለም” ይላሉ፤በሌላው ወገን ደግሞ የመንግስት አስፈፃሚዎች ‘በህግ በተያዘ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አንገባም” ሲሉ ይደመጣሉ። እናም ሚዲያው አንዱን ፅንፍ አንጠልጥሎ መሄድ አይኖርበትም። የትኛው ወገን ትክክለኛ እንደሆነ ለህዝቡ ግልፅ የሆነ ምስል መፍጠር ይኖርበታል። ለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸውን ባለሙያዎች በማነጋገር ተገቢውን የምስል ክሰታ ከራሱ ፍረጃ ውጪ ማሳየት ይኖርበታል። በዚህም ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ዕውን የህግ የበላይነት እዚህ ሀገር ውስጥ የለምን?፣ ዕውን ለተቃዋሚዎቹ አንድ ይም ሁለት አባላት ሲባል የሚቀለበስ ህግ ይኖራልን? የህግ የበላይነትን በማስከበር መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?…ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አግባብ ያለውን ዘገባ ጥልቀት ባለው 3 መንገድ መስራት ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ በአንድ ወገን ዕይታ ከሁለት ለአንዱ በመወገን መዘገብ ማህበራዊ ሃላፊነትን እንዳለመወጣት የሚቆጠር ነው። እርግጥ መልካም አስተዳደርን በተመለከቱ ዘገባዎች ላይ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝብ በቀዳሚ የመረጃ ምንጭነት መጠቀም ይገባል። ምክንያቱም የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት ለዘገባው የሚሆን የዳበረና ተዓማኒ መረጃና ማስረጃ ማግኘት ስለማይቻል ነው። ሚዲያ ከመልካም አስተዳደር አፈፃፀም አኳያ ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት የሚባሉትን እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመሳሰሉ የመረጃ ምንጮችን በተገቢው መንገድ ሊጠቀምባቸው ይገባል። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በመንግስትም ይሁን በህዝቡ ዘንድ አፈፃፀሙ ያማረ እንዲሆን የመፈለገውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ሚዲያው ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በዚህ ረገድ ሚዲያው የሚጠበቅበትን ተግባር በሚፈለገው መጠን ተወጥቷል ተብሎ የሚገለፅ ባይመስለኝም፣ እየታዩ ያሉት ጅምር ተግባሮቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ከአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ተላቅቆ የመልካም አስተዳደር ጉዳይን በዘላቂነት በመያዝ በዚህ ሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል እላለሁ—መልካም አስተዳደር የሀገራችን የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደ ተግባር ነውና።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy