English

ስሙን የቀየረው ፒቲኤ ባንክ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች 60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለቀቀ

By Admin

January 29, 2017

– ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች አገልግሎት የሚሰጠውን ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይከፍታል

ከተመሠረተ 30ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የንግድና የልማት ባንክ (ፒቲኤ ባንክ) ስያሜውን በመቀየር ወደ ንግድና ልማት ባንክነት በተቀየረበት ሰሞን፣ ለሦስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች 60 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማፅደቁን አስታወቀ፡፡

አዲሱን ስያሜውን በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ይልማ ታደሰ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንይ ጄነራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ፣ እንዲሁም ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እያንዳንዳቸው የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከሦስቱ ኩባንያዎች በተጨማሪ ሌሎችም በድርድር ሒደት ላይ የሚገኙ እንዳሉና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል ለመክፈት በካሊብራ አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ከፈረንሣዩ አኮር ግሩፕ ጋር ስምምነት ያደረገው እንይ ኩባንያ፣ አኮር ከሚስተዳድራቸው ውስጥ ፑልማን የተባለውን ብራንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ለመክፈት የ20 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ እንደሚያስፈልገውና ከፈረንሣይ አበዳሪ ተቋማት ብድሩን ለማግኘት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ ይሁንና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ ተቋም (ኮሜሳ) ባንክ ከሆነው የንግድና የልማት ባንክ ብድሩን ሊያገኝ በመቻሉ፣ የሆቴል ፕሮጀክቱን በቅርቡ ዕውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ጋቴፕሮ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያም የ20 ሚሊዮን ዶላር ብድር የፀደቀለት ለሚገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አቶ አድማሱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር ለመልቀቅ ባንካቸው ዝግጁ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ብድር ለመስጠት ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የአሁኑ የንግድና የኢንቨስትመንት ባንክ ከዚህ ቀደም ለሐበሻ ሲሚንቶ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቁን አቶ አድማሱ አስታውሰዋል፡፡ ከሐበሻ ሲሚንቶ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ብድር እንደሚለቀቅለት መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ባንኩ ለኢትዮጵያ ከሚሰጣቸው የፋይናንስ አገልግሎቶች በተጨማሪ በጎረቤት አገሮች ማለትም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለሚገኙ አገሮች ተደራሽ የሚሆን የቀጣናውን ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ለመክፈት እንዲችል፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ከወራት በፊት ያደረገውን ስምምነት ወደ ተግባር በመለወጥ በኦሎምፒያ አካባቢ ጽሕፈት ቤቱን ለመከፈት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን አቶ አድማሱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሰው ኃይል ማሟላትን ጨምሮ፣ ከውጭ የሚገቡ ልዩ ልዩ መገልገያዎች እንዲመጡለት ማዘዙን ጠቁመዋል፡፡

በቡሩንዲዋ ዋና ከተማ ቡጁምቡራ የነበረውን ጽሕፈት ቤት በአገሪቱ በተከሰተው ብጥብጥ ምክንያት ለመዝጋት መገደዱ ታውቋል፡፡ የቡጁምቡራ ጽሕፈት ቤቱን ወደ ኬንያ ያዛወረው የንግድና የልማት ባንኩ፣ በታሪክ በአንድ ጊዜ ሲፈቅድ የመጀመርያው የሆውን የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኬንያ አፅድቋል፡፡ የባንኩን ስያሜ መቀየር ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል በየጊዜው እያደገና ለውጥ እያሳየ ከመምጣቱ ጋር እንደሚያያዝ፣ ከዚህም ባሻገር የኮሜሳ አባል ያልሆኑ አገሮችንም ለማካተት ታስቦ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አድማሱ በዚህም እንደ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ሱዳንና ታንዛንያ ያሉ አገሮች በቅርቡ ወደ አባልነት መቀላቀላቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው አባል አገሮችን ጨምሮ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማትን በባለድርሻነት ያቀፈው ይህ ባንክ፣ በአቶ አድማሱ መመራት ከጀመረ ወዲህ የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅም በ300 ፐርሰንት በማሳደግ አራት ቢሊዮን ዶላር ማድረስ ችሏል፡፡ ለዚህ ለውጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱት አቶ አድማሱ በኮሜሳ ዋና ጸሐፊ ሲንዲሶ ንዴማ ንግዌንያ ተሞካሽተዋል፡፡

የባንኩ የዳይሬክትሮች ቦርድ አማካሪ እንዲሆኑ የተመረጡት የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዘዲንዳት ሩፒያህ ባንዳም ስለ አቶ አድማሱ ብቃት ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ባንዳ በወጣትነት ዘመናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራት ኪሎ ካምፓስ ተማሪ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በንግግራቸው ወቅት በአማርኛ ሰላምታ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡

አቶ አድማሱ በዓለም ትልቅ ክብርና ዝናን ካተረፉ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚና በባንክ ሙያ መስኮች ተቀብለዋል፡፡ በሐርቫርድ፣ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፖለቲካል ሳይንስ፣ እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓና  የካናዳ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ባለቤታቸው ሱፐር ሞዴል አና ጌታነህም ታዋቂነትን ያተረፈች የሞዴል ባለሙያ ከመሆኗም በላይ፣ አፍሪካ ሞዛይክ የተባለውንና በፋሽን ኢንዱስትሪው ተቀባይነት ያተረፈውን ዓመታዊ የፋሽን ትርዒት በማዘጋጀት ሁለት አሥርት ገደማ አስቆጥራለች፡፡ ከዚህ ሙያዋ በተጨማሪ ሕፃናትን የሚረዳና የኢትዮጵያ ሕፃናት ፈንድ የተባለ ግብረ ሰናይ ተቋም በአሌልቱ አካባቢ በመመሥረት ከባለቤቷ ከአቶ አድማሱ ጋር እያንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡