Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት እየተገነቡ ያሉ ዋሻዎች በቀጣይ 5 ወራት ይጠናቀቃሉ ተባለ

0 1,577

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት እየተገነቡ ያሉ ዋሻዎች በቀጣይ 5 ወራት ይጠናቀቃሉ ተባለ

በመቀሌ-ወልድያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት እየተገነቡ ያሉ ትላልቅና መካከለኛ ዋሻዎች ግንባታቸው በሚቀጥሉት አምስት ወራት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

እስካሁንም ቁፋሯቸው እየተከናወኑ ካሉ ስምንት ዋሻዎች ውስጥ እያንዳንዳቸው 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የሁለት ዋሻዎች ቁፋሮ ተጠናቋል።

ግንባታቸው የተጠናቀቀው የኮከሌ ዋሻዎች መሆናቸውን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

በዚህ የባቡር ፕሮጀክት ላይ ካሉት ዋሻዎች በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነው የማይሰልፊ ዋሻ ከ2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር በላይ ተጠናቋል።

ዋሻው በአጠቃላይ 3 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ነው።

የዚህ ዋሻ መጠናቀቅ ለፕሮጀክቱ መፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የፕሮጀክቱ ሀላፊ ገብረመድህን ገብረአሊፍ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ ዋሻዎች ለመጠናቀቅ ከ20 እስከ 25 ሜትር ግንባታ ይቀራቸዋልም ብለዋል።

ከእነዚህ ዋሻዎች ጎን ለጎን እየተገነቡ ካሉ 170 ድልድዮች ውስጥ 3 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን ጨምሮ በአጠቃላይ በስምንት ወራት ግንባታቸው ይጠናቀቃሉ።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የአፈር ሙሌትና ቆረጣ ስራም 67 በመቶ መጠናቀቁን ኢንጂነር ገብረ መድህን ገብረአሊፍ ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸምም 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ የእነዚህ ትልልቅ ግንባታዎች መጠናቀቅ በአጠቃላይ የባቡር መስመር ግንባታው ላይ ከፍተኛውን ደርሻ እንደሚይዝ ተጠቁሟል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ የደልድዮቹና የዋሻዎቹ ግንባታ መፋጠን እንዲሁም የአፈር ሙሌትና ቆረጣ ስራ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ያስችለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክቱ ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የመቀሌ-ወልድያ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy