ኢሕአዴግ ለቅድመ ውይይት ከጠራቸው 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በአቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ ቡድን የተገኘ ቢሆንም፣ በውይይቱ ላይ መሳተፍ የቻለው እስከ ሻይ ዕረፍት ድረስ ብቻ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ የሰማያዊ ፓርቲ ትክክለኛ መሪ ማን እንደሆነ በትክክል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ማለትም የተወሰኑ አባላት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መሆናቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ አቶ ይልቃል ጌትነት መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ለቅድመ ውይይት ባለቀ ሰዓትም ቢሆን እንዲገኙ ጥሪ ያቀረበላቸው ለእነ አቶ ይልቃል መሆኑን፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ እስከ ሻይ እረፍት ድረስ መሳተፋቸውን የገለጹት የፓርቲው ምክር ቤት አባላት አቶ ስለሺ ፈይሳና አቶ ይድነቃቸው አዲስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እነሱን ጨምሮ በውይይቱ ላይ 22 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፡፡
ነገር ግን ለሻይ እረፍት ወጥተው ሲመለሱ፣ እነ አቶ ስለሺ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ መጠራታቸውን፣ አቶ ሽፈራው ጠርተዋቸው ሕጋዊ የሰማያዊ ፓርቲ መሪ ማን እንደሆነ ሲጠይቋቸው፣ እነሱ የሚያውቁትና በምርጫ ቦርድም የሚታወቁት አቶ ይልቃል ጌትነት መሆናቸውን እንደገለጹላቸው ተወካዮቹ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲ በመደበኛ ጉባዔ የተመረጠ መሪ እንዳለው አቤቱታ ቀርቦላቸው፣ ከምርጫ ቦርድ ሲያረጋግጡ ትክክል መሆኑን ስለተረዱ ከሻይ ዕረፍት በኋላ መሳተፍ እንደማይችሉ ተገልጾላቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እያለ ኢሕአዴግ የሚፈልገውንና የሚስማማውን የፓርቲ መሪ እሱ የሚወስን መሆኑንና ይኼ ደግሞ በእነሱ የተጀመረ ባለመሆኑ ብዙም እንዳልገረማቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱ እንደ አገር ተገቢ አለመሆኑንና ሕግ ሊከበር እንደሚገባም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውን የገለጹትና ስለሰማያዊ ፓርቲ ማብራሪያና አቋማቸውን መግለጻቸውን የተናገሩት ሌላው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አገርና ሕዝብን የማረጋጋት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጥሪ ማቅረባቸውን ለሪፖርተር ተልጸዋል፡፡ በአቶ የሺዋስና በአቶ ይልቃል መካከል ያለውን ‹‹እኔ ነኝ ሊቀመንበር›› ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ምርጫ ቦርድ እያጠናው መሆኑን ገልጿል፡፡
ኢሕአዴግ ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው ቅድመ ውይይት ላይ የተገኙት 22 ፓርቲዎች፣ የየራሳቸውን ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማስገባት መስማማታቸው ታውቋል፡፡ አራት የተስማሙባቸው ነጥቦችም ቀጥሎ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች በማን እንደሚመሩ፣ በውይይቱ ላይ እነማን በታዛቢነት እንደሚሳተፉ፣ ውይይቱ ምን ዓይነት የአካሄድ፣ የአጀንዳና የንግግር ሥርዓት እንደሚኖረውና ከውይይትና ከድርድር በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እንዴት እንደሚሰጡ የሚገልጹ መሆኑም ታውቋል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com