ተሸናፊው የጋምቢያው መሪ ዕውቅና መነፈጋቸውን ኢትዮጵያ ደገፈች
– የአፍሪካ ኅብረት አዲሱን ተመራጭ አዲስ አበባ ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ሊጋብዛቸው ነው
ባለፈው ወር በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን ለማስረከብ አሻፈረኝ ያሉትን የጋምቢያ መሪ፣ የምዕራብ አፍሪካ አገሮችና አፍሪካ ኅብረት ዕውቅና አንሰጥም ማለታቸውን ኢትዮጵያ ድጋፏን ቸረች፡፡
በምዕራባዊቷ አፍሪካዊ አገር ጋምቢያ በታኀሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የተቃዋሚው መሪ አዳማ ባሮው፣ አገሪቱን ለ22 ዓመታት ያስተዳደሯትን ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህን ሳይጠበቅ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ በምርጫው ማግሥት ፕሬዚዳንቱ ጃሜህ መሸነፋቸውን በመግለጽ ለተተኪው ሥልጣን በአግባቡ ለማስረከብ ፈቃደኝነታቸውን ቢያሳዩም፣ ከቀናት በኋላ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት እንዲደገም ጠይቀዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ያህያ ጃሜህን ወዲያው በማውገዝ ሥልጣናቸውን ለአሸናፊው እንዲያስረክቡ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ)፣ ወታደራዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አገሮቹ አስታውቀዋል፡፡
ሐሙስ ጥር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በኒውዮርክ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤኮዋስ ለጃሜህ ዕውቅና አለመስጠቱን በሙሉ ድምፅ የደገፈው ሲሆን፣ ቅድሚያ ግን በዲፕሎማቲክ ጥረት ጃሜህን እንዲለቁ ማድረጉ ይበጃል ሲልም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ለፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ቋሚ ያልሆነ ውክልና አግኝታ የተመረጠችው ኢትዮጵያም የኤኮዋስን ዕርምጃ በተመለከተ ድምፅ በመስጠት፣ የማኅበረሰቡን ዕርምጃ በመደገፍ ለአዲሱ ተማራጭ ፕሬዚዳንት ባሮው ድጋፏን አሳይታለች፡፡
የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ዶ/ር ተቀዳ ዓለሙ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመሄዳቸው በፊት አፋጣኝ ዕርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት ሊፈቀድ አይገባም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ በበኩላቸው ተማራጩ ባሮው በጎረቤት አገር ሴኔጋል በሚገኘው የጋምቢያ ኤምባሲ ቃለ መሀላ መስጠታቸውን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኮሚሽነሯም አዳማ ባሮው ከሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ በሚጀምረው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንዲገኙ፣ ከሌሎች የአኅጉሪቷ መሪዎች ጋር ትውውቅ እንዲያደርጉ እንደሚጋብዟቸውም ገልጸዋል፡፡
የቀጣናው አገሮች ኤኮዋስ በጋምቢያ ለሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ሴኔጋልን በፊታውራሪነት የመረጡ ሲሆን፣ የሴኔጋል ጦር ባለፈው ሐሙስ ከቀትር በኋላ የጋምቢያን ድንበር አልፎ በመግባት ወደ ዋና ከተማዋ ባንጁል መቃረቡን የሴኔጋል መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ግን ጦርነትና ኃይል የመጠቀምን አማራጭ አልደገፈም፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሐሙስ ቀትር ላይ ሥልጣን እንዲያስረክቡ ቢጠበቁም፣ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ይልቁንም በፓርላማቸው አማካይነት የሦስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ በሥልጣን እንደሚቆዩ ገልጸዋል፡፡
ኤኮዋስ እስከ ዓርብ ቀትር ድረስ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን በማስረከብ አገሪቱንም እንዲለቁ ጊዜ የሰጣቸው ሲሆን፣ ዓርብ ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ጃሜህ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ተስማምተዋል፡፡
ከአፍሪካ ኅብረትና አባል አገሮች በተጨማሪ፣ አሜሪካና ሌሎች የምዕራብ ኃያላን አገሮች ጃሜህ መልቀቅ እንዳለባቸው በመጠየቅ ለአዲሱ ተመራጭ ዕውቅናቸውን ሰጥተዋል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com