Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሰር ኩባንያ በራሱ ተነሳሽነት የገነባውን አረንጓዴ ፓርክ አጠናቆ ለሥራ እንዳዘጋጀ አስታወቀ

0 579

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የመንገድ ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው አሰር ኮንስትራክሽን፣ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገበት የአረንጓዴ ፓርክ ግንባታን አጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዳበቃ አስታወቀ፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ አብርሃ እንደገለጹት፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ የሥራ ሒደት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት አረንጓዴው ፓርክ ተገንብቶ ለሥራ ተዘጋጅቷል፡፡ በቦሌ፣ ሩዋንዳ አካባቢ ካራማራ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው ተሻጋሪ መንገድ ሥር የተገነባው ፓርክ 6064 ካሬ ሜትር ሥፋት ያለው ነው፡፡ የግራና ቀኝ መንገድ አካፋዮችን ተከትሎ የተሠራው ይህ ፓርክ፣ ለአካባቢውና ለአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ ከሚሰጠው የገጽታ ለውጥ ባሻገር የተለያዩ አገልግሎቶችን ያካተቱ ግንባታዎችንም አኳቷል፡፡

ዘመናዊነቱ የተነገረለት ይህ ፓርክ በከተማው እምብርት፣ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ባለበት የአፍሪካ ጎዳና ላይ መገንባቱ ለከተማዋ ገጽታም ብቻ ሳይሆን ለዕይታ ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ፓርኩ ለሕዝብ ክፍት ተደርጎ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት 70 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በተለያዩ ዕፅዋቶች ያሸበረቀ አረንጓዴ ሥፍራ፣ የልጆች መጫወቻ፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ መቀመጫ ወንበሮች፣ መፀዳጃ ቤቶችና የገላ መታጠቢያዎችን እንዲያካትት ተደርጓል፡፡ ለአዛውንቶችና ለወጣቶች ማረፊያ ቦታ፣ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ካፍቴሪያ፣ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የውኃ ፏፏቴዎች፣ ልዩ የሙዚቃ ማጫወቻ የድምፅ ሲስተም፣ የጥበቃ ካሜራዎች፣ የአፍሪካ አገሮችን ባህሎች የሚያንፀባርቁ ቅርጻ ቅርጾችና ሥዕሎች የተጌጠው ፓርኩ፣ ሌሎችንም አገልግሎቶች እንዳካተተ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አሰር ኮንስትራክሽን ይህንን ግንባታ ያካሄደው በራሱ ተነሳሽነት የማኅበረሰብ ኃላፊነቱን ለመወጣት ነው ተብሏል፡፡ ተቋራጩ ደረጃ አንድ ተቋራጭ ሲሆን፣ ለዚህ ዘርፍ የሚሰጡ GC-1 እና WC-1 የተባሉ የግንባታ ፈቃዶች አሉት፡፡ ድርጅቱ በአመዛኙ የሚታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ በአማካይ በፈጣን የግንባታ ሥርዓት ባካሄዳቸው የመንገድ ሥራዎች ነው፡፡

እስካሁን ያካሄዳቸውን ግንባታዎች በተመለከተ ተቋራጩ በሰጠው ማብራሪያ መሠረት፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲሁም ከአሥር በላይ የመንገድ ሥራ ተቋራጮችን በወቅቱ ገንብቶ አስረክቧል፡፡ ታሪካዊውን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፣ ከተነሳበት የቀድሞ ቦታው በአግባቡ እንደነበር አድርጎና ዙሪያውን አስውቦ የመትከል ሥራ ማከናወኑንም ገልጿል፡፡ በአሁኑ የቂሊንጦ አካባቢ እንዲሁም ኮዬ ፊቼ ላይ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት ማከናወኑ፣ የቤተልና የአካባቢው የፍሳሽ መሥመር ዝርጋታ ፕሮጀክት፣ የመስቀል አደባባይ – ቦሌ ቀለበት መንገድ ፕሮጀክት (ከወሎ ሰፈር አደባባይ በኡራኤል አትላስ አገናኝ መንገድ) በጉርድ ሾላ፣ በመስቀል ፍላወርና በቦሌ የመኖሪያ አፓርትመንት ግንባታዎች ላይ ያከናወናቸው  ተጠቃሽ ሥራዎቹ እንደሆኑ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት የቆቃ አዱላላ ደብረዘይት የመንገድ ፕሮጀክትን ተረክቦ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

አሰር ኮንስትራክሽን በግንባታ ሥራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲሁም በጨረታ ሒደት ወቅት የሚያደርገውን ተሳትፎ የሚገልጸው ጊዜው የሚጠይቀውን፣ የኮንስትራክሽን ገበያው የሚፈልጋቸውንና ሌሎችም ለዘርፉ ወሳኝ ለሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በተጓዳኝ ኩባንያው የተለያዩ የግንባታ ግብዓቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ዘመናዊ ፋብሪካዎችን፣ ሁለት የኮንክሪት ማከማቻ ጣቢያዎችን እንዲሁም ሁለት ጠጠር መፍጪያዎችን ተክሏል፡፡

እያንዳንዳቸው በሰዓት 150 ቶን የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ጠጠር የማምረት አቅም ያላቸው የኮንክሪት ቱቦ ማምረቻም ገንብቷል፡፡ በቀን ከ100 በላይ የተለያዩ ኮንክሪት ቱቦዎችን የማምረት አቅም ያላቸው የአስፓልት ማደባለቂያዎችን፣ በቀን 120 ቶን ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የአስፓልት ሚክስ የሚያመርቱ ተቋሞችን ተክሎ የግንባታ ሥራውን እያካሄደ ይገኛል፡፡ እነኚህ ግዙፍ ማምረቻዎች ግብዓቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ከሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ፍጆታ ባሻገር፣ ለግንባታ ድርጅቶችና ለሥራ ተቋራጮች በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ በጥራት ችግር ምክንያት የሚመጣውን የግንባታ ብልሽት ለመከላከል እየጣረ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy