NEWS

አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያን ሰላም የማስፈንና ስደተኞችን የማስተናገድ ጥረት አደነቁ

By Admin

January 29, 2017

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት በማስፈንና ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ የምታደርገውን ጥረት አደነቁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ምክክር አካሂደዋል።

ዋና ጸሃፊው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላሟ የተጠበቀ ሃገር መሆኗ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች የአህጉሪቱ አካባቢዎች ሠላም ለማስፈን ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።

የሃገሪቱን ሰላም ዋስትና አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን የጎረቤት ሃገራት ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ ረገድም የምታደርገው ሰብዓዊ ተግባር የሚመሰገን መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፥ በቀጠናውም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ከመንግስታቱ ድርጅታ ጋር ኢትዮጵያ በቅርበት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ዋና ጸሃፊውም እነዚህንና ሌሎች ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው ተግባራት የመንግስታቱ ድርጅት ድጋፍ እንደማይለያት አረጋግጠዋል።

በኅብረቱ ጉባዔ አጀንዳዎችና ሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያም በስፋት ምክክር አካሂደዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የክብር ተጋባዥ መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

FBC