Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመቻቻልና የአንድነት ተምሣሌት

0 583

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመቻቻልና የአንድነት ተምሣሌት

ወንድይራድ ኃብተየስ 01-09-17

ኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ነች። ሁሉም የራሳቸው ወግ፣ ታሪክ፣ ኃይማኖትና ቋንቋ ያላቸው ሲሆን ይህ ብዝሃነት ለኢትዮጵያዊያን ልዩ ውበት ነው። በአገሪቱ የሚገኙ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመከባበርና በመቻቻል ለዘመናት ኖረዋል። ኢትዮጵያ የመቻቻልና የአንድነት ተምሣሌት ሆና የምትጠቀስ አገር ካደረጋት አንዱ ይህ ነው። ይህ አብሮነት የኢትዮጵያ መለያ ብሎም የኢትዮጵያዊያን ኩራት ነው። ከዚሁ አቻ የሆነው ሌላው የአብሮነት መገለጫ ደግሞ የኃይማኖት መቻቻል ነው። ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የኃይማኖት ብዝሃነትን ተቀብላ በአግባቡ ስታስተናግድ የኖረች አገር ብትሆንም የታሪክ ማህደራት እንደሚያሳዩት የብዝሃነትና የመቻቻል ባህል በመሸርሸር አብሮ የመኖር ታሪካችን ጥላሸት የሚቀባ ክስተት አልተፈጠረም፤ ተፈጥሮም አያውቅም። በቀደሙት ሥርዓታት አገሪቱን ያስተዳደሩ የነበሩ መሪዎች የኃይማኖት እኩልነትና ነጻነትን አፍነው ምዕመኑን እየከፋፈሉ ሥልጣናቸውን ለማራዘም ተጠቅመውበታል። አንድ አገር፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ኃይማኖት የሚል ፖሊሲን ለማስረጽ ተንቀሳቅሰዋል። በመሆኑም ብዝሃነትን የአንድነት አደጋ አድርጎ በመውሰድ በሕዝቦች መካከል መቃቃርን በመፍጠር ሲከፋፍሉት ኖረዋል። በ1948 ዓ.ም በተሻሻለው የንጉሰ ነገሥቱ ዘመን ህገ መንግሥት አንቀፅ 126 ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት መሠረታዊ ቤተ ክርስቲያን ናት በማለት በግልፅ ደንግጓል፡፡ በዚሁ ህገ መንግሥት አንቀፅ 127 ላይ ደግሞ ህዝብና ካህናት ጳጳሳት ቢመርጡም ንጉሰ ነገሥቱ ምርጫቸውን ካልተቀበሉና ሹመቱን ካልፈቀዱ መንፈሣዊ ሥርዓት መፈፀም እንደማይቻል በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ ሌሎች ኃይማኖቶች በአገሪቱ ለመንቀሳቀስ ምንም ዓይነት ነጻነት ያልነበራቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ኃይማኖት ተብሎ የተመረጠው ሳይቀር አመራሮቹ በንጉሱ ይሁንታ ካላገኙ ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን ሊመሩ አይችሉም ነበር። በዚህ ዘመን ስለኃይማኖት ነጻነት ስናወራ ምናልባትም የቀደሙትን አለመረዳት በራሱ የሚያመጣው ጫና እንዳለ መረዳት አያዳግትም። ከላይ የቀረበው ድንጋጌ እንደሚያመለክተው የንጉሱ ኃይማኖት የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ነው የሚል ድንጋጌ እስካለ ድረስ መንግሥትና ኃይማኖት አንድና አንድ ነበሩ ለማለት ይቻላል። አንዱ የሌላኛው ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንጂ የተለያዩና አንዱ በአንዱ ተግባር ጣልቃ የማይገባበት ሁኔታ አልነበረም። ያ ዘመን የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነፃነት በሕገ መንግሥት የተገደበበት ዘመን ስለነበር የኃይማኖት ብዙሃነት የማይታሰብ ነበር። የይስሙላ የኃይማኖት ነፃነት የተከበረባት አገር ለማስመሰል ከወረቀት የዘለለ ትርጉም ያልተሰጠው ህገ መንግሥት ያፀደቀው አምባገነኑ የደርግ ሥርዓትም ቢሆን በመሠረቱ ከንጉሱ ዘመን የተለየ ነገር መሥራት የሚያስችል ፖሊሲና ህዝባዊ አስተሳሰብ አልነበረውም። አምባገነኑ የደርግ መንግሥት በኃይማኖት ላይ ይከተለው የነበረው አግባብ ኃይማኖትን የሚያጠፋና ሁሉም ዜጋ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ነበር፡፡ የአፈናና የጭቆና ሥርዓቱን ለማራዘም ሲል ኃይማኖት ፀረ አብዮት፣ ፀረ ልማትና ጎታች የሆነ የአድኃሪዎች ተምሣሌት አድርጎ በመሳል በግልፅ ፀረ ኃይማኖት አቋሙን ያንፀባርቅ ነበር፡፡ ኃይማኖት የአድኃሪዎች መሣሪያ፣ ጎታችና የፀረ አብዮት መሣሪያ አድርጎ በመፈረጅ የኃይማኖት ተቋማትን በማዳከም የእምነት ተቋማት ጭምር የተዘጉበት፣ ተከታዮቻቸው ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉበት አስከፊ ሥርዓት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ካለፉት ሥርዓታት በእጅጉ የተለየ ነበር። ያለፉትን ሥርዓቶች ስንመለከት የኃይማኖት ብዝሃነት የየሥርዓቱ አደጋ ተደርጎ ነበር የሚወሰደው። በመሆኑም ከፋፍለህ የመግዛት አቅጣጫ መጠቀም አንዱ መሠረታዊ ነገር ነበር። ይህንን እኩይ መርህ አንድን ኃይማኖት የበላይ ሌላውን የበታች በማድረግ፤ መንግሥት የኃይማኖት አስተዳዳሪ አሊያም አደናቃፊ የሆነበት ሥርዓት ነግሶ እንደነበርም ይታወቃል። መንግሥት በኃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባበት የመንግሥትና የኃይማኖት መለያየት የሚባል ነገር ፍፁም የሌለበት ዜጎች የሚፈልጉትን ኃይማኖት በነፃነት ማራመድ የማይችሉበት ሥርዓት እንደነበረ ከማንም የተደበቀ አይደለም። ዜጎች ያለፈቃዳቸው የገዥዎችን ኃይማኖት እንዲቀበሉ በማስገደድ አንድ ኃይማኖት አንድ ህዝብ የሚል መርህ ተገደው እንዲቀበሉ በማድረግ በአገሪቱ የእምነት ነፃነት የማይታሰብ እንደነበር የታሪክ ማህደራት ያሳያሉ። የኃይማኖትና የብሔሮች ብዝሃነትን የማጥፋትና የህዝቦችን መብቶች በኃይልና በአስገዳጅ ፖሊሲዎች የመጨፍለቅ አካሄድ ህዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ አድርጓል፡፡ ተነግሮ የማያልቅ ክቡር መስዋዕትነት በመክፈልም ለብዝሃነትና ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር አደጋ የሆነው ሥርዓት ላይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሥር መሠረቱ ነቅሎ ለመጣል በተደረገው ትግል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጎላ ሚና ነበራቸው። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት በግልጽ እንደሰፈረው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የኃይማኖት ነፃነት ተረጋግጧል። መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ሆነዋል። መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን ያስቀምጥ እንጂ ህዝቦች የፈለጉትን ዓይነት እምነት መከተል እንደሚችሉ መብታቸውን አልገደበም ብቻ ሳይሆን በዚህ ረገድ ኃይማኖታዊ ተልዕኮ ጋር ተያይዞ ልቅ ተለቋል ማለት ይቻላል። የነበረውን ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዝ በመገዝገዝና ከሥር መሠረቱ በመጣል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተገነባ ይገኛል። አብሮነትንና መቻቻልን መሠረት ያደረገ ብዝሃነት ውበት፣ ጥንካሬና አንድነት እንጂ የሥርዓቱ ሥጋት አለመሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ሥርዓት ዛሬ በኢትዮጵያ ተፈጥሯል። ለዚህ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ዋናው ምክንያት ደግሞ የኢሕአዴግ ህዝባዊነት ነው። ገና ከጅምሩ መላውን የአገራችንን ህዝቦች ያለ ምንም ልዩነት እኩል መሆናቸውን ነበር የተቀበለው። ዜጎች በብሄር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በዘር፣ በቀለም እንዲሁም በኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው በአገራቸው ላይ እኩል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሥርዓት በመዘርጋት ሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ያጠናክራሉ በሚል ነበር እምነት በአዲስ አስተሳሰብ ጉዞውን የጀመረው። ኢሕአዴግ የሕዝቦችን እኩልነት፣ መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ ታግሎ ያተገለ ህዝባዊ ድርጅት በመሆኑ ለእኩልነትና ለብዝሃነት የተሰለፈ ድርጅት እንደሆነም በትጥቅ ትግል ወቅት ያሳየውን ብቃት በልማትና በሠላም በቀጣይነት ማስመስከር ችሏል፡፡ በዚህ መልክ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ህገ መንግሥት በማስፀደቅ በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል። በህገ መንግሥቱ ማንኛውም ሰው ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በህግ ፊት እኩል መሆኑ እንዲረጋገጥ ተደርጓል። ማንኛውም ዜጋ ያለልዩነት እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት በግልፅ ተቀምጧል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የኃይማኖት እኩልነትና ነጻነቱ ተከብሯል። በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 11፣ አንቀፅ 25 እና አንቀፅ 27 ላይ የሁሉም ኃይማኖቶች እኩልነት ተደንግጓል። በኢትዮጵያ የበላይና የበታች የሚባል ኃይማኖት እንደሌለም ተሰምሮበታል። ኃይማኖት በመንግሥት መንግሥትም በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡም በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ከመቼውም በበለጠና በላቀ መንገድ እንዲያውም በአገሪቱ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የኃይማኖት ተቋማት ተስፋፍተዋል። ዜጎችም የአምልዕኮ ሥርዓቶቻቸውንና አስተምህሮዎቻቸውን ያለምንም ተጽዕኖ በነጻነት ማከናወን ችለዋል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ይኼ ነው። የመቻቻልና የአንድነት ተምሣሌት አገር – ኢትዮጵያ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy