የቤተ-ጎለጎታና ቤተ-ሚካኤል ቤተ መቅደሶች ሊታደሱ ነው
የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ እንደገለፁት ሁለቱ ቤተመቅደሶች በረጅም እድሜ አገልግሎት በደረሰባቸው መሰነጣጠቅ ምክንያት ጥገና አስፈልጓቸዋል።
ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት ከወርልድ ሞኑመንት ፈንድ በተገኘ 16 ሚሊየን ብር ለቤተ-ገብርኤልና ቤተ-ሩፋኤል ቤተ-መቅደሶች ጥገና አድርጓል።
አሁን ደግሞ የቤተ-ጎለጎታና ቤተ-ሚካኤል ቤተመቅደሶችን ጥገና ለማከናወን ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ 500 ሺህ ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ተናግረዋል።
በመጪው የካቲት ወር አጋማሽ የሚጀምረው የጥገና ስራ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችና የጥገና ክህሎት በመጠቀም እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት።
ጥገናውን በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደታሰበም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ጥገናው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ መርሆዎችን በመከተል እንደሚከናወን የተናገሩት አቶ ኃይሉ፥ በዚህም መሰረት ቅርሶቹ ነባራዊ ሁኔታቸውን ሳይለውጡ ይታደሳሉ ብለዋል።
አብዛኛው የጥገና ስራም በአገር ውስጥ ባለሙያ ከመሰራቱ ባለፈ ከወርልድ ሞኑመንት ቴክኖሎጂ የሚመጣ ባለሙያ አቅጣጫ የመስጠት ስራውን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ በቀጣይ ሳምንት ጨረታ አውጥቶ ያሸነፈውን ተቋራጭ በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዓለም ቅርስነት የሰፈሩት የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩና ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሠሩ 11 ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ናቸው።
ምንጭ፦ ኢዜአ