Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

0 838

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር የቀብር ሥነ-ሥርዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጸመ።

በአትሌቱ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተወካዮቻቸው በህልፈቱ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

ሻምበል ምሩጽ በአትሌቲክስ ስፖርት ለአገሩ ያበረከተው አስዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

ለአትሌቱ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር በእግዚያብሔር አለበልና የአትሌቱ ቤተሰቦችና ወዳጆች ተገኝተዋል።

የአትሌቱ አስክሬን ዛሬ ጠዋት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የአትሌቱ ቤተሰቦችና ታዋቂ አትሌቶች የክብር አቀባበል አድርገውለታል።
የአትሌቱ አስከሬን በማርሽ ባንድና በክብር ዘብ ታጅቦ ቦሌ መድኃኔዓለም ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ወደ ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ደርሷል።

ብሔራዊ ጀግና ለሆነው አትሌት ምሩጽ የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የሚገባውን ክብር በጠበቀ መልኩ ተፈጽሟል፡፡

አትሌት ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር በ25 ዓመቱ ለአትሌቲክስ ያለው ልዩ ፍቅር ተሳክቶለት በ1961 ዓ.ም በአየር ሀይል አትሌቲክስ ክለብ ተቀጥሮ መስራት ችሏል ።

በክለቡ በተዘጋጁ የውስጥ ውድድሮች በቀዳሚነት በማጠናቀቅ አገሩን ወክሎ በተለያዩ የዓለምና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላቅ ያለ ውጤት አስመዝግቧል።

በተለይ አትሌት ምሩፅ በ 1972 ዓ.ም የሞስኮ ኦሊምፒክ በአምስትና በ 10 ሺህ ሜትር ሩጫ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በታሪክ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አትሌት ሆኗል።

በአንድ ኦሊምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ምሩጽ በአጨራረስ ብቃቱ ”ማርሽ ቀያሪው” አትሌት የሚል ስም ተሰጥቶታል።

በ 1964 ዓ.ም የሙኒክ ኦሊምፒክ በ 10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ በአትሌቲክስ አገሩን ወክሎ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ካስመዘገባቸው ጣፋጭ ድሎች መካከል ተጠቃሽ ነው።

አትሌት ምሩፅ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካደረጋቸው ከ 410 በላይ ውድድሮች 271 ጊዜ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ብቃቱን ያስመሰከረ ጀግና አትሌት ነበር።

ምሩፅ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበርም የወርቅ ጫማ ሽልማት የተበረከተለት ታላቅ አትሌት በዓለም አቀፍ ውድድሮችም ስምንት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችሏል።

አትሌት ምሩጽ ይፍጠር ባደረበት ህመም ምክንያት በካናዳ ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ታኅሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በ 72 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በትግራይ ክልል አዲግራት በ1936 ዓ.ም የተወለደው አትሌቱ ባለትዳርና የስምንት ልጆች አባት ነበር።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy