NEWS

የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን ለታዳሽ ሃይል ልማት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

By Admin

January 29, 2017

የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን ለሃይል ልማት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል ኢኒሼቲቭ የመጀመሪያው የቦርድ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ቻድ፣ ናምቢያና ጊኒ የቦርዱ አባል አገራት ሲሆኑ ቦርዱን ደግሞ የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ በሊቀ-መንበርነት ሲመሩት የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ አስተባባሪ ናቸው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢኒሼቲቩን በገንዘብ የሚረዳው ሲሆን ጀርመንና ፈረንሳይም ድጋፍ ያደርጋሉ።

በቦርዱ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ያለ በቂ ታዳሽ ሃይል አፍሪካን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ማሸጋገር የማይታሰብ ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳይ በዘላቂ ልማት ግብና በአጀንዳ 2063 ማዕቀፍ በተቀመጠው መሰረት አፍሪካውያን ታዳሽ የኃይል አማራጮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቩ በትክክለኛው ጊዜ ላይ መጀመሩን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የተነደፈውን ዕቅድ በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በኢኒሼቲቩ ዕቅድ በተካተቱት ጉዳዮች እንደምትስማማና ለተግባራዊነቱም በሙሉ አቅሟ እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠዋል።

የአፍሪካን ህዝቦች ህይወት ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር አባል ሃገራት ለፕሮጀክቱ ተግባሪዊነት መረባረብ ይኖርባቸዋል ያሉት ደግሞ የኢኒሼትቩ ሊቀመንበርና የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ናቸው።

ህዝቦች ሰርተው ህይወታቸውን ለመለወጥ የኃይል ምንጭ ያስፈልጋቸዋል፤ የማገኘትም መብት አላቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህን ለማድረግ ደግሞ የዚህ ዓይነቱ ፕሮጀክት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በመድረኩ ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ምዕራፍ የሚያሳይ ሪፖርት ቀርቦ በቦርዱና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል።

FBC