የደጋው ክፍል ኤርትራውያን አብዛኞቹ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ የጊዜ አቆጣጠራቸውም እንደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት በኤርትራ ደገኛ ትግረኛ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍልም ይከበራሉ፡፡

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መሪ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስን ለእስር የዳረገው የኤርትራ መንግሥት ግን አቆጣጠሩም ሆነ አገራዊ በዓላት አከባበሩ ከአውሮፓውያን ጋር የሚገጣጠም ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የዘንድሮ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የዓለም መሪዎች በዓለም አቀፍ መድረክ የተበየነላቸውን መሬት ከኢትዮጵያ ለመረከብ እንዲተባበሩዋቸው ጠይቀዋል፡፡

ትኩሳት ማብረድ እስከ መቼ?

በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለማደናቀፍ ታስቦ የመከነው ‹‹አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ›› የሚለው የአስመራ ኦፕሬሽን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቋም ለውጥ እንድያደርግ አስገድዶ ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅቱ በፓርላማ ቀርበው፣ ‹‹እስከ ዛሬ የኤርትራ መንግሥት ተላላኪዎችን እየተከታተሉ ማምከን የሚለውን ፖሊሲ ስንከተል ቆይተናል፡፡ ሆኖም የፀረ ሰላም ኃይሎችን ብቻ እየተከታተሉ መያዝና ማምከን የመሰለ የመከላከል ፖሊሲ ከዚህ በላይ ሊቀጥል አይችልም፤›› ብለው ነበር፡፡

‹‹……በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ዕለታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን መርካቶ  ገበያን ሁሌም መጠበቅ አንችልም፡፡ አማራጩ የኤርትራ መንግሥት ባህሪው እንዲቀይር አልያም ከሥልጣን እንዲወርድ የኤርትራን ሕዝብ መደገፍ ይሆናል፤›› በማለት ኢትዮጵያ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ፖሊሲ መሸጋገሯን ተናግረው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዓመት ከተከሰተው ተቃውሞና አመፅ ጀርባ፣ የኤርትራ መንግሥት እጅ እንዳለበት ገልጿል፡፡ ዘግይቶ በነፃ ቢለቀቁም በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ከትግራይ ክልል አፍኖ መውሰዱም ይታወሳል፡፡

በቅርቡም ከ100 በላይ በኢትዮጵያ መንግሥት በሽብር የተፈረጀው የግንቦት ሰባት የሽብር ቡድን አባላት በምዕራብ ትግራይ ለማስገባት የኤርትራ መንግሥት ሞክሮ እንደነበርም ተዘግቧል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ አቶ ዮሐንስ ገበየሁ የተባሉ ጸሐፊ፣ ‹‹የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከል ኢትዮጵያውያንና ቀጣናውን ማተራመስ እንደሆነ ማሳያ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የኤርትራ መንግሥት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የየመንን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት በሚል ሰበብ ለተሰባሰቡትና ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ አላቸው የሚባሉ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቅንጅት አባል በመሆን እያገለገለም ይገኛል፡፡ ለሳውዲ  ዓረቢያ፣ ለግብፅና ለተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ የባህር የጦር ሠፈር መፍቀዱ  እየተነገረ ነው፡፡

አንድሪው ኮሪብኮ የተባሉ ሩሲያዊው የፖለቲካ ተንታኝ በየመን አካባቢ ያለው መሰባሰብ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በቀይ ባህር አካባቢ ያላትን የበላይነት ለማቀጨጭና ለማዳከም ያለመ ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት፣ በኤርትራ ያለው የጦር ሠፈር ኢትዮጵያን ለማዳከምና የየመን አማፅያን ለመዋጋት በሁለቱም ወገን የተሳለ ጎራዴ ነው፡፡

‹‹የኳታር በኤርትራ መንቀሳቀስ ሆን ተብሎ የተቀነባበረና በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ አመፅ በመቀስቀስ፣ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ደሴት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያቀደ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች  የቀድሞ ዳይሬክተር ሃንክ ኮሃን፣ በአንድ የቆየ ጽሑፋቸውና የእሱ ቀጣይ በሆነውና ባለፈው ዓመት በጻፉት “The Red Sea is Slipping into Total Arab Control” በሚለው አጭር ጽሑፋቸው፣ ‹‹አቢሲንያውያን እርስ በርሳችሁ ስትናቆሩ የባህረ ሰላጤው መንግሥታት ምሳችሁን እየበሉት ነው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በእርግጥ የእሳቸው ምክር ባድመን ያለ ቅድመ ሁኔታ ለኤርትራ በመስጠት ግንኙነቱ ወደነበረበት መመለስና ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የሚል ነው፡፡ ይሁንና ከሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያገኘ ሐሳብ አይመስልም፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን፣ መንግሥታቸው ቀድሞ የሚከተለው ‹‹የተመጣጣኝ ዕርምጃ›› ፖሊሲ ውጤታማ እንደሆነና ይህንን ፖሊሲ ለመቀየር ሐሳብ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ ግርማ፣ በኤርትራና በቀይ ባህር አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን የመከላከል ፖሊሲ ለመቀየር በቂ ምክንያት መሆኑን ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የአስመራን መንግሥት ከሥልጣን ማውረድ ለኢትዮጵያ ቀላል ሥራ ቢሆንም፣ የአካባቢውን ሰላም ሊያናጋ ስለሚችል አደጋ እንዳለው ይሠጋሉ፡፡ ‹‹በሌላ በኩል የአገሮች ሉዓላዊነት ላይ የማይናወጥ አቋም ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ላይ ጣልቃ በመግባት ከመርህ መውጣት አይፈልግ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ›› የሚለው ፖሊሲ እንደሁኔታው ሊተረጎም የሚችልና የኤርትራ መንግሥትም ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ሥጋት የሚሆንበት ምክንያት እንደማይኖርም ያምናሉ፡፡

‹‹ተመድ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ የኤርትራ መንግሥትን ባህሪ አልቀየረውም፤›› የሚሉት የደኅንነት ተመራማሪው፣ ‹‹የተመጣጣኝ ዕርምጃ ፖሊሲ ብቻውን መከተል ግን ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ትኩሳት እያበረዱ መኖር አይቻልም፤›› ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት ያገባናል የሚሉ አካላትን በሙሉ በማስተባበር አንድ ተጨማሪ ጠንከር ያለ ስትራቴጂ እንዲቀረፅ ያሳስባሉ፡፡

አቶ ኃይሌ ተሰማ የተባሉ ሌላ ጸሐፊ በበኩላቸው የሩሲያንና የዩክሬን ታሪክ በምሳሌነት በመውሰድ፣ በተለይ የመን አካባቢ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ ሥጋት መሆኑን በማመን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አስመራ ያለውን መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ጭምር እንዲያስወግድ ይመክራሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት ባህሪ

ከዓደዋ ጦርነት ማግሥት ጀምሮ የጣሊያን ቅኝ ግዛት የነበረው፣ ቀጥሎም ለአሥር ዓመታት በእንግሊዝ ሥር የነበረው ይኼው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ምድር፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ የዲፕሎማሲ ጥረት ወደ ነባር አገሩ ተመልሶ የነበረ ቢሆንም፣ የ30 ዓመታት ደም አፍሳሽ ጦርነት አስከትሏል፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የተንገሸገሸው የኤርትራ ሕዝብ ከአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም ለመገንጠል ታግሏል፡፡ ትግሉም ተሳክቶለት ይኼው ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ለብቻው መኖር ከጀመረ 25 ዓመታት አልፈዋል፡፡

ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ውጪ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የኤርትራን መገንጠል የሚቃወም ነው፡፡ በተለይ ከኢኮኖሚም ሆነ ከደኅንነት አንፃር ከፍተኛ ትርጉም ያለውን የባህር በር ወደብ (አሰብ) ኢትዮጵያ እንድታጣ መደረጉን ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ተቃውሞ ያዳመጠበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ለአገር አንድነት አደጋ ተብሎ የተሠጋው የፌደራሊዝም ሥርዓትና ኤርትራ እንድትገነጠል የተወሰደው ዕርምጃ፣ የበርካታ ኢትጵያውያን ተቃውሞ የቀረበበት የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት፣ ከቀድሞ ወዳጁ ከአስመራ መንግሥት ተመሳሳይ ምላሽ አላገኘም፡፡

የኢትዮጵያን መገበያያ ብር በናቅፋ መተካቱን ያወጀው የኤርትራ መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የማይጣጣም የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል መጀመሩ ለግጭቱ መነሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከድንበር መዋሰን ጋር በተያያዘ የተነሳው አለመግባባት የባድመ ባለቤትነት ጥያቄን አምጥቷል፡፡

በአቶ ኢሳያስ የሚመራው አስመራ ላይ የከተመው መንግሥት  ድንበርን አመካኝቶ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ከፈጠረ ቀን ጀምሮ፣ ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር ማለት ይቻላል ጦርነት ውስጥ ገብቷል፡፡ አገሪቱን ያለ ሕገ መንግሥት እያስተዳደራት ይገኛል፡፡  የዴሞክራሲና የሥርዓት አካሄድ ጥያቄ ያቀረቡ የገዥው ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም ጋዜጠኞች የገቡበት አይታወቅም፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ሳቢያ ግጭት ካስነሳ በኋላ የኤርትራ መንግሥት ወደ ለየለት ጨቋኝነት የተለወጠ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

የድንበር ኮሚሽኑ ፍርድ ገምድል ፍርድ መስጠቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ያምናል፡፡ ከዚህ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ከ16 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የትንኮሳ፣ የማተራመስና ዜጎችን አፍኖ የመውሰድ ድርጊቶች ሲፈጽም ተስተውሏል፡፡ በጦርነቱ ወቅት በእጁ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል ጀምሮ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለውን ነፃ የጉልበት ሥራ እንደሚያሠራቸው ተደጋግሞ ተጽፏል፡፡

በሶማሊያ ተጠናክሮ የነበረውና በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ ያወጀው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትንና የእሱ ውልድ የሆነውን አልሸባብን ከጀርባ መደገፉን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ነፍጥ ያነሱ ድርጅቶችን በማስጠለል ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የሽብር ድርጊቶች ማስፈጸሙ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ በኦጋዴን በነዳጅ ፍለጋ ላይ የነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣውን ጥቃት ጨምሮ፣ በርካቶችን ከአፋርና ከትግራይ ክልሎች እያፈነ በመውሰድ የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣሉ በስፋት መነገሩ አይዘነጋም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናውን ለማተራመስ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)ና የአሜሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜያት አረጋግጠዋል፡፡
ተመድ በኤርትራ መንግሥት ላይ ሁለት ጊዜ ማዕቀብ የጣለበት ቢሆንም፣ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ግን አልቻለም፡፡ በቅርቡም በተጣሉበት ማዕቀቦች ላይ የማራዘም ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ መንግሥት ላይ ከተወሰዱ ዓለም አቀፍ  ማዕቀቦችና ሌሎች ዕርምጃዎች ጀርባ እጁ እንዳለ ባይጠራጠርም፣ ተጨማሪ አጥጋቢ ዕርምጃ ሲወስድ አይስተዋልም ተብሎ ይተቻል፡፡  የድንበር ጦርነቱን ተከተሎ በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ ለተፈጠረው መሰነጣጠቅ የኤርትራ ጉዳይ አንዱ ምክንያት ነበረ፡፡ በኤርትራ ላይ የተለየ አስተሳሰብ የነበራቸው የድርጅቱ አመራሮች እንዲወገዱ መደረጉም ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ኤርትራ ለምትፈጥራቸው ችግሮች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙዎቹ ተቃውሞ የሚያቀርቡበትን ‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ›› የመውሰድ ፖሊሲ እንደሚከተል ሲገልጽ ይሰማል፡፡ በኦጋዴን ከደረሰው ጥቃት በኋላ አቶ መለስ ኤርትራን ሲያስጠነቅቁ ወደ ጦርነት እንደማይገባ፣ ከተገባ ደግሞ እስከ መጨረሻ አስመራ ድረስ በመሄድ የሥርዓት ለውጥ ማድረግን ይጨምራል ብለው ነበር፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ የማተራመስና የሽብር ተግባራት ያቀነባበረ መሆኑ እየታወቀና የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የኤርትራ መንግሥት መሆኑ እየታመነ፣  የኢትዮጵያ መንግሥት ከቃላት ድንፋታ በዘለለ በአስመራ መንግሥት ላይ ባለመጨከኑ የሚተቹት በርካቶች ናቸው፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የኤርትራ መሪዎች በሰው ዘር ላይ በፈጸሙት ወንጀል ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሪፖርት ማቅረቡም ይታወሳል፡፡ ይኼም ቢሆን በኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ መንግሥት ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ ይወሰድበታል መባሉ አልቆመም፡፡ የኤርትራ መንግሥት በባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች የሚመራው በየመን ላይ የዘመተው የጦር ኅብረት አባል በመሆን የአሰብ ወደብን ለዚሁ ዓላማ በገንዘብ አከራይቷል፡፡ ከዚህ የሚያገኘውን ገቢ እንደተለመደው በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ለመቀስቀስ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡