Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግብርና ሲዘምን በበጋም ምርት አለ!

0 1,952

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግብርና ሲዘምን በበጋም ምርት አለ!

ኢብሳ ነመራ 12-23-16

ኢትዮጵያ ባለፈው 2ዐዐ8 ዓ.ም 8 በመቶ አጠቃላይ የእድገት ምጣኔ አስመዝግባለች። ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም በነበረው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዘመን በየዓመቱ በአማካይ 10 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚው እድገት መመዝገቡ ይታወሳል። የባለፈው ዓመት እድገት ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ብሏል። ይሁን እንጂ፤ ከ7 በመቶ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅና ፈጣን እድገት ነው። የባለፈው ዓመት 8 በመቶ እድገት ከአጠቃላይ 5 በመቶ አማካይ የአፍሪካ እደገት አኳያም ሲታይ ትልቅ እድገት ነው። ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ለለመዱ ኢትዮጵያውያን ግን አነስ ብሎ ታይቷል። የባለፈው ዓመት የኢኮኖሚ እድገት ዝቅ ሊል የቻለው ኤልኒኖ ያስከተለው ድርቅ በግብርና ምርት ላይ ባሳረፈው ተጽአኖ ነው። ድርቁ በአገሪቱ የመኸር ግብርና ምርት ላይ የ1 ነጥብ 3 በመቶ ቅናሽ እንዲኖር አድርጓል። ከድርቁ በተጨማሪ የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና የሸቀጦች ዋጋ መውረድም ለእድገቱ መቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታውቋል። የተመዘገበው እድገት ከተያዘው እቅድ አኳያ ቅናሽ ቢያሳይም አገሪቱ ገጥሟት ከነበረው ችግር አንፃር ሲታይ ግን መልካም ሊባል የሚችል መሆኑንም ኮሚሽኑ አመልክቷል። አገሪቱ በ2007 ዓ.ም በግማሽ ክፍለ ዘመን ውስጥ ከገጠማት ሁሉ የከፋ ድርቅ አጋጥሟትም የኢኮኖሚ እድገቱ በጉልህ ያላዘቀዘቀው ወይም ከፈጣን እድገት ውጭ ያልሆነችው ከዚያ ቀደም ከአስር ዓመታት በላይ ባስመዘገበችው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት ምክንያት ነው። የባለፉት ዓመታት ተከታታይ፤ ፈጣን ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፉንም ድርሻ ስላጎላው በአየር መዛባት ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በመቋቋም እድገት እንዲመዘገብ ማድረግ አስችሏል። በ2008 በጀት ዓመት ግብርና በ2 ነጥብ 3 በመቶ፤ ኢንዱስትሪ በ20 ነጥብ 6 በመቶ፤ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ በ8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ማሳየቱን ከብሄራዊ ፕላን 2 ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የግብርና ዘርፍ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 44 ነጥብ 4 በመቶ በ2008 በጀት ዓመት ወደ 36 ነጥብ 4 ዝቅ ብሏል። በሌላ በኩል፤ በተመሳሳይ ጊዜ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ከ10 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 16 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል። የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ከነበረበት 45 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 47 በመቶ ከፍ ብሏል። የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ይህ መረጃ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ከመመዝገቡ በተጨማሪ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ወይም ሽግግር የማምጣቱ እቅድ የስኬት አቅጣጫ መያዙን ያመለክታል። ለባለፈው ዓመት የኢኮኖሚ እድገት መቀነስ ምክንያት የነበረው የግብርናው ዘርፍ፤ ዘንድሮ በከፍተኛ መጠን እድገት አሳይቷል። በዘንድሮ የመኸር ወቅት በአጠቃላይ 320 ሚሊዮን ኩንታል ያህል የሰብል ምርት ይሰበሳባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቋል። ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ50 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው። ሚኒስቴሩ እንዳስለው፤ በ2008/09 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ተሸፍኗል። ከዚህ በሰብል ከተሸፈነ መሬት 320 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚሰበሰብ ተገምቷል። በዘንድሮ የመኸር ወቅት አምና በኢልኒኖ ምክንያት የተከሰተውን የምርት ጉድለት ለማካካስ፤ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውሷል። በመኸር ወቅት በአገሪቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ለግብርና ተስማሚ የሆነ የዝናብ ሥርጭት ነበር። የመኸር እርሻ ቅድመ ዝግጅቶችና ለአርሶ አደሩ የተሠጡት ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች፤ እንዲሁም የተደረገው ክትትል ለምርቱ መጠን ከፍ ማለት አስተዋጽኦ ማበርከቱን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ገልጿል። በመኸር እርሻ በአገሪቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ከ275 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ቀርቦ እንደነበረ፤ የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸውንም አመልክቷል። እንደሚኒስቴሩ ገለጻ፤ በምርት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮችንና የዋግ በሽታን ለመከላከል 264 ሺህ 599 ሊትር የፀረ ዋግ መድሃኒት በማሠራጨት የተጠናከረ በሽታ የመከላከል እርምጃ ተወስዷል። 3 እስከተህሳስ ወር ሁለተኛ ሳምንት ድረስ ባለው መረጃ መሰረት በመላ አገሪቱ በመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው 13 ሚሊዮን 349 ሺህ 715 ሄክታር መሬት ውስጥ በ7 ሚሊዮን 699 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው የሰብል ምርት ተሰብስቧል። ይህም በሰብል ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ 60 በመቶ ያህል የሚሆን ነው። እስከ ጥር ማብቂያ ደግሞ ምርቱ ተሰብስቦ ሊያልቅ ይችላል ተብሎ ይገመታል። እነዚህ ሁኔታዎች የዘንድሮ የኢኮኖሚ እድገት በእቅድ የተያዘውን ከ11 በመቶ በላይ ማሳካት እንደሚቻል ከወዲሁ ያመላክታሉ። አጠቃላይ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እንዲዋዠቅ የማድረግ አቅም ያለውና በተለይ ድርቅና የሰብል በሽታ ሲከሰት ብዙዎችን የእለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን በሚዳርግ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ግብርና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የመጀመሪያው ትኩረትም ከዝናብ ጥገኝነት እንዲላቀቅ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ በያዝነው ዓመት 108 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአነስተኛ መስኖ ልማት ስራ በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በትግራይ፤ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ተጀምሯል። በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሰራው የመስኖ ስራ በዘጠኝ ዞኖች በሚገኙ 40 ወረዳዎች ውስጥ ከ8 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታውቋል። በአማራ ክልልም ይሄው ተግባር በስፋት መከናወኑን የክልሉ ተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በየአካባቢ ያሉትን ወራጅ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አማራጮች በመጥለፍና በየአባወራዎቹ ይዞታ እንዲደርስ በማድረግ፤ ውሃን በማቅረብ አርሶ አደሮቹ የጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን እንዲያለሙ መደረጉን ነው ማስተባበሪያው ያስታወቀው፤ በዚህም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ3 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክቷል። በትግራይ ክልልም 22 ወንዞችን በማስቀየስ ከ4 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ የመስኖ አውታሮች ተገንብተዋል። ከ13 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ከክልሉ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፤ ይህ የእስካሁን የመስኖ ልማት ክንውን እንደ 4 ጅምር ጥሩ ቢሆንም፤ በአጠቃላይ በግብርና ከሚኖረው ከ70 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ አኳያና አገሪቱ ካላት የውሃ ሃብት አንጻር ሲታይ እጅግ ትንሽ ነው። የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ እስካሁን በቤተሰብ ደረጃ ማረጋገጥ ያልተቻለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋጋጥ፤ አገሪቱ ትኩረት ለሰጠችው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ በቂና ጥራት ያለው ግብአት ለማግኘት፤ እንዲሁም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ማድረግ የሚያስችል አገራዊ የካፒታል ክምችት ለመፍጠር ትኩረት ሊደረገበት የሚያሻው ሌላው ጉዳይ የእርሻና የሰብል ስብሰባ ሜካናይዜሽን የማስፋፋት ጉዳይ ነው። በሰብል ስብሰባ ወቅት የሚያጋጥመው እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የምርት ብክነት መፍትሄ ይፈልጋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአገሪቱ የማረሻ ትራክተር ስርጭት 2 ነጥብ 4 ትራክተር በ100 ኪሎ ሜትር ካሬ ነው። በቀጣይ ዓመታት ይህን ሁኔታ በማሻሻል 50 በመቶ የአገሪቱ እርሻ በትራክተር እንዲከናወን ታቅዷል። በኮምባይነር የሚታጨደውንም ምርት 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል። በዚህም የምርት ብክነቱን አሁን ካለበት 30 በመቶ ወደ 5 በመቶ የመቀነስ እቅድም ተይዟል። በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚያጋጥመው ብክነት ዋና ምክንያት ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ሜካናይዜሽን ካለመጠቀም ጋር የተገናኘ ነው። የመስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን ከተስፋፋ በቀጣይ ዓመታት እስካሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት መሆኑን ያልለቀቀውን የግብርና ዘርፍ ማሳደግ ይቻላል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት የግብርናው ዘርፍ የመሪነት ስፍራውን ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እየለቀቀ የሚሄድ ቢሆንም፤ ዘርፉ ግን የማያቋርጥ እድገት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል። የመዋቅር ሽግግር ማምጣት ግብርና እና ኢንዱስትሪ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ በንጽጽር ያላቸውን ድርሻ የማበላለጥ ጉዳይ እንጂ፤ አንዱን ችላ የማለት ጉዳይ አይደለም። በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት በድርቅ ምክንያት የግብርናው ዘርፍ እድገት ማሽቆልቆል በኢኮኖሚው እድገት ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ዘንድሮ አይኖርም። የግብርናው ዘርፍ በድርቅና መሰል ተፈጥሯዊ ቀውሶች የሚያጋጥመውን የምርት መቀነስና የምርቱ መቀነስ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተዕእኖ ለማስቀረት፤ እንዲሁም አገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር እንዲያስችል ዘረፉን ለማዘመን የተሰጠው ትኩረት 5 ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። አርሶ አደሩ ግብርናን በክረምት ብቻ የሚሰራው ስራ ሳይሆን በመስኖና በቴክኖሎጂ እየታገዘ ሁሌም የሚሰራው የሙሉ ጊዜ ስራው ማድረግ አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy