የኢህአዴግ ጉባኤ አሠራር ይስተካከል – ታዋቂ ሰዎች ተናግረዋል
ዜና ሐተታ አጎናፍር ገዛኽኝ 01-11-17
የህወሓት እና ኢህአዴግ መስራች አቶ ስብሐት ነጋ የኢህአዴግ ጉባዔ አሠራሩን መፈተሽና ማስተካከል እንዳለበት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ሠፋ ያለ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ይሄንን የአቶ ስብሐትን አስተያየት ተከትሎም አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ታዋቂ ግለሰቦች ሃሳቡን በመደገፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሚሰነዝራቸው ሃሳቦችና በማህበራዊ ሂሱ የሚታወቀው ዲያቆን ዳንዔል ክብረት እንዳለውም፤ ኢህአዴግ ቀድሞ ከነበረበት አንጻር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚታይበት ድርጅት አልሆነም። ይህ የፓርቲው ውስጠ ዴሞክራሲ መዳከም በአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ላይም የራሱን ጥላ እያጠላ ነው። «በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል የሚደረገው ግምገማ ክልሎችን መንካት አድርጎ የመቁጠር አመለካከት አለ። ይሄ ደግሞ ብሔራዊ ድርጅቶቹ እርስ በእርስ የችግራቸውን ሰንኮፍ አውጥተው በመገማገም ያለምህረት እንዲተራረሙና እንዲቀረጹ አላደረጋቸውም። ይልቁንም ተሸካክመው እንዲጓዙ አድርጓል» ነው ያለው ዲያቆን ዳንኤል። እንደ ዲያቆን ዳንዔል አስተያየትም፤ የኢህአዴግ ጉባዔ ከበዓልነት ማለፍ አለበት። ምርትና ግርዱ የሚለይበትና በየዘመኑ የሃሳብ ልዕልና የሚመጣበት መሆን ይገባዋል። በጉባዔው ላይም የተወሰኑ ሰዎች የሚደመጡበት ሳይሆን፤ ሁሉም እኩል ቁጭ ብለው የሚከራከሩበት ከሆነ የተሻለ ሃሳብ ያለውን መለየት ይቻላል። አሁን ካለው አታካች አካሄድ መውጣት ያስፈልጋል። የድርጅቱ ልሳንም ቢሆን እራሱን የመተቸትና የመተጋገል አካሄድን መከተል አለበት። ጉባዔው መፈተሽና መስተካከል አለበት የሚለው የአቶ ስብሐት ነጋ ሃሳብም ትክክል ነው። አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ፤ የኢህአዴግ ጉባዔ መፈተሽ አለበት ከሚሉት ሰዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጾ ሲያበቃ፤ ኢህአዴግ ሊሠራ ያሰበውንና የሠራውን፤ እንዲሁም ያልሠራውን በተመለከተ በሩን ለትችት ክፍት ማድረግ አለበት። ጥቅምና ጉዳቱ የጋራ ስለሆነ ችግሮቹን ለማስተካከል በጋራ መሥራት ያስፈልጋል። ሁልም ጊዜም የተሻለ ለመሆን ፉክክርና የባለቤትነት ስሜት መኖር እንዳለበት ያነሳው አትሌት ኃይሌ፤ ህዝብ የአገሪቱ ባለቤት መሆን ስላለበት የተሠራውን መንከባከብ፣ ያልተሠራውን መጠየቅና መሥራት ይገባዋል የሚል እምነት አለው። ለዚህ ደግሞ ሚኒስትሮች ለተቀመጡበት ቦታ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ለመሥራት ዝግጁ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የአህአዴግ ጉባኤ ወሳኙን ድርሻ ስለሚይዝ ለዚህ ዓይነቱ አካሄድ ምቹ መንገድ መፈለግ ይኖርበታል። «የምንከተለው አካሄድ የምዕራብም የምሥራቅ ያልሆነ ነው። በቅርቡ በአገሪቷ የተከሰተው ችግርም ቢሆን የኢህአዴግ የእርስ በእርስ መተጋገል በመቀዝቀዙ የተፈጠረ ነው። አሁንም ቢሆን ነገ ችግሩ ዳግመኛ ላለመከሰቱ ማስተማመኛው ምንድነው? ዋስትናዬ መንግሥት ከሆነ፤ እንደ አቶ ስብሐት በግልጽ በመነጋገርና በመወቃቀስ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል» በማለትም የአቶ ስብሐትን ሃሳብ እንደሚጋራው አስታውቋል። በመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ገነነው አሰፋ ደግሞ፤ ኢህአዴግ ጉባኤውም ብቻ ሳይሆን የምስረታ ዘመኑ ላይ የነበረው የመሥራቾች የጋለ የትግል መንፈስን መመለስ ወይንም ወደዚያ የተቃረበ መንፈስ መፍጠር አለበት፤ አለበለዚያ አሁን የገባባት ችግር በቀላሉ የሚፈታ አይደለም የሚል አመለካከት ነው ያላቸው። አማካሪው እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት ችግሮች መፍትሔ ካልተሰጣቸው ማለቂያ ወደ ሌለው አደጋ ያመራል። በፌዴራልዝም ስርዓቱ እያንዳንዱ አባል ህገ መንግሥታዊ ዋጋ ወደ መክፈል ካልገባ አዳጋች ይሆናል። የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ እራሱን መፈተሽና ማስተካከል እንዳለበትና ለዘመናት እንዲያስተካክል ሲጮሁ የኖሩለትን ሃሳብ አቶ ስብሃት ዛሬ በገሀድ መናገራቸው ትክክል መሆኑን ገልጸዋል። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ችግሮች መታየት ያለባቸው በኢህአዴግ ማዕቀፍ ሳይሆን በመንግሥት መዋቀር ነው። የኢህአዴግ ጉባኤ የድርጅቱ ጉዳይ የሚመከርበት መድረክ እንጂ ኢህአዴግ በመንግሥት ሥራዎች ጣልቃ እየገባ የሚገመግምበት መድረክ መሆን የለበትም። «አሁን ባለው ሁኔታ በኢህአዴግና በመንግሥት መካከል ልዩነት ጠፍቷል። ህዝቡ ጥያቄዎችን ያቀረበው ለመንግሥት ነው። በመሆኑም በድርጅት መዋቅር መፍታቱ ቀርቶ ሁሉም ዜጋ በሚያገባውና ግብር እየከፈለ በሚያስተዳድረው የመንግሥት መወቀር መፍትሔ መስጠት ይገባል» ብለዋል አቶ ሙሼ። እንደ አቶ ሙሼ ገለጻም፤ ኢህአዴግ በታሪኩ ከፓርቲው መዋቅር ወጪ ያሉ ሰዎችን ለአገር ይጠቅማሉ ብሎ የመሾም ዝንባሌ እንደ አሁኑ በብዛት ታይቶበት አይታወቅም። እንዲያውም ከዚያም ወርዶ ምንም ቢሆን ለፓርቲ ታማኝ ከሆነ ማንኛውን ቦታ ያገኛል የሚል አስተሳሰብ ነበረው። አሁን ግን ይህንን ሊሰብር በሂደት ላይ ነው። ይህንን ማበረታታት ያስፈልጋል፤ ዋጋም የሚሰጠው ዕርምጃ ነው። ዲያቆን ዳንዔል በበኩሉ፤ በፓርቲው ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ባህል ይበልጥ ለማጠናከርና ለአገር የሚበጅ ሥራ ለመሥራት ኢህአዴግ ለአንድ ቦታ ሰው ከመሾሙ በፊት ለቦታው የሚመጥኑ ሰዎች ክርክር ሊያደርጉና ፖሊሲውንም ሆነ ስትራቴጂውን ይበልጥ ላሳከው የምችለው እኔ ነኝ ብለው መሟገት አለባቸው የሚል ምክረ ሃሳብ አለው። «ይህንን ሂደት አልፈው ወደ መንግሥት አስተዳደር የሚመጡ ሰዎችም በመንግሥት ኃላፊነት ላይ አይቸገሩም። በአንጻሩ ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ስልጣን እንዳይወጡ ማድረግም ያስችላል፤ፓርቲውንም ማዳን ይቻላል።» አትሌት ኃይሌ በበኩሉ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ችግር የለባትም፤ ችግራችን የማስፈጸም ነው ይልና፤ «የዚህ ቁልፉ ችግር ድግሞ ፖሊሲውን ያወጣው አካል እራሱ ፈጽሞ ወደታች አለማውረዱ ነው። የኢህአዴግ ጉባዔ በአሠራሩ ህጎችን ያሳልፋል እንጂ ጉባኤውን የሚመራው ከፍተኛ አመራር ያወጣውን አሠራርም ይሁን ፖሊሲ እራሱ ፈጽሞ አያሳይም። ስለ ሙስና፣ ስለ መልካም አስተዳደርና ስለሌሎችም ይወራል። ብዙ ጊዜ ችግር ያለው እታች ነው ይባላል። ነገር ግን ችግሩ የሚጀምረው ከላይ ነው። እነርሱ ለህጉ ተገዥ ከሆኑ በተዋረድ ያለው አመራርም ይሁን ፈጻሚ ለህግ ተገዥ የማይሆንበት ምክንያት የለም”» ሲል ሃሳቡን ቋጭቷል። አቶ ገነነው በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ ጉባኤውንም ብቻ ሳይሆን አሠራሩንም ማሻሻል ይገባዋል የሚል አመለካከት አላቸው። «ፓርቲዬ ባስቀመጠኝ ቦታ እሠራለሁ የሚባለው አካሄድ መሻሻል አለበት። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የተወሳሰቡና ለማስተናገድም ጥበብ የሚፈልጉ ነገሮች ተፈጥረዋል። ከተነሳሽነት ባለፈ የቴክኒክ እውቀትም የግድ ሆኗል። ተነሳሽነትና ለፓርቲ ያለው ታማኝነት በጊዜ ሂደት እየተሸረሸረ በመምጣቱም ጠንካራ የመቆጣጣሪያ ስርዓት መትከልና መዘርጋት አለበት። ይሄንን ማድረግ ካልተቻለ የዚህ አገር ችግር እየተወሳሰበ ሄዶ ወደማይፈታበት ደረጃ ይደርሳል። ከዚያ በፊት የመሥራችነት ዘመን መንፈስ ይመለስ፤ ጉባኤውም ይታደስ» ብለዋል።