ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ የተወለዱት ትግራይ አክሱም ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ግንኙነት በአሜሪካ፣ ሁለተኛውንም በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ በኔዘርላንድ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ሠርተዋል፡፡ ወይዘሮ ሰሎሜ የመንግሥት ቃል አቀባይ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚዲያና የፖለቲካ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጀንደር ዲፓርትመንትም አማካሪ በመሆን፣ እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠርተዋል፡፡ ኢመርጅ የተሰኘው የቢዝነስ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ዲፊድ (DFID) የሚደገፈው የኛ ፕሮሞሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተርም ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሰሎሜ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ጥምረትን በመመሥረት እንደ ‹‹አንድ ብር ለአንድ ወገን›› ያሉ ስኬታማ የዕርዳታ ዘመቻዎችን በመምራትም አስተዋፅኦ አድረገዋል፡፡ ‘የኛ’ በወጣት ሴቶች ዙሪያ የአመለካከት ለውጥ ማምጣትን ግቡ ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡ ‘የኛ’ በሴቶች ዙሪያ የሚንፀባርቁ አመለካከቶች፣ እምነቶችና ምግባሮች ላይ ሐሳቦች እንዲንሸረሸሩ የሚያስችል የሚዲያ ሥራ ሲሆን፣ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ብቻ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሬዲዮ ድራማ ተከታታዮች እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት የ“የኛ” ደጋፊ የሆነው የእንግሊዝ ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት ዲፊድ (DFID) ለፕሮጀክቱ የሚያደርገውን ዕርዳታ ማቋረጡን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግል ሕይወታቸውን በሚመለከት ምሕረት አስቻለው ከ‘የኛ’ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ፈንዱ ከመቋረጡ በፊት ውሳኔውን በሚመለከት የተደረጉ ውይይቶች ወይም ውሳኔውን የሚመለከት መረጃ ነበር ወይ?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- የዲፊድ አጋርነት ለገርል ኢፌክት (Girl Effect) በመሆኑ ፈንዱ በቀጥታ ወደ እኛ አይደለም የሚመጣው፡፡ ፈንዱ ሲፈቀድም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በክፍል በክፍል ሥራዎችን ተከትሎ ነው የሚለቀቀው፡፡ ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት ውሳኔውን በሚመለከት በዲፊድና በገርል ኢፌክት መካከል ንግግር እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በዚህ ቀን ስለምናቋርጠው እንደዚህ ይሆናል የሚል ነገር እኛ ዘንድ አልደረሰም፡፡ በቀጥታ ለእኛ ከዲፊድም ሆነ ከገርል ኢፌክት እንደዚህ ልናደርግ አስበናል ተብሎ የደረሰን ምንም ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ውሳኔውን ያወቃችሁት “የኛ”ን በመቃወም ከበፊት ጀምሮ ይጽፍ ከነበረው ዴይሊ ሜል ጋዜጣ ነው ማለት ነው? ውሳኔውም ድንገተኛ ነው ማለት ነው?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- ዴይሊ ሜል አሁን የጻፋቸውን ነገሮች እንደ ቀድሞ መመልከት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የእንግሊዝ የውስጥ ፖለቲካ ተቀይሯል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ድሮ በሰማንበት ጆሮ ልንሰማው አንችልም፡፡ ወደኋላ ሄደን የዴይሊ ሜል ዘገባዎችን ስንመለከት ስለየኛ ከመጻፉ በፊት ስለዕርዳታና ስለሥደት ብዙ ጽፏል፡፡ አሁን የሚጽፋቸው ነገሮች ግን የሚንፀባረቁት በተለወጠው የአገሪቱ ውስጣዊ ፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ነው፡፡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ወጥታለች፡፡ ለዲፊድ አዲስ ሴክሬታሪ ተሹሟል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ለውጦች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኛ ከዲፊድ ያገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ያጣው በእንግሊዝ የውስጥ ፖለቲካ ምክንያት ነው?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣትን ተከትሎ በአገሪቷ የቀኝ ዘመም ፖለቲካ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ይህ ፖለቲካ በጀርመን፣ በፈረንሣይ፣ በኔዘርላንድም እየታየ በመሆኑ በሌሎችም አውሮፓ አገሮች እንደሚቀጥል ይገመታል፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ነገር እየተስተዋለ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ አካሄድ ተፅዕኖ ውስጥ ከሚወድቁ ነገሮች አንዱ ዕርዳታ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሥደት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው በአጠቃላይ እንግሊዝ ውስጥ ፀረ ዲፊድ ፀረ ዕርዳታ ዘመቻ የተጀመረው፡፡ የራሳችን አገር ውስጥ እንዲህ ወይም እንደዚያ እየሆነ ዕርዳታ መስጠት አለብን ወይ? ለምን ዕርዳታ እንሰጣለን? የሚሉ ዘገባዎች ይሠራሉ፡፡ ዘመቻዎችም እንደዚያው፡፡ በዚህ ውስጥ እንደ ማሳያ ቀዳሚ ዒላማ ሆኖ የተገኘው ደግሞ የኛ ነው፡፡ የኛ ለምን ተቀዳሚ ዒላማ ሆነ ለሚለውም ምክንያት አለው፡፡

ምዕራባውያን ዕርዳታን የሚመለከቱት ለተራቡ ሰዎች ዳቦ ከመስጠት፣ የውኃ ጉድጓድ ከመቆፈር፣ መድኃኒት ከመስጠትና ከመሳሰሉ የነፍስ አድን ሥራዎች አንፃር ነው፡፡ ሰዎች የራሳቸውን ዳቦ እንዲጋግሩ፣ የባህሪ ለውጥ አምጥተው የራሳቸውን ማንነት እንዲገነቡ የማብቃት ሥራም አለ፡፡ የኛ ከሌሎች የዕርዳታ ድርጅቶች በተለየ የሚከተለው መስመርና አሠራር የተለየ እንደሆነ ቀደም ሲልም ተናግረናል፡፡ የኛ የሚጠቀመው መገናኛ ብዙኃንን ነው፡፡ የሚጠቀመው መስመር ማስቻልን ነው፡፡ የሚችሉ ሴቶችን የሚፈጥር እንጂ ዕርዳታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሴቶች ረዥም ርቀት ሄደው ውኃ እንዲቀዱ ጀሪካን የሚያድል ሳይሆን፣ ከእንደዚህ ያለ ሁኔታ የመውጣት አቅምና ብቃት ያላቸውን ሴቶች መፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉ ፕሮጀክቶች በተጠቀሰው የፖለቲካ ዕርምጃ ማሳያ ቀዳሚ ዒላማ የመሆን ዕድላቸው ግን ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ውጪ ሊጠቀስ የሚችል ነገር ይኖራል?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- በዘገባዎቹ ፕሮግራሙን ያለመረዳት ነገርም ይታያል፡፡ ሆን ብሎ ወይም በስንፍና የሚባለው ቶክ ሾው እንዲጀመር ይኼን ያህል ገንዘብ ተሰጠ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ግን ሲጀመርም ቶክ ሾው፣ ድራማ፣ ሙዚቃ አለው፡፡ የግብር ከፋዩ ብር የኢትዮጵያ ‘ስፓይስ ገርል’ን ለመፍጠር እየሄደ ነው እየተባለ ነው የተዘገበው፡፡ የኛ ግን ዕርዳታ በልዩ መልክ የተሠራበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁልጊዜም ደግሞ የተለየ ነገር ሲሠራ ተቃውሞ አለ፡፡ የተለመደ ነገር የሚሠራ ፕሮጀክት አይጨፈጨፍም፡፡ ወጣ ያለ ነገር ግን አነጋጋሪም አወዛጋቢም ይሆናል፡፡ እዚህ አገርም ሆነ ውጭ ሰዎች እንዲረዱት የምፈልገው ሌላ ነገር ከድራማ፣ ከሙዚቃና ከቶክ ሾው ሌላ በተለይም በአማራ ክልል የኛ መሬት ላይ ወርዶ የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከተፈለገ ይህንን ወደ አማራ ክልል ወጣ ብሎ ማየት፣ ውጤቱ ምንድነው ብሎ መጠየቅም ይቻላል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ ሦስት ሺሕ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ ከአማራ ክልል የትምህርት በሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለትምህርት ቤቶቹ በሙሉ የኛ በፍላሽ ዲስክ ይሠራጫል፡፡ ስለዚህ በሚኒ ሚዲያ የኛ በትምህርት ቤቶቹ ይሰማል፡፡ በዚህ ምክንያት እንደ እንጅባራ፣ ደንበጫ ባሉ ከተሞች እኛ ቡድን መሥርቱ ብለን ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ተማሪዎች የየኛ ክለቦችን መሥርተዋል፡፡ በመጨረሻ ውጤት ማምጣት የሚቻለው ደግሞ እንዲህ በራሳቸው ተነሳሽነት መንቀሳቀስ የሚችሉ ሴቶችን መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮችና መምህራንም የኛን እንደ አንድ ማስተማሪያ እንደሚጠቀሙበት ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

አሠራራችን ከሰማይ የወረደ ሳይሆን ዲፊድም ለሰባትና ለስምንት ወራት አጥንቶ እንደዚህ ዓይነት ነገር ነው የሚያስፈልገው ብሎ ነው ወደዚህ ነገር የገባነው፡፡ በዚሁ ክልል እሑድ እሑድ ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ ሴቶች የኛን ያዳምጣሉ፡፡ በሌሎችም ቦታዎች ከዕድሮችና (የወንድ) የሴቶች አደረጃጀቶች ጋር እንሠራለን፡፡ የኛ በዘጠኝ የሬዲዮ ጣቢያዎች ተከፍሎበት የሚተላለፍ ነው፡፡ ከ280 በላይ የየኛ አድማጭ ቡድኖች፣ በአማራ ክልል ከከፍተኛ የትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተውጣጡ ከ500 በላይ አምባሳደሮች አሉ፡፡ ዲፊድ የራሱን ውሳኔ ወስኗል፡፡ እኛ ግን በሠራነው ሥራ ደስተኞች ነን፡፡ ውሳኔው የየኛን ማንነት የሚጠይቅ ሳይሆን የፖለቲካ ውጤት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የየኛ የእስከ ዛሬ ግምገማ ምን ይመስል ነበር?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- ዲፊድ ዕርዳታ ሲሰጥ የራሱን ግምገማ አድርጎ ነው፡፡ በየዓመቱ ገለልተኛ አካል አምጥተው ፕሮጀክቱን ያስገመግማሉ፡፡ የኛ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመደዳ ‹‹ኤ›› አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ውሳኔው ከፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን ከፖለቲካ ተፅዕኖ የተነሳ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ለእስከዛሬው ዲፊድን እናመሠግናለን የኛ ግን ከዚህ ወዲህም በተሻለና በላቀ መንገድ ይቀጥላል፡፡ በዩኒቨርሲቲ መምህራን የምናሠራው የራሳችን ግምገማ ውጤትም ጥሩና ዲፊድ ካሠራቸው ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱን ዓላማ በተሻለ ሌላ ውጤታማ መንገድ ማሳካት ይቻላል? ለፕሮጀክቱ ወጪ የሆነው ገንዘብም በጣም የተጋነነ ነው የሚሉ አስተያየቶች በዘገባም፣ በተለያየ መንገድም ተንፀባርቀዋል፡፡

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- ዕርዳታ ሁሌም ፖለቲካ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የበለጠ ፖለቲካ ሆኗል፡፡ የዲፊድ ድጋፍ የማቋረጥ ውሳኔም ሙሉ በሙሉ ፖለቲካ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ የተሻለ ውጤታማ የሚያደርግ መንገድ አለ ከተባለ እየሰየው ነው፡፡ እኔ እየተያያዙ መሄድ አለባቸው የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት መያያዝ ሲኖርባቸው ዘላቂው ፍላጎት ነው ብለው ከሚያምኑ መካከል ነኝ እኔ፡፡ ቢሆንም ግን አቅርቦት አያስፈልግም ከሚሉት ግን አይደለሁም፡፡ ሙሉ በሙሉ አቅርቦት ማድረግ ግን እንደ አዙሪት ይሆን እንደሆነ እንጂ ከችግር ያወጣል ብዬ አላምንም፡፡ ባለብሮቹ ይኼ የተሻለ ነው ካሉ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ግን ደግሞ ፍላጎት መፍጠር ችግር ነው ማለት አይደለም፡፡ የኛ በጣም ደስ ብሎን የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ በውጤቱም በጣም ተበረታትተናል፡፡ የማይስተካከል ነገር የለም፡፡ ሁሌም ጥሩ ነገር እየተስተካከለ ነው የሚሄደው፡፡ ሴቶች ላይ መሥራት ለእኔ ትክክለኛው ነገር ነው፡፡ የሴት ልጅ ጉዳይ ላይ የሚሠራ ማንኛውም ሥራ ችግርም ቢኖርበት እየተስተካከለ መሄድ እንጂ ድርግም ብሎ መጥፋት የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ዕርዳታ ሁሌም ፖለቲካን የሚከተል የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችም የሚቀመጡበት ነው፡፡ ቀደም ብሎ የተነሳው ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የዕርዳታ ጉዳይ አለ፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ፈንድን እንደ አማራጭ እንመልከት ሲባል ያለው የአቅም ውስንነት ይታወቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የየኛ ቀጣይ ዕርምጃ እንዴት ነው የሚሆነው?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአገር ውስጥ አቅሞች ብቅ ብቅ እያሉ እያየን ነው፡፡ አቅም ስላለ ያ አቅም እንደ የኛ ያለውን ዓላማ ይደግፋል አይባልም፡፡ ይህንንም እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ግንዛቤ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እንደዚህ ያሉ ነገሮች ድጋፍ እያገኙ ይሄዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ሁሌም ዓይኔን የምጥልበት አንዱ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ60 ዓመታት በላይ ከእኛ ጋር አለ፣ መለያ ኩራታችንም ነው፡፡ የግድ የሴቶችን ጉዳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ድርጅት ረዥም ርቀት ሲጓዝና ስኬታማ ሲሆን ሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ ለመደገፍ ይነሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ባንኮቻችንም ይከተላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ግን ነገ የሚሆን እንዳልሆነም አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የመሥራትና የመቀጠል ነገር ነው መኖር ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አጋጣሚ የሚወሰደው ትምህርት ምን ይሆናል?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- መሆን አለበት የምለው ነገር አሁንም ሁለት ነው፡፡ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ኮርፖሬሽኖች ይሁኑ ኃላፊነት ወስዶ ባለቤት ሆኖ በጉዳዩ ላይ በጥንካሬ እየሠሩ መዝለቅ ያስፈልጋል፡፡ የኛ የመንግሥትን ሥራ የሚደግፍ ነው፡፡ መደገፍ ብዙ ብር መስጠት ላይሆን ይችላል፡፡ ነፃ የአየር ሰዓት መስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ድጋፍ ማድረግ የዚህን ያህል ቀላል ነው፡፡ አሁንም እኔ መሥራት የምፈልገው በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ይቀራል ማለትም አይደለም፡፡ እኛ አገር ስላልተለመደ ነው እንጂ የተለየ ዓላማ አንግበው የሚነሱ መገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ምናልባት ሌሎች ኮሜርሻል አማራጮችን መመልከት ሊኖርብን ይችላል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ አማራጮችን አስፍቶ መቀጠል እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዲፊድ ፈንድ የማቋረጥ ውሳኔ በቀጣይ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመመሥረት የምታስቡት አጋርነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- ውሳኔው ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም የተለያየ ዓይነት ለጋሽ ነው ያለው፡፡ ለጋሾች የተለያየ ፍላጎትና አስተሳሰብ ነው ያላቸው፡፡ ለጋሾች የእውነት ይህ ነገር ተፅዕኖ የሚፈጥር ሳይሆን እንዲሁ ብን ብሎ የሚጠፋ ነው፡፡ ዴይሊ ሜይል ግብር ከፋዩን ማስደሰት ነበር ዓላማው፡፡ ዓላማውን አሳክቷል፡፡ እኔ ዓለም ለመነጣጠል የቱን ያህልም ቢጥር አይቻልም ብለው ከሚያምኑ ሰዎች መካከል ነኝ፡፡ የተለያዩ የሚያያይዙ ፍላጎቶች አሉና፡፡ ስለዚህ በውሳኔው ተፅዕኖ የኛ ፈንድ አያጣም፡፡

ሪፖርተር፡- ውሳኔው በምን ያህል ደረጃ ተፅዕኖ ያሳድርባችኋል?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- አሁን ገና ሳምንት በመሆኑ የሆንነው ነገር የለም፡፡ በቀጣይ ተፅዕኖ ያሳድርብናል ወይ ከተባለ አዎ ነው፡፡ የየኛን ሐሳብ ወደሚደግፉ ተቋማት ዓይኔን እንዳዞር ያደርገኛል፡፡ ስምንተኛው ክፍል ድረስ የየኛ ፕሮዳክሽን ተሠርቷል፡፡ ታሪኩም እስከ አሥረኛው ክፍል ዘልቋል፡፡ ይህ በቀጣዮቹ ስድስት ሰባት ወራት ወይም በላይ ይሄዳል፡፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው ነገር ይቀጥላል፡፡ አልፎም ከፍ ብሎ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት አቅም ገንብተናል፡፡ ስለዚህ ውሳኔው የሚንደው ነገር የለም፡፡ ነገሮች ግን ቀላል ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገሮችን የምናደርገውም ቀላል ስለሆኑ አይደለም፡፡ እኔ በሕይወት ምርጫ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ፈተናዎቹን ተቋቁመን እናልፋለን እንቀጥላለን፡፡ ውሳኔው ብዙ ውጣ ውረድ ሊያስከትል ይችላል፣ ግን የኛ አይቆምም፡፡ ለውጦችን እያደረግን የተሻለ ደረጃ እንደርሳለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ንቅናቄ ጥሩ ነው፡፡ ወደ ተሻለ ደረጃ ይገፋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ውሳኔው የየኛን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኛን እንደ ዕርዳታ ድርጅት የመመልከት ነገር አለ፡፡ በዚህም የተነሳ የፈንዱ መቋረጥ የኛን ያስቆመዋል የሚል አመለካከት አለ?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- የኛ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሮጀክት አስፈጻሚ አይደለም፡፡ የኛን የሚሠራው ኢመርጅ ማንጎ የቢዝነስ ኩባንያ ነው፡፡ መጀመሪያ ጨረታ ተወዳድረን አሸንፈን ነው ከዲፊድ ድጋፉን ያገኘነው፡፡ ስለዚህ ይህ ቢዝነስ ኩባንያ በተለያየ የቢዝነስ ስትራቴጂ ይቀጥላል፡፡ እኔ በተለይም ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝ ከዚህ አንፃር መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ኢመርጅ ማንጎ የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን እየተመለከተ የመንግሥት፣ የኩባንያዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ድጋፍ ተጨምሮበት የኛን እንዲያስቀጥል ነው የምንፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- የኛ ላይ የምናነሳውን ነገር እዚህ ላይ ገትተን ወደ እርስዎ እንምጣ፡፡ በማኅበራዊ ጉዳዮች በተለይም ሴቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መሥራት የመፈለግዎን ያህል፣ በሌላ በኩል በፖለቲካው ዘርፍም ለአገርዎ ማበርከት የሚፈልጉት ነገር አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ባፈው ምርጫ የግል ተወዳዳሪ ለመሆንም ተንቀሳቅሰው ነበር፡፡ ዛሬም ይኼ ፍላጎት እንዳለ ነው?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- አዎ አሁንም የግል ተወዳዳሪ በመሆን በፖለቲካው መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ ሁሌም በዚህ መንገድ የምችለውን ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን የግል ተወዳዳሪነት ለሴቶች የተሻለ ነው የሚለውን ወደማመን እየመጣሁ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የወንድ የበላይነት የነገሠበት የመሆኑን ያህል፣ ፖለቲካ ፓርቲዎቹም እንደዚያው ናቸው፡፡ ብዙ ሴቶችን በፖለቲካ የማናየው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህም የግል ተወዳዳሪነት ለሴቶች የተሻለ አካሄድ ነው ብሎ ወደ ማመን እያጋደልኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለማየት የሚመኙት ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲስ ይኖር ይሆን?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሴቶች ፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊነት እየታየኝ ስለመጣ ይህ ዕውን ሆኖ ባይ እመኛለሁ፡፡ ለሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች ጉዳይ አንድ ነገር ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ዋናና ተቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ የሚንቀሳቀስ የሴቶች ፖለቲካ ፓርቲ ቢኖር የፆታ እኩልነት ለውጥ እንዲመጣ በደንብ መሥራት ያስችላል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ አስባለሁ እመኛለሁም፡፡ አጀንዳዬ ይኼና ይኼ ነው የሚል የሴቶች ፖለቲካ ፓርቲ ጠንካራና ድምፁ በደንብ የሚሰማ ይሆናል፡፡ የሴቶች ፖለቲካ ፓርቲ ማለት ግን ሴቶች ብቻ አባል የሚሆኑበት ሳይሆን በጉዳዩ የሚያምኑ፣ ጤናማ ኢትዮጵያን ማየት የሚፈልጉ ወንዶችም የሚኖሩበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አቅም ያላቸውና በፖለቲካ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ሴቶች አሉ፡፡ አቅም ያላቸውና ውጤታማ ሴቶች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው ሲመጣ ግን እውነታው ይህ አይደለም፡፡ እነዚህ አቅም ያላቸው ሴቶች ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዴት ሊመጡ ይችላሉ?

ወይዘሮ ሰሎሜ፡- በእውነት እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሴቶች አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውይይቶችን ከሌሎች ጋር አድርገን እናውቃለን፡፡ አቅም ያለው ሰውን የምንንከባከብ ማኅበረሰብ አይደለንም፡፡ የምዕራብ አፍሪካ አገሮችን እንኳ ብንመለከት አቅም ያለው ሰው ሲያገኙ ያን ሰው ለመንከባከብና ለመጠየቅም ይፈልጋሉ፡፡ እኛ አገር ደግሞ የመጨፍጨፍና የመንቀፍ አቅም ነው ያለን፡፡ አንድ ሰው ብቅ ብሎ የሆነ ነገር ለመሥራት ሲል ጭንቅል ጭንቅላቱን የምንል ነን፡፡ ይህ ይቀለናል፡፡ ይህ ደግሞ ሴቶች ላይ ይበረታል፡፡ ኅብረተሰቡ የወንድ የበላይነት የነገሠበት በመሆኑ ጭፍጨፋውም ሴት ላይ ይደምቃል፡፡ የመሸማቀቅ፣ የመጥፋትና ወደኋላ የመመለስ ነገር የሚመጣው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ይህን የመለወጥ ኃላፊነት ያለው አንደኛ ኅብረተሰቡ ላይ፣ ሁለተኛ እኛው ራሳችን ሴቶች ላይ ነው፡፡ ማንም ይህን ሊለውጥልን ስለማይችል ሳንሸማቀቅ እንዴት ነው ይህን የምንበጥሰው? ነው ጥያቄው፡፡