Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ራሴን የለውጥ መሪ አድርጌ እመለከታለሁኝ›› ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

1 488

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በ1957 ዓ.ም. ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ፣ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በለንደን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኖቲንግሪም ዩኒቨርሲቲ ሠርተዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመሆን ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ያገለገሉ ሲሆን እስከ 2009 ዓ.ም. መጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሠርተዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን በመወዳደር ላይ ሲሆኑ ከተመረጡ የመጨረሻ ሦስት ዕጩዎች መካከል መሆን ችለዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ‹‹ቱጌዘር ፎር ኤ ሄልዚየር ወርልድ›› በሚል መሪ ቃል ለዚህ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት የሚያደርጉትን ውድድር በተመለከተ ዲቬክስ ከተሰኘ ድረ ገጽ ጋር ያደጉት ቃለ ምልልስ ወደ አማርኛ ተመልሶ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ጥያቄ፡- ይህንን ኃላፊነት መረከብ ለምን ፈለጉ?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- በእውነት ይህን ሥራ የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ፡፡ ልምድም እንደዚሁ፡፡ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አድርጌያለሁ የዚህን ውጤትም ማየትም ችያለሁ፡፡ በጤናው ዘርፍ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባካበትኩት ልምድ አስፈላጊው የቴክኒክ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዕውቀት አለኝ፡፡ ሥራውን የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ ስል የተወለድኩት፣ ያደግኩትም አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ በሽታ ማኅበረሰቦችን፣ የራሴን መንደርና እኔን ራሴን እንዴት እንዳጠቃን አውቃለሁ፡፡ እንደ ወባ ያሉና ሌሎች በሽታዎች የጤና ብቻም ሳይሆን የሚያስከትሉትን ኢኮኖሚያዊ ጫናም ተመልክቻለሁ፡፡ ይህን ማወቅ የኢኮኖሚክስ ዕውቀት አይጠይቅም፡፡ ሰዎች አልጋ ላይ ውለው ሰብል የሚሰበስብ ጠፍቶ ነበር፡፡ ሰዎች ለምን እንዲህ ይሰቃያሉ? ለምን ልናድናቸው አልቻልንም? ይህን ችግር ለምን አንፈታውም? የሚሉና ሌሎችንም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አድርጎኛል፡፡ ከዚያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለይም የወባ መቆጣጠሪያ ፕሮግራም አባል በመሆን የወባ ወረርሽኝ ምን ያህል ጥፋት እንዳደረሰ ተመለከትኩኝ፡፡ መከላከያዎችን በማድረግ ሕክምናዎችን በመስጠት ብዙዎችን ረዳን፣ የብዙዎችን ሕይወት አተረፍን፡፡ ቢሆንም የወረርሽኙ ተፅዕኖ በጣም ከባድ ስለነበር የሠራነው በቂ መሆን አልቻለም፡፡ ብዙዎች የአልጋ ቁራኛ በመሆናቸውና በመሞታቸው ሰብል የሚሰበስብ አልነበረም፡፡ ነገሩ አዕምሮ የሚረብሽና ሊቀበሉትም የሚከብድ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለጤናው ዘርፍ የምችለውን ሁሉ ማበርከት አለብኝ ያልኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የሁለተኛ ዲግሪ ከዚያም ፒኤችዲና ሌሎችንም ጥናቶቼን ያደረግኩት፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበርኩበት ወቅት ወባ ላይ በጣም ሠርቻለሁ፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት አሥራ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የወባ ወረርሽኝ ያልታየው፡፡ ይህ የተሠራው ሥራ ክፍያ ውጤት ነው፡፡

ጥያቄ፡- ከራስዎ ልምድ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያመጡት ተሞክሮ?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- በጠንካራ የጤና አገልግሎት ሥርዓት አስፈላጊነት አምናለሁኝ፡፡ እንደ ወባ ዓይነቱን በሽታ መዋጋት የሚቻለው በዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ያደረግነው ወባን እየተዋጋን ጎን ለጎን የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት፣ የመረጃ መሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይልና የጤና ዘርፍ ፋይናንሲንግ ግንባታ ጀመርን፡፡ በእርግጥ ረዥም ጊዜ ያገለገልኩ የአፍሪካ ሚኒስትር ነኝ፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች አሳክተናል፡፡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሞትን በሁለት ሦስተኛ፣ የእናቶች ሞትን በ71 በመቶ፣ የኤችአይቪን ሞት በ90 በመቶ፣ እንዲሁም የቲቢ ሞትን በ64 በመቶ ቀንሰናል፡፡ የጠቀስኩት የጤና አገልግሎት ሥርዓት ማሻሻያና ግንባታ የተሠራው በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ መሠረት ነው፡፡ ድርጅቱ ሁሉም የጤና ዘርፍ አካል ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ይፈልጋል፡፡ እኛም የተከተልነው ይህንኑ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ልምድ አለኝ፡፡ ኃላፊነቱንም በሚገባ ልወጣው እችላለሁ ስልም የዓለም ጤና ድርጅትን መመሪያ ስለተገበርኩት፣ በመመሪያው መሠረት የጤና ዘርፍ ማሻሻያዎችን ስላደረግኩኝና አገሮች ይህን እንዲተገብሩ መርዳት ስለምችል ነው፡፡ በዚህ በደንብ አምናለሁ፡፡ አድርጌዋለሁና በዓለም አቀፍ ደረጃም በተሻለ ደረጃ መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን አደርጋለሁ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም እንደ ግሎባል ፈንድ፣ የተመድ የኤድስ ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የእናቶች፣ የጨቅላና ሕፃናት ጤና አጋርነት ድርጅትና ሮልባክ ማሌሪያ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መርቻለሁ፡፡ እንደ ጋቪና ቫክሲን አልያንስ ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቦርድ አባልም ነኝ፡፡ በተለይም በግሎባል ፈንድ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2011 ያገለገልኩ ሲሆን ዓለም አቀፍ ልምድ አለኝ፡፡ ግሎባል ፈንድ ከግራና ከቀኝ ወቀሳ ሲሰነዘርበት ማሻሻያዎችን በማድረግ ለውጦች እንዲደረጉ አድርጌያለሁ፡፡ በዚህ ራሴን የለውጥ መሪ አድርጌ እመለከታለሁኝ፡፡ ዛሬ ግሎባል ፈንድ እንዴት እየገሰገሰ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ ይመስለኛል እኔን ከሌሎች ዕጩዎች የሚለየኝ፡፡ የሚፈለገው ልምድ አለኝ ስል እንዲሁ ዝም ብሎ ማውራት ሳይሆን የምለው የኖርኩትን፤ ያደረግኩትን ነው፡፡ የችግሮች ተጠቂ ነበርኩኝ፣ ችግሮችን እንደ ሚኒስትር ተጋፍጫለሁ፣ የጤናው ዘርፍ ላይ ለውጥ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ውጤትም አስመዝግቤያለሁ፡፡ ይህን ኃላፊነት የፈለግኩበት ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ያለኝን የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የቴክኒክ ዕውቀቴን ያገናዘበ ነው፡፡ ለልማት የዋሉ የፋይናንስ ድርድሮችን በመምራት ለውጤት አድርሻለሁ፡፡ እነዚህ እነዚህ ልምዶቼ ሚዛን በጠበቀ መልኩ የዓለም ጤና ድርጅትን ይጠቅማሉ፣ ወደ ፊት ያራምዳሉ ብዬ አምናለሁኝ፡፡ ድርጅቱ እንዲሁ የቴክኒክ ድርጅት አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ዕርምጃ ዓለም አቀፍ መሪም ያስፈልገዋል፡፡ የቴክኒክ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ዕውቀት ሚዛን መጠበቅ ያስፈልገዋል፡፡

ጥያቄ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ዋነኛ ተግዳሮቶች ምንድናቸው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- ድርጅቱ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ውጤታማ፣ ብቃት ያለውና ግልፅነት የተሞላ አሠራር ያለው ተቋም ያስፈልገናል፡፡ እዚህ ላይ የለውጥና መረጋጋት ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊነት ወሳኝ ነው፡፡ ማሻሻያ ስናደርግ ነገሮች እንዲፈጸሙ ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ ምክንያቱም ዓለም ፈጣን ውጤቶችን ይጠብቃልና፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የድርጅቱን ተዓማኒነት ማረጋገጥ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸው የተለዩ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- የማሻሻያ ለውጥ ስል ሰፋ አድርጌ ነው ነገሩን የምመለከተው፡፡ አንድ ነገር ይዞ ለውጥ አድርጌአለሁ አይባልም፡፡ ለውጥ የሚጀምረው መረጃዎችን ከመስማት፣ አገሮችን፣ አባል አገሮችን ከማድመጥ፣ ለውጥ የሚያስፈልገው የት ላይ እንደሆነ ከማወቅ ነው፡፡ የቱ ነገር ላይ ማሻሻያ ይደረግ ብቻም ሳይሆን መቼ የሚለውንም ማሰብ፣ ሁሉም አገር መሳተፍም ይኖርበታል፡፡ እኔ የማደርገው ይህን ነው፡፡ ሁሉንም የሚያሳትፍ የለውጥ ሒደት፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሒደቱን የጀመርነው ያለውን ሁኔታ ከመገምገም ነው፡፡ በጥናቶች ውጤት መስማማት የማኅበረሰቡን ይሁንታም ማግኘት ነበረብን፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የፖለቲካ መሪዎች፣ አገሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪል ማኅበራትን ይሁንታ ማግኘት ነበረብን፡፡ እንደዚህ ነው ውጤታማ ማሻሻያ ማድረግ የቻልነው፡፡ ከሐሳብ ጀምሮ ማሻሻያና ለውጥ አካታች መሆን አለባቸው፡፡ እውነቱም ለውጦች መጀመር ያለባቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ በማድመጥ መሆኑ ነው፡፡ ማሻሻያው ብዙ ነገሮችን ሊሸፍን ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- ፋይናንሲንግ ከዓለም ጤና ድርጅት ችግሮች በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ መጠቀም የሚችሉት የበጀቱን ሃያ በመቶ ብቻ በመሆኑ መጪው ዋና ዳይሬክተር ጫና ውስጥ ይገባል፡፡ ይህን በምን መንገድ ለመወጣት ያቅዳሉ?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- አባል አገሮች በ20 በመቶ መዋጮ ድርጅቱን የራሳቸው ማድረግ አይችሉም፡፡ በአንድ ኩባንያ ከ50 በመቶ በታች ሼር ካለህ ትልቅ ባለድርሻ አይደለህም፡፡ ቀላል መርህ ነው፡፡ ይህን ድርጅት የራሳችን እንዳላደረግነው ይህም ያለን ድርሻ 20 በመቶ ብቻ በመሆኑ እንደሆነ የዕጩዎች ፎረም ላይ ሐሳብ አንስቼ ነበር፡፡ መዋጮአችንን ከፍ በማድረግ ቁርጠኝነታችንን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ ይህን ማድረግ የምንችለው በትንሹ 51 በመቶ መዋጮ በማድረግ ነው፡፡ አብላጫ ባለድርሻ ለመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ የሚታመንበት ነገር ነው፡፡ በዚህ መልኩ መዋጮ ጥሩ ካልሆነ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ማድረግ አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት የአባል አገሮች በድርጅቱ ላይ ያላቸው በራስ መተማመን ዝቅተኛ ነው፤ ለዚያም ነው አገሮች አስተዋጽኦዋቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የምጠይቀው፡፡ እኛም በፍጥነት ውጤት በማምጣት አገሮች በድርጅቱ እንዲተማመኑ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ነገሮች ተከውነው ውጤት መምጣት መቻል ይኖርበታል፡፡

ጥያቄ፡- የሚሏቸው ፈጣን ውጤቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- ሊነሱ የሚችሉ ወረርሽኞችን መገመት ባንችልም ዝግጁ በመሆን የተሻለ መሥራት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ኢቦላ ላይ የነበረው ነገር የዓለም ጤና ድርጅት ክፍተት የታየበት ነበር፡፡ መሠረታዊ ነገሮቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ቀድሞ ማወቅ፣ አፋጣኝ ምላሽ፣ የቅኝት ሥርዓትን ማጎልበት፣ በአገሮች መካከል ያለውን ተግባቦት ማሻሻልና ዓለም አቀፍ የጤና ቁጥጥሮችን በታማኝነት ተግባራዊ ማድረግ ናቸው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አምስቱን ለይቼ አውጥቻለሁ፡፡ የመጀመሪያው ድርጅቱ ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ዩኒቨርሳል የጤና ሽፋን ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በተቀናጀ የመንግሥት ሥርዓት ቀድሞ ከማወቅ ጀምሮ የድንገተኛ ምላሽ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ አራተኛው በብዙ አገሮች ትኩረት የማይሰጣቸው እናቶች፣ ሕፃናትና ታዳጊዎች ላይ ማተኮር ነው፡፡ የሕዝብን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ክፍል ስታገልል ዕርምጃህ ያን ያህልም ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ አምስተኛው ደግሞ የአየር የአካባቢ ለውጥ ነው፡፡ ብልፅግና የሚያመጣው ጤናማ ማኅበረሰብ እንደሆነ በማመን የዓለም አቀፍ የልማት አጀንዳ ዋነኛ ነጥብ ጤና መሆን አለበት፡፡ ሁሉም መንገድ ወደ ዩኒቨርሳል ጤና ሽፋን የሚያመራ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ዩኒቨርሳል የጤና ሽፋን ማለት ማንም ከኋላ አይቀርም ማለት ነው፡፡ ተላላፊ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ የእናቶች ጤና በጉዳት ወይም በእርጅና ማንም ወደኋላ አይቀርም፡፡ የጤና ሽፋኑ የሥነ ሕዝብ ለውጦችንም የሚመለከት በመሆኑም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ትኩረት ዩኒቨርሳል የጤና ሽፋን ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህን ሁሉም ይረዳል፣ ችግሩ ለውጥ አለማድረጋችን ነው፡፡ ማድረግ ብንችል ግን ብዙዎቹ የጤና ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ስለዚህም ትኩረታችን በዚህ መልኩ መቃኘት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ ትግበራው ቀላል አይሆንም፡፡ ይህ ኢትዮጵያ እንዴት ነው የሆነው? የሕክምና ባለሙያዎችን ማቆየት ትልቅ ችግር ሆኖ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ የሰው ኃይል ቀውሱ መሠረት የተማረ የሰው ኃይል ነው ብለን ማሰባችን ስህተት ነበር፡፡ ችግሩ ግን ውስጣዊ ነው፡፡ ያለውን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ እያሠለጠንን አልነበርንም፡፡ ስለዚህም ለሁለት ዓመታት በየዓመቱ ቅበላችንን ከ300 ወደ 3000 አሳድገን ነበር፡፡ ብዙዎቹን ትልልቅ ሆስፒታሎችን ወደ ማስተማሪያ ሆስፒታልነት ቀየርን፡፡ በተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት አሁንም የሠለጠኑ ሰዎቻችንን እያጣን ቢሆንም በዓመት ከ2000 በላይ እያስመረቅን ነው፡፡ መፈታት ያለበት መሠረታዊ ችግሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ችግሩን የፈታነው እንዲህ ነው፡፡

ጥያቄ፡- የፈንድ አመዳደብ ላይ ያሉ ነገሮችን እንዴት ያስተናግዷቸዋል? ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ከሚገኘው ፈንድ ከፍተኛው ለኤችአይቪ የሚውል ነው፡፡  

ዶ/ር ቴድሮስ፡- ያደረግነው ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መደራደር ነበር፡፡ ትልቅ የጤና ችግር የሆነው በሽታ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ነገር ግን ደግሞ የጤና ሥርዓቱ ወደፊት የሚመጡ የጤና ችግሮችን መፍታት የሚችል ይሆን ዘንድ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ላይም መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ነገርናቸው፡፡ በዚህ መሠረትም የጤና አገልግሎት ሥርዓቱ የመረጃ ፍሰት፣ የመድኃኒት አቅርቦት፣ የሆስፒታሎች ማኔጅመንትና የጤናው ዘርፍ ፋይናንስ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ችለናል፡፡ ሥርዓቱን እንዲሁ በጥቅል ሳይሆን ወባ፣ ኤችአይቪ፣ ቲቢ እንዲህ እንዲህ እያልን ነው የተመለከትነው፡፡ ቢሆንም ሥርዓቱንም በጥቅል መመልከት የሚያስፈልግበት ምክንያት አለ፡፡ በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ማሻሻያው በፔፕፋር፣ ግሎባል ፈንድ፣ በእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ልማት ድርጅትና በሌሎችም አገሮች ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ እናም የጤና ሥርዓቱ አሁን በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ያደረግነው ድርድር በጣም ጥሩ ነበር፤ የጤና ሥርዓቱ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ማሳየት ችለን ነበር፡፡

ጥያቄ፡- ኢቦላን በሚመለከት ከተስተዋለው ነገር ለዓለም ጤና ድርጅት ትምህርት ይሆናል የሚሉት ነገር?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- ያሉንን ነገሮችና አመቺ ሁኔታዎች መመልከት ያለብን ይመስለኛል፡፡ በላይቤሪያ፣ ጊኒና ሴራሊዮን ችግሮች የነበሩ ቢሆንም በናይጄሪያ ግን ኢቦላ በጥሩ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ናይጄሪያዎችን ይህን ማድረግ ያስቻላቸው ቀደም ሲል ለፖሊዮ የዘረጉት ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ሌላ ነገር ከመፈለግ ይልቅ እጅ ላይ ያለውን ነገር መጠቀም መቻል ትልቅ ነገር ይመስለኛል፡፡ ለፖሊዮ በተዘረጋው ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለኢቦላ ወረርሽኝ ምላሽ መስጠት ይቻላል እያልኩኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ ለኢቦላ ኬዝም አገልግሏል በዚህ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ሌላ አማራጭ መፈለግ ጠቃሚ ሆኗል፡፡

ጥያቄ፡- ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ወቀሳዎች ይሰነዘራሉ፡፡ አሁን እርሶ ለዓለም አቀፍ ኃላፊነት እየተወዳደሩ ነው፡፡ ለእነዚህ ወቀሳዎች ምላሽዎ ምንድን ነው?

ዶ/ር ቴድሮስ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በቁርጠኝነት ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ላይ እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት እንደሆነ የምንረዳውም ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚያድገው የሚጎለብተውም ከውስጥ እንጂ ከውጭ ይሆንሃል ተብሎ የሚታዘዝ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ደግሞ በግንባታ ላይ ያለ እንደመሆኑ ጉድለቶች ሊኖሩበት ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት ነውና፡፡

  1. Mulugeta Andargie says

    Hey!!! I forgot to say something; all the Africans are beside you!!! Have a confidence and campaign to Asia and South American.

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy