በመዲናዋ ቀለበት መንገዶች መብራት ባለመኖሩ በምሽት አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የትራፊክ መብራት በተገቢው ቦታ አለመኖሩም ችግሩን እንዳባባሰው ነው የገለጸው።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀለበት መንገዶች የመንገድና የትራፊክ መብራት ባለመኖሩ በምሽት አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመያዝ አዳጋች ሆኗል።
በቀለበት መንገድ የሚያሽከረክሩ በሰዎች ላይ አደጋ ካደረሱ በኋላ እንደሚሰወሩ አመልክተው፤ የትራፊክ ፖሊሶች በአካባቢዎቹ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ጫና እየፈጠረባቸው መምጣቱን ነው የገለጹት።
በአዲስአበባ ዋና ዋና መንገዶች በተለይም ከመካኒሳ-ጀሞ-ሀናማሪያም ወደቃሊቲ የሚወስደው የቀለበት መንገድ መብራት ባለመኖሩ ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት እየሆነመምጣቱን ነው የተናገሩት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ።
ምክትል ኢንሰፔከተር አሰፋ የትራፊክ መብራት የሚያስፈልግባቸው ቦታዎችን ለይቶ አለማወቅ አንዱ ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት መሆኑን ነው የተናገሩት። የሚያስፈልግበት ቦታ እያለ ከማያስፈልግበት ቦታ እየተተከለ መሆኑንም ገልፀዋል።
ምክትል ኢኒስፔክተር አሰፋ እንዳሉት ከሜክስኮ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ የትራፊክ መብራት ያስፈልጋል። ነገር ግን የለም፤ ገነት ሆቴል መታጠፊያ ላይ እንዲሁም የቀድሞው ጉምሩክ አካባቢ ለጊዜው አያስፈልግም፤ ግን የትራፊክ መብራት ተገጠሞለታል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት የመንገድ መብራቶችን በየወቅቱ እየፈተሸ ችግሮችን በፍጥነት ከመፍታት አኳያ ጉድለት እንዳለበት ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሄር ታፈረ እንደተናገሩት፤ በመንገድ መብራቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በግምገማ ተለይተው ታውቀዋል።
ከአዲሱ ገበያ ወደ ዊንጌት የሚወስደው የቀለበት መንገድም የመብራት ተከላ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው የተናገሩት።
ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የቀለበት መንገዶችንም ግንባታቸው እንደተጠናቀቀ የመብራት ተከላውን ስራ ለማከናወን አስፈላጊ ማቴሪያሎች መሟላታቸውን ነው የተናገሩት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ እንደገለጸው፤ መስሪያ ቤቱ አዲስ በመሆኑ ትራፊክ መብራት የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን መስመሮች የመለየት ሥራ እየሰራ ነው። ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል የጥናት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ትራፊክ ማኔጅመንት ዋና ዳይሬከተር አቶ ገነቱ ደሳለኝ፤ መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመ አንድ ዓመት መሆኑን ገልጸው።
ከመካኒሳ -ጀሞ-ቃሊቲ የሚወስደው መንገድ ትራፊክ መብራት ያልተገጠመለት መንገዱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ነው።
ለአገልግሎት ክፍት የሆነበት ምክንያት የመንገድ መጨናነቅ በመኖሩ “መጨናነቁን ይቀንሳል በሚል አማራጭ ነው” ብለዋል።
የመንገዱ ግንባታ እንደተጠናቀቀ በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ የመግጠም ስራ ወዲያውኑ ይከናወናል ነው ያሉት ።
አዳዲስ የመንገድና ትራፊክ መብራት የሚያስፈልጋቸውን ለመለየትም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።