Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲስ አበባን ‹‹ከጅብ ጥላ›› ለመታደግ

0 441

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲስ አበባን ‹‹ከጅብ ጥላ›› ለመታደግ

ከቀናት በፊት 24 ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነው፡፡ አንድ ነዋሪ በመስኮቱ በኩል የሳተላይት ቲቪ ስርጭት መቀበያ ዲሽ ሠሀን ለመትከል በማሰብ ግድግዳ ለመብሳት ሙከራ ሲያደርግ የሚበሳበት መሳሪያ ድምፁ ከፍ ያለ ነበረና የኮንዶሚኒየሙን ነዋሪዎች የኮሚቴ አባሎችን ጭምር ትኩረት ሳበ፡፡

ሰውየው ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ አቀርቅሮ ግድግዳውን መብሳት ቀጠለ፡፡ ሁኔታው ያስቆጣቸው የኮሚቴው አባል በንዴት ጦፈው በኃይለ ቃል ይናገሩ ጀመረ፡፡ ነገር ግን መደዳውን በየመስኮቱ የተተከሉ የዲሽ ሠሀኖች እያሉ ግድግዳውን አትብሳ ብለው ደፍሮ ለመናገር አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ይመስላል ቁጣቸውን ጀመር አድርገው ተውት፡፡ አትሥራ ነው የሚሉኝ በሚል ግራ በተጋባ ስሜት ሲያያቸው የነበረው ግለብም በመገረም አንገቱን እየነቀነቀ አቋርጦ የነበረውን ዲሽ የመትከል ሥራ ቀጠለ፡፡

ቴሌቪዥን ብርቅ የሆነበት ዘመን ካበቃ በኋላ ሰዎች የመረጃና የመዝናኛ አማራጫቸውን ለማስፋት በየቤታቸው የሣተላይት ዲሽ መትከልን ሥራዬ ካሉ ቆይቷል፡፡ በየመኖሪያ ቤቱ ጣራ ላይ፣ በየበረንዳው በተገኘ ቦታ ላይ ሁሉ ዲሽ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለው የዲሽ ሠሀን ብዛት አጀብ የሚያሰኝ ነው፡፡ በአንዳንድ ኮንዶሚኒየሞች በየበረንዳው ላይ ሌሎች ጋር ደግሞ መሬት ላይ ዲሽ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ ነገሮችን ቀለል ለማድረግ ትልልቅ ዲሾችን መሬት ላይ ተክለው የተወሰኑ ነዋሪዎች በጋራ እንዲጠቀሙ የሚያደርጉ ኮንዶሚኒየሞችም አሉ፡፡ በየኮንዶሚኒየሙ፣ በሌሎችም መኖሪያ አካባቢዎች ያለው ነገር ከላይ ሆኖ ለሚመለከት ከተማዋ የጅብ ጥላ ማሳ እስክትመስል በነጫጭ የዲሽ ሠሀን ተሞልታ ነው የምትታየው፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አከካባቢ የሚተከሉ ዕፅዋትን ሥርጭት አስተጓጎሉ በሚል የሚቆርጡ ሰዎች አሉ፡፡ ልጆች በሚጫወቱበት ጊዜ በአጋጣሚ ዲሹን በሚነኩበት ጊዜም ሥርጭት ይቋረጣል፡፡ ይህም በጎረቤታሞች መካከል ‹‹ልጅህ/ልጅሽ አስቸገረ›› በሚል የጭቅጭቅ ርዕስ እንዲሆን እያደረግ ይገኛል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የከተማዋን ውበት የተዘበራረቀ እንዲሆን አድርጓል በሚል ብዙዎች ይተቻሉ፡፡

እነዚህን ማኅበራዊ ችግሮች እንደሚያስቀር የታመነበት ወጥ የሣተላይት ቲቪ ሥርጭት መቀበያ ዘዴና እሳት አደጋ ጠቋሚ ቴክኖሎጂ ወደ አገሪቱ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በልደታ መልሶ ማልማት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃ 33 ላይ ተገጥሞ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አሥር ወራትን አስቆጥሯል፡፡

አገልግሎቱን እያቀረበ የሚገኘው ኢሰርቭ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ታደሰ እንደሚሉት፣ በቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች አንዳንድ ክፍተቶች አሉ፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ወጥ የሆነ የሣተላይት ቲቪ ሥርጭት መቀበያ ዘዴ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ነዋሪዎች በየመስኮቱ ዲሽ እንዲገጥሙና የከተማው ገፅታ እንዲበላሽ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩልም ሰዎች በገቡ በወጡ ቁጥር ዲሽ ለመትከል በየጊዜው ግድግዳውን የሚበሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ የቤቱን ዕድሜ የሚያሳጥር ነው፡፡ በየጊቢው ያሉ አረንጓዴ ቦታዎችም ለዲሽ ማስቀመጫነት እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

ይህንን ችግር መቅረፍ የሚችል ቴክኖሎጂ አገር ውስጥ እንዲሠራበት ለኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር በደብዳቤ በመጠየቅ፣ እንዲሁም አንድ ናሙና በድርጅቱ ውጪ ሠርቶ ለማሳየት ቃል ገብተው ከአመት በፊት ወደ ስራው መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህ መሠረትም በልደታ መልሶ ማልማት የጋራ መኖሪያ ቤት ሕንፃ ቁጥር 33፣ 25 ቤቶችን የያዘ ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ወስደው የሙከራ ስራውን እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

ቤቶቹ የእሳት አደጋ መጠቆሚያ መሣሪያ የላቸውም፡፡ በአጋጣሚ የእሳት አደጋ ቢከሰት እንኳን ሰዎች ሊወርዱበት የሚችል የአደጋ ጊዜ ማምለጫ የላቸውም፡፡ ለዚህም ከሣተላይት ዲሹ ጎን ለጎን የእሳት አደጋ መጠቆሚያ መሣሪያ መግጠምም ነበረባቸው፡፡ ይሁንና ከማኅበረሰቡ አኗኗር አንፃር ብዙም ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ እጣን፣ ሠንደልና ሌሎችም የጢሳጢሶች በጨሱ ቁጥር የእሳት አደጋ መጠቆሚያው እያስተጋባ ነዋሪዎች እንዲረበሹ ስላደረገ ለመተው አስበዋል፡፡ ነገር ግን አንገብጋቢ የሆነውን አንድ ወጥ የሣተላይት ቲቪ ሥርጭት መቀቢያ ቴክኖሎጂ ውጤታማ እንደሆነ አቶ መንግሥቱ ይናገራሉ፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በአንድ ጊቢ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአንድ ዲሽ ማንኛውንም ዓይነት የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ በፓይለት ፕሮጀክቱ ላይ የተረጋገጠውም ይኸው ነው፡፡ በኢሰርቭ ቴክኒካል ማኔጀሩ አቶ እንግዳወርቅ ደስታ እንደሚሉት፣ በፕሮጀክቱ ማለትም በልደታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕንፃ ቁጥር 33 ላይ የሚገኙ 25 ቤቶች የሚገለገሉበት ሁለት ዲሽ ተተክሏል፡፡ አንደኛው የናይል ሰዓት ላይ ያሉ ቻናሎችን መጠቀም የሚያስችል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዲኤስቲቪ ላይ ያሉን ሥርጭቶችን የሚያገኙበት ነው፡፡

አሠራሩ በተናጥል ዲሽ ተክሎ ማግኘት የሚቻለውን የቲቪ ሥርጭት ሁሉ ማግኘት የሚያስችል ነው፡፡ አገልግሎቱ በየቤቱ የሚገባውም በኬብል ሲሆን የሚተከለው የዲሽ ሠሀን ቋሚ በመሆኑ ሰዎች ሲወጡ ሲገቡ የሚነካ አይደለም፡፡ የአገልግሎቱ ክፍያም ለየቤቱ ከ1200 እስከ 1700 ብር ድረስ ነው፡፡ በአንድ በተወሰነ ቦታ (በሕንፃው ጣራ) ላይ የሚቀመጥ በመሆኑ በንክኪ የመበላሸት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ዝናብና ነፋስ በመጣ ቁጥርም ሥርጭቱ እንደሌላው እንደማይቋረጥ ያናገራሉ፡፡

‹‹ቴክኖሎጂው በሁሉም ህንፃዎች ላይ ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይም በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ወሳኝ ነው፡፡ ቀድሞ በተላለፉ ቤቶች ላይም መሰራት አለበት፡፡ ለህዝብ ለመተላለፍ በዝግጅት ላይ ባሉ ቤቶች ላይ ለመግጠም እንቅስቃሴዎች ጀምረናል›› ብለዋል አቶ መንግስቱ፡፡

15 Feb, 2017 By ሻሂዳ ሁሴን Ethiopian Reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy