Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያሰበውን ያህል መጓዝ እንዳልቻለ ገለጸ

0 963

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሁሉም የባንክ የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበ፣ የገበያ ድርሻውም ከፍ እያለ ቢመጣም በተፈለገው የዕድገት ደረጃ ልክ እየተጓዘ አይደለም ሲሉ የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር ገለጹ፡፡

የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አበራ ቶላ ይህንን የገለጹት፣ የባንኩ ‹‹የወጪ ንግድ ቀን›› በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ወቅት ነው፡፡ የባንኩ ዕቅድ አሁን ከተመዘገበው ዕድገት በላይ መሆን ነበረበት ያሉት አቶ አበራ፣ ይሁንና ውጫዊ ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ ዕድገቱን ለመጨር ወይም በፍጥነት ለመሮጥ አላስቻለውም ብለዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ፖሊሲዎችና አሠራሮች እንደተፈለገው ባንኩን ለማራመድና ከደንበኞች ጋር ሆኖ የአገር ኢኮኖሚን ይበልጥ ከመደጎም ባሻገር አሁን ባለው ዕድገት ላይ ለመጨመር ያላስቻለ አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች በሒደት ሊፈቱ የሚችሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበራ፣  በተለይ ራሳችን በምናመጣቸው ፈጠራዎች ሊለወጡ ይችላሉ በማለት እየሠሩ ስለመሆኑና አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን ባንኩ የደረሰበት ደረጃ ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖሊሲ ባለቤት የሆነው መንግሥት በፍጥነት ከመጓዝ የሚያደናቅፉ ጉዳዮችን በመመልከት ያሻሽላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የግል ዘርፉ ለአገር አለኝታ ሆኖ እንዲቀጥል ማንኛውንም ነገር ወደፊት ሊያራምድ የሚችል አቅም እንዳለውና ይህም እየሰረጸ እንዲሄድ የሚያስችል ዕድል መፍጠር ይገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሁላችንም ጉዞ የኤሊ የሚሆን ይመስለኛል ብለዋል፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን አደራጅቶ ባንኩን ለማቋቋም ሲነሱ ታሳቢ አድርገው የነበሩት በወቅቱ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍተት ነበር ያሉት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወልዴ ቡልቶ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ባንኮች ተደራሽነታቸው ውስን ስለነበር ይህንን ክፍተት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አስተዋጽኦ በማበርከት ድርሻውን መወጣት ይኖርበታል በማለት  የተጀመረው እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እያደገ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ አነስተኛና መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛ የቅርንጫፍ ተደራሽነት በቂ አለመሆን፣ ሦስተኛ በእምነታቸው ምክንያት በመደበኛ ባንክ አገልግሎት መጠቀም የማይፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለነበሩ እነሱንም ለመድረስ የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ለባንኩ መቋቋም መነሻ ነጥቦች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ይህንንም ለማመልከት ባንኩ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ዘርዝረዋል፡፡

ባንኩ እንደ ስኬት ከሚቆጥራቸው ተግባራቱ አንዱ በቅርንጫፍ ማስፋፋት ሥራ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ሥራ ሲገባ በመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት 26 ቅርንጫፎችን ይዞ ነው፡፡ ይህ የተለየ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከ26ቱ ቅርንጫፎች አምስቱን ብቻ በአዲስ አበባ 21ን ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ብዙም የባንክ አገልግሎት ባልነበረባቸው የክልል ከተሞች መሆኑ በተለየ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ይኼ እንቅስቃሴና በመጀመርያው የሥራ ዓመት 26 ቅርንጫፍ መክፈቱን ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ መንገድ ቅርንጫፍ ወደ ማበራከት እንዲገፋ ያደረገና የባንክ ተደራሽነት የበለጠ እንዲሆን ማድረግ ችለናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ስኬት የምናየውም ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባንኩ ቅርንጫፎች 211 ደርሰዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የቅርንጫፍ ቁጥሩን ስትራቴጂክ ዕቅድ መንደፉንም አመልክተዋል፡፡

ሌላው የባንኩ ስኬት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ከሁሉም ቀድሞ መጀመሩ ነው ተብሏል፡፡ በሌሎች ባንኮች ያልተሞከሩ አዳዲስ አገልግሎት መጀመርም የባንኩ መለያ መሆኑን በመግለጽ፣ በዕለቱ ለዕውቅናና ለሽልማት የተጋበዙ ደንበኞቻቸው አብረዋቸው ቢጓዙ የበለጠ ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡

በባንኩ እንቅስቃሴና ዕቅዶች ዙሪያ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖም ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የተጣራ ትርፍ 248.3 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ ተከታታይ የትርፍ መጠን ዕድገት የባንኩን ጤናማ አካሄድ ያመላክታል ተብሏል፡፡

ባንኩ ሐሙስ፣ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጪ ንግድ የዋንጫና የምሥጋና ምስክር ወረቀት ያበረከተላቸው ደንበኞቹ 22 ናቸው፡፡ በአራት ዘርፎች የተመደቡት ተሸላሚዎች የባንኩ ተበዳሪ፣ ላኪዎች፣ ከባንኩ ብድር ሳይወስዱ የወጪ ንግድ የባንክ አገልግሎትን ሲጠቀሙ የቆዩ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ላኪዎችና ለላኪዎች ፋይናንስ የሚደረግ ከፍተኛ ገንዘብ አስቀማጮች በሚሉ ምድቦች ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy