Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከኃላፊነት የሚነሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መብትና ጥቅማጥቅም የሚወስነው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

0 2,076

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅማጥቅሞች ለመወሰን የወጣው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ።

በረቂቅ አዋጁ የመንግሥት መሪዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች መብትና ጥቅማጥቅም የሚገባቸው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሆኑ ተቀምጧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ከኃላፊነት የሚነሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን መብትና ጥቅማጥቅም ለማስከበር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 653/2001 ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

በዚሁ መሰረት፤ ረቂቅ አዋጅ 8/2009 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታና ምርመራ በዋናነት ለበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም በተባባሪነት ለሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቶ ነበር።

ቋሚ ኮሜቴዎቹም በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ መሰረት በረቂቅ አዋጁ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባልደረቦች ጋር ጭምር ዝርዝር ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በተወሰኑ የአዋጁ ክፍሎች ላይ ብቻ መጠነኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም በመንግሥት በጀት ላይ የተለየ ተጽዕኖ የማይፈጥር መሆኑን ቋሚ ኮሚቴዎቹ አረጋግጠዋል።

በዚህም ከኃላፊነታቸው ለተነሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተፈቀደው የመኖሪያ ቤት አገልግሎት ሁለት የምርጫ ዘመን ወይንም ከዚያ በላይ ላገለገሉ የምክር ቤት አባላት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተደንግጓል።

አንድ የምርጫ ዘመንና ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎት፤ በህመም፣ በአካል ጉዳት ወይንም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ ለራሱና ለቤተሰቦቹ ኪራይ እየከፈለ የሚኖርበት ቤት ይሰጠዋል ተብሏል።

ከኃላፊነት የተነሳ የቀድሞ የምክር ቤት አባል ቀድሞ በነበረበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት በአዋጁ አንቀጽ 9 መሰረት መመደብ ካልቻለ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ክፍት የሥራ ቦታ ተመድቦ እንዲሰራም እንዲሁ።

ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከኃላፊነት ተነስቶ ጥቅሞችን ከማግኘቱ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ሊከፈለው የሚገባው የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንበት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤት አበልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለቤተሰቡ እንዲሰጥም ተፈቅዷል።

ማሻሻያው ሌሎች ጉዳዮችንም ያሻሻለ ሲሆን፥ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አንዲወጡ ያስችላል ነው የተባለው።
ተሿሚዎች ከኃላፊነታችን ከተነሳን በኋላ ምን እንሆናለን ከሚል ስጋት ለማላቀቅ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

ወደ መንግሥት የሥራ ኃላፊነት የሚመጡ አዳዲስ ግለሰቦችን ከማበረታታት በዘለለ በመንግሥት ተቋማት ያለውን የአሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የማጎልበት ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ነው የተነገረው።

የቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሥራ ኃላፊዎች ከሥራቸው ከተሰናበቱ በኋላም ያካበቱትን ልምድና እውቀት ለአገር ልማት ለማዋል የሚያስችል መሆኑ ላይም ስምምነት ተደርሶበታል።

በዚሁ መሰረት የበጀትና ፋይናንስ እንዲሁም የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ በመሆን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴዎቹ የቀረበውን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy