Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመድሃኒት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኃላፊነታቸውን ለቀቁ

0 978

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከመድሃኒት ግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በዋና ኦዲተርና በህዝብ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው የመድሃኒት ግዥና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስራቸውን በፍቃዳቸው መልቀቃቸው ተገለጸ። የመንግስት ወጪና አስተዳደር  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥፋት ያለባቸው የኤጀንሲው ሃላፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለአፈጉባዔው ደብዳቤ መጻፉን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል።የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀነ ለአዲስ ዘመን ብቻ እንደገለጹት፤ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መስቀሌ ሌራ ስራቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለቀዋል። በምትካቸውም ሰው ለማስቀመጥም ኮሚቴ ተቋቁሞ 16 ሰዎችን በማወዳደር የመጨረሻው ሰው ተለይቶ ውሳኔው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል።ሚኒስቴሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረባቸው ግለሰብም ተቀባይነት ማግኘታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ይፍሩ፤ የዳይሬክተሩ ሹመት በተያዘው ሳምንት ይፋ እንደሚደረግና ስራም እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪና አስተዳደር  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥፋት ያለባቸው የኤጀንሲው ኃላፊዎች በሙሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለአፈጉባዔው ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል።የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ለአዲስ ዘመን እንደገለጹትም፤  እርሳቸው የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴና የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በጋራ በመሆን ባደረጉት ማጣራት፤ የኤጀንሲው የመንግስት ሀብት አያያዝና አሰራር ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን አረጋግጠዋል። በመሆኑም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ሲባልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኤጀንሲው እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ችግሮቹ ተገምግመው ትክክለኛ ስለመሆናቸው መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።እንደ አምባሳደር መስፍን ማብራሪያም፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ኤጀንሲው በተለዩት ችግሮች ላይ የህግ ጥሰት የፈጸሙ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ ችግሮቹንም ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ እንዲፈቱና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ የመዋቅር ማሻሻያና አሰራርም እንዲዘረጋ ቋሚ ኮሚቴዎቹ  አቅጣጫ አስቀምጠዋል።ዋናው ኦዲተር በኤጀንሲው ላይ ባከናወናቸውና በደረሰባቸው የተለያዩ የኦዲት ግኝቶቹ ላይ በመመርኮዝም መወሰድ ያለበት እርምጃ እንዲወሰድ የመጨረሻ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለምክር ቤቱ አፈጉባዔ ከ15 ቀናት በፊት ደብዳቤ መጻፉቸውን ያስታወሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ አፈጉባዔውም ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ያለውን ችግር እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብረሃነ በኤጀንሲው ችግሮች ዙሪያ ለምክር ቤቱ ቀርበው ምላሽ መስጠታቸውን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኤጀንሲው ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑንና በአገሪቱ መድሃኒት በሚፈለገው ደረጃ እንደማይቀርብ፣ በተለይም የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መድሃኒት በአግባቡ እንደማይደርሳቸው፣ በእቅድ የተመሰረተ ግዥ እንደሌለ፣ ወደ አገር ውስጥ መግባት የሌለባቸው መድሃኒቶች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውና በጊዜ መወገድ ያለባቸው እንደማይወገዱ ማመናቸውን ተናግረዋል።የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም ብቻ በመድኃኒት ግዥና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መጋዘኖች ውስጥ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሳያልፍ ለጤና ተቋማት መሰራጨት የነበረባቸው ነገር ግን ያልተሰራጩ 569 ሚሊዮን 833 ሺ 919 ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች መገኘታቸውን ሪፖርት ማቅረቡ አይዘነጋም።በታህሣሥ 2009 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የኦዲት ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት፤  ኤጀንሲው በውስጥ ጨረታ፣ በቀጥታ ግዥና በዋጋ ማቅረቢያ በድምሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ መፈጸሙን፤ ነገር ግን የግዥው ሂደትና አጠቃላይ ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነ ተገልጿል።ኤጀንሲው የግዥ አፈጻጸም መስፈርትን ሳያዘጋጅ የ16 ሚሊዮን 863 ሺ 333 ብር ግዥ መፈጸሙንም ዋናው ኦዲተር በሪፖርቱ አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ኤጀንሲው ማቅረብ ሲገባው አለማቅረቡን መገለጹንና ይህንኑም በተከታታይ ዘገባ ማቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy