NEWS

ሀገሪቱ የምትከተለውን ስርዓት መረዳት ለተሻለ የመገናኛ ብዙሃን ስራ መሰረት ነው – ዶ/ር ደብረፂዮን

By Admin

February 06, 2017

ሀገሪቱ የምትከተለውን ስርዓት ከምትመራበት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ጋር አጣምሮ ማወቅ ለተሻለ የመገናኛ ብዙሃን ስራ መሰረት መሆኑን የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ተናግረዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአጠቃላይ ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው ሚኒስትሩ ይህን ያሉት።

ዶክተር ደብረፂዮን “ኢትዮጵያ ለምን የልማታዊ ዴሞክራሲ መስመርን መከተል ወደድች” በሚል ርእስ በመድረኩ ላይ ለተገኙ ጋዜጠኞች የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

በመነሻ ጽሁፉም ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የተሻለ አማራጭ ያደረገችው የልማታዊ መስመር ላይ ዴሞክራሲን ጨምራበት በዚሁ መስመር መመራትን ነው ብለዋል።

ይሄኛውን መንገድ የሚከተል መንግስት ሶስት ባህርያትን የተላበሰ ነው ሲሉም ዶክተር ደብረፂዮን አብራርተዋል።

እነዚህም ልማትን ህልውና አድርጎ መውሰድ፣ ከባለሀብቱ ጋር የተነጻጸረ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት እንዲኖር ማድረግ እና ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነት እንዲኖረው ማስቻል ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም በሶስቱ የልማታዊ መንግስታት ባህሪ ሲለካ፥ ዜጎች መላ ትኩረታቸው ልማት ከሆነ 14 ዓመታት መቆጠሩን ነው በማሳያነት ያቀረቡት።

በተመረጠ እና በተጠና መንገድ የገበያ ጉድለትን የመሙላት ነፃነት የሰጠ ሰርዓትን የሚከተለው መንግስት የሚያስተዳድረው የበዛ ሀብት፣ ባለስልጣናቱም የሚያዙበት ገንዘብ አለው፤ ከዚህ የመነጩት ፈተናዎችም አሉበት ብለዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ደቡብ ኮርያውያን ከተመፅዋችነት ወጥተው ሀገራትን በቋሚነት እስከመደገፍ የደረሱት የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነትን ማምጣት የቻሉ መገናኛ ብዙሃን ስለነበራቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶክተር ደብረፂዮን በመድረኩ ላይ ለተሳተፉ አካላት ኢትዮጵያ ህዝብን ከድህነት ለማውጣት የሚተጋ መገናኛ ብዙሃን ያሻታል ብለዋል።