NEWS

ለመምህራን በዝቅተኛ ኪራይ የሚተላለፉ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ይፋ ሆነ

By Admin

February 23, 2017

ለመምህራን በዝቅተኛ ኪራይ የሚተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ ይፋ ሆነ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኤጀንሲ፥ ለመምህራኑ በኪራይ የሚተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ኪራይ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት ስቱዲዮ 353 ብር፣ ባለ 1 መኝታ ቤት 671 ብር እንዲሁም ባለ 2 መኝታ ቤት ደግሞ 871 ብር እንዲሆኑ ተወስኗል።

ቤቶቹ በተጠቀሰው ዋጋ መሰረት፥ በቤት ዕጣው ተጣርተው ዕጣው ይገባቸዋል ተብለው ከተለዩ 16 ሺህ 798 መምህራን መካከል የፊታችን እሁድ ዕጣ ለሚወጣላቸው 5 ሺህ መምህራን የሚከራዩ ይሆናል።

ቤቶቹ መምህራኑ ባላቸው ቤተሰብ ብዛት ልክ እንደሚከራዩ፥ የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት ተናግረዋል።

እስከ 2 ቤተሰብ ያላቸው መምህራን ስቱዲዮ ሲከራዩ፥ እስከ 3 ቤተሰብ ያላቸው ደግሞ ባለ 1 መኝታ ቤት መከራየት ይችላሉ።

5 እና ከዚያ በላይ ቤተሰብ ያለቸው መምህራን ደግሞ ባለ 2 መኝታ ቤት እንደሚከራዩም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ለመምህራን የወጣው ዕጣ አገልግሎትን መሰረት ያደረገም ነው ተብሏል።

ከ1 እስከ 5 አመት፣ ከ6 እስከ አስራ አምስት አመት እና አስራ ስድስት አመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ በሚል በአገልግሎት ዘመናቸው መሰረት ተመድበዋል።

በተጨማሪም በኪራይ የሚተላለፉት ቤቶች መምህራኑ በመምህርነት ሙያ እስካሉ ድረስ እንደሚገለገሉባቸው የሚያመለክተውን ጨምሮ ሙሉ መመሪያም ተዘጋጅቷል።

በዕጣው የተካተቱት መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራሮች፣ የቴክኒክ እና ሙያ አሰልጣኞችን ጨምሮ ሱፐርቫይዘሮች ናቸው።