NEWS

አየር መንገዱ ሶስተኛውን ኤር ባስ ኤ350 አውሮፕላን ተረከበ

By Admin

February 01, 2017

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሶስተኛውን ኤር ባስ ኤ350 አውሮፕላንን በዛሬው እለት መረከቡን አስታወቀ።

አዲሱ ኤር ባስ ኤ350 አውሮፕላን “ኤርታሌ” የሚል ስያሜ እንደተሰጠውም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የርክክብ ስነ ስርዓቱ አውሮፕላኑ በተገጣጠመባት እና ሙከራ በተደረገባት የፈረንሳይ ቱሉዝ ከተማ ተከናውኗል።

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ሁለት ኤርባስ ኤ350 አውሮፕላኖችን የተቀበለ ሲሆን፥ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350 ኤክስ ደብሊው ቢ አውሮፕላን በ2008 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ መረከቡ ይታወሳል።

በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኤር ባስ ኤ350 ኤክስ ደብሊው ቢ ”ሰሜን ተራሮች” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለተኛውን ኤር ባስ ኤ350 ኤክስ ደብሊው ቢ አውሮፕላን ደግሞ በሀምሌ ወር 2008 ዓ.ም መረከቡ አይዘነጋም።

አውሮፕላኖቹም ከአዲስ አበባ ሌጎስ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዱባይ ለሚደረጉ በረራዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።

የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 14 ኤር ባስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787 አውሮፕላኖችን ከአራት ዓመታት በፊት በማስገባት ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ነው።

በሙለታ መንገሻ