NEWS

ከሶስት የመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተነሱ አርሶ አደሮች ካሳ እንዳልተከፈላቸው የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ገለፀ

By Admin

February 02, 2017

ከሶስት የመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች   የተነሱ  አርሶ  አደሮች ካሳ እንዳልተከፈላቸው የህዝብ እምባ ጠባቂ  ተቋም ገለፀ።

የህዝብ እምባ ጠባቂ   ተቋም ቁጥራቸው የበዛ አርሶ አደሮች   ካሳ አንዳልተከፈላቸውና፣ ምትክ ቦታ እንዳልተሰጣቸው የገለፀው በአርሾ ዴዴሳና የጣና በለስ  ስኳር  ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም  በጊቤ   ሶስት የኃይል  ማመንጫ ፕሮጀክት  ተነሺ  የሆኑትን ነው።

ተቋሙ በሶስቱ  ፕሮጀክቶች  በአርሶ  አደሮች  የቀረቡ   ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ያቀረበውን   ሪፖርት  ይፋ  አድርጓል።

ችግሩ  በተፈጠረባቸው አካባቢዎች  ላይ  ያሉ  አርሶ አደሮችም  የከፋ ችግር ውስጥ  መሆናቸውን ማርጋገጡንም ገለጿል።

ከመኖሪያ ቦታቸው ተነስተው ምትክ የእርሻ ቦታ  የተሰጣቸው  አርሶ  አደሮችም ቢሆን አዲሱ  ቦታቸው ከበፊቱ  ጋር የማይመጣጠንና ለእርሻ  እንደማይሆን ማረጋገጡንም በሪፖርቱ  አመልክቷል።

የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ምርመራውን ባካሄደባቸው ቦታዎች የመሰረተ ልማት  ግንባታዎችና   ማህበራዊ ተቋም  ግንባታም  በበቂ  ሁኔታ  አልተሟሏም ብሏል።

በዚህ ምክንያት አርሶ  አደሮቹ   ለጤና ችግር ተጋልጠዋል፤ ትምህራታቸውን ያቋረጡ ህጻናት  መኖራቸው በሪፖርቱ ቀርቧል።

ችግሮቹ በአፋጣኝ በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሊሰጣቸው  ይገባል ብሏል በመፍትሄው ጥቆማው ።

እንደ ስካር  ኮርፖሬሽን ፣ ውሃ  ፣መስኖና ኤሌክትሪክ  ሚኒስቴርና  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል   ያሉ   የሚመለከታቸው ተቋማትም  ችግሩ  መፈጠሩን  አመነዋል። ችግሩን ለመፍታትም  እንቅስቃሴ  መጀመመራቸውን  ተናገርዋል።

ሪፖተር ፥ ሰመረ ምሩፅ