– በአገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት አነስተኛ ተፅዕኖ አሳድሮበታል
– ከውጭ አየር መንገዶች የሚገጥመው ፉክክር አሳሳቢ ሆኗል
ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ. 2015 እስከ 2016 በጀት ዓመት የተጣራ ስድስት ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ ፈስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የገጠሙትን የተለያዩ ፈተናዎች ተቋቁሞ በ70 ዓመት ታሪኩ ትልቁን ገቢና ትርፍ ማግኘት ችሏል፡፡
ሰኔ 2008 ዓ.ም. በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አየር መንገዱ 55 ቢሊዮን ብር ገቢና ስድስት ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ የአየር መንገዱ ገቢ ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር በ10.3 በመቶ ያደገ መሆኑ፣ የተጣራ ትርፉ ደግሞ በ70 በመቶ ማደጉ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ አየር መንገዱ 7.6 ሚሊዮን መንገደኞችና 270,000 ቶን ጭነት አጓጉዟል፡፡ አየር መንገዱ ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል በነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት ነዳጅ አምራች የሆኑ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ በመጎዳቱ፣ ለአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ያለው ፍላጎት መቀነስ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለአየር መንገዱ ወጪ በመቆጠብ ረገድ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ገቢው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡
እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሱዳንና ግብፅ ያሉ ነዳጅ አምራች አገሮች በነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው በመጎዳቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በእነዚህ አገሮች የአየር ቲኬት ሽያጩ ተቀዛቅዞበታል፡፡
ከነዳጅ ዋጋ ጋር ተያይዞ ሌላው የተከሰተው ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ነዳጅ አምራች አገሮች በገጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አየር መንገዶች በእነዚህ አገሮች ያከናወኑትን ሽያጭ ወደ ራሳቸው ማስተላለፍ አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዋነኛነት በናይጄሪያ፣ በአንጎላ፣ በሱዳንና በግብፅ በየአገሮቹ ገንዘብ የሸጠውን 220 ሚሊዮን ዶላር ወደ አገሩ ማስተላለፍ አልቻለም፡፡ ‹‹ከ70 በመቶ በላይ ግዢያችን በአሜሪካ ዶላር የሚፈጸም በመሆኑ፣ ከ220 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከአንድ ዓመት በላይ ተይዞብን በመቆየቱ በገንዘብ ዝውውራችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል፤›› ብለዋል አቶ ተወልደ፡፡
ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር 18 የአፍሪካ አገሮች 1.4 ቢሊዮን ዶላር የተለያዩ አየር መንገዶችን ገንዘብ አግተው መያዛቸውን አስታውቋል፡፡ ናይጄሪያ 339 ሚሊዮን፣ ግብፅ 310 ሚሊዮን፣ አንጎላ 190 ሚሊዮን፣ ሱዳን 250 ሚሊዮን፣ አልጄሪያ 125 ሚሊዮን ዶላር መያዛቸውን ማኅበሩ አስረድቷል፡፡
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ዳይሬክተር አሌክሳንደር ጁኒያክ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ የአፍሪካ መንግሥታት የያዙትን የተለያዩ አየር መንገዶች ገንዘብ እንዲለቁ ግፊት በማድረግ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበርም በበኩሉ ገንዘቡ እንዲለቀቅ ከአፍሪካ መንግሥታት ጋር በመምከር ላይ ነው፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አለመረጋጋት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አቶ ተወልደ ግን የተከሰተው አለመረጋጋት በአየር መንገዱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳላሳደረ ነው የገለጹት፡፡
‹‹የምንነጋገረው ስለ 2015-2016 በጀት ዓመት ነው፡፡ በጀት ዓመቱ የተዘጋው በሰኔ 2016 በመሆኑ አለመረጋጋቱ በገቢያችን ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ በአዲሱ በጀት ግን አነስተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ከመንገደኛ ፍሰት ውስጥ 70 በመቶ በላይ መንገደኞቻችን ትራንዚት የሚያደርጉ (በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ) በመሆኑ አለመረጋጋቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ አላደረሰብንም፡፡ ሆኖም በአዲሱ በጀት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡ መንገደኞች ላይ አነስተኛ የቁጥር መቀነስ ተመልክተናል፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ፈተና ከውጭ አየር መንገዶች የሚገጥመው ፉክክር በእጅጉ እየተጠናከረ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ ከቱርክ አየር መንገድና ከመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ አየር መንገዶች የሚገጥመው ፉክክር ታይቶ በማይታወቅ መጠን መጠናከሩን አቶ ተወልደ አስረድተዋል፡፡
‹‹የዋጋ ጦርነት ውስጥ ገብተናል፡፡ አንዳንዴ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ አመርቂ የፋይናንስ ውጤት ማግኘቱ መላው የአየር መንገዱን ሠራተኛ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሠራተኛው ጥንካሬ፣ የማኔጅመንቱና የቦርዱ ብልህ አመራር ለአየር መንገዱ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ታኅሳስ ወር የዓለም አቀፉ አየር ትራንስፖርት ማኅበር ይፋ ያደረገው መረጃ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 800 ሚሊዮን ዶላር መክሰራቸውን ያሳያል፡፡
የአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ታዋቂ አማካሪ የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስመዘገበውን ውጤት አድንቀዋል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በማማከር ላይ የሚገኙት አቶ ዘመዴነህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስመዘገበው ትርፍ ‹‹አስገራሚ›› ነው፡፡
‹‹በቀደም ዕለት የናይጄሪያ መንግሥት አሪክ ኤር የተባለውን የናይጄሪያ የግል አየር መንገድ ከአቅም በላይ በሆነ የዕዳ ክምችት ምክንያት ተረክቦታል፡፡ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ኪሳራ ማስመዝገብ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦርድ ሊቀመንበሩን ቢለዋውጡም ለውጥ ማምጣት ተስኗቸዋል፡፡ የኬንያ አየር መንገድ ላለፉት ሦስት ዓመታት ኪሳራ ሲያስመዘግብ ቆይቷል፡፡ ሁለቱ አየር መንገዶች እየተንገታገቱ ያሉት መንግሥቶቻቸው በየዓመቱ በሚያደርጉላቸው ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተቃራኒው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንደሆነ አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል፡፡ እንደ ድሪምላይነርና ኤርባስ ኤ350 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛትና የመዳረሻ አድማሱን በማስፋት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለው አየር መንገዱን በሚገባ የሚመራ ብቃት ያለው ማኔጅመንት በመኖሩ ነው፡፡ በአግባቡ የሠለጠነ አቅም ያለው ሠራተኛ ስላለው፣ ይህን የሠለጠነ የሰው ኃይል አስተባብሮ የሚመራ ቁርጠኛ ማኔጅመንት በመኖሩ ነው፡፡ ማኔጅመንቱ ግልጽ የሆነ ራዕይ አስቀምጦ ያንን ለማሳካት የሚተጋ ነው፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ መንግሥት በአየር መንገዱ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ ለማኔጅመንቱ ነፃነት መስጠቱ ለአየር መንገዱ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ በአፍሪካ የተለመደ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንግሥት ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የሚመራው በዓለም አቀፍ ንግድ መርሆዎች ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 82 አማካይ ዕድሜያቸው አምስት ዓመት የሆኑ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን፣ 20 የአገር ውስጥና 94 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡ በየዓመቱ እያደገ የመጣው የሠራተኞቹ ቁጥር 12,000 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር