Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግመል የሰልፍ ጉዞ ዓመታዊ ፌስቲቫል ሊሆን ነው

0 1,420

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአፋር ግመሎች አሞሌ ጨው በመጫን ተሰልፈው ከቦታ ወደ ቦታ የሚደርጉት ጉዞ /ቅፍለት/ ዓመታዊ ፌስቲቫል እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዕለታዊ የጉዞ ትዕይንቱ የቱሪስት መስህብ ያለው በመሆኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል።

በአፋር በረሃማዋ ምድር ዳሎል ብዙ ግመሎች በአንድ ቀጭን መስመር አሞሌ ጨው ጭነው ይጓዛሉ።

እንዲህ አይነቱ ጉዞ ቅፍለት በመባል ይታወቃል።

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የኒም ፕሮሞሽን የመጀመሪያውን ዙር የግመል ቅፍለት ፌስቲቫል በክልሉ በርሐሌ ወረዳ አመዳሌ ቀበሌ በስኬታማ ሁኔታ አካሂዷል።

የፕሮሞሽኑ ባለቤት ወይዘሮ ኒም ሐጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት በቀጣይም ፌስቲቫሉን በየዓመቱ ለማከናወን አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል።

”ፌስቲቫሉን ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ ግመል ለሶስት ሺህ ዓመታት የሰውን ልጅ ሲያገለግል የቆየ እንስሳና ባለውለታ በመሆኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

”ለዚህ ዘመናትን ለተሻገረ ረጅም አገልግሎት ግመልን ልናመስግን ይገባናልም” ብለዋል።

ግመል ሥጋና ወተቱ ለምግብነት ከመጥቀሙ ባሻገር አርብቶ አደሩ ለጭነት ማጓጓዣ ስለሚገለገልበት ጥቅሙ የበዛ ነው።

ፌስቲቫሉ ግመል ለሰው ልጅ ላደረገው ጥቅም የሚመሰገንበት ሲሆን የቱሪስት ፍሰቱም እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ ዓመታዊ ፌስቲቫል ከማዘጋጀት ባሻገር ግመሎች በስፋት አገልግሎት በሚሰጡበት አካባቢዎች ተመሳሳይ ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ግመል “የበረሐ መርከብ” የሚል መገለጫ ቢኖረውም እስካሁን ጥቅሙና አገልግሎቱን በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች አናሳ ናቸው ብለዋል።

ፕሮሞሽኑ የግመል ቆዳን ጥቅም ላይ የማዋል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥናት የማካሄድ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ያዮ በበኩላቸው የግመል ቅፍለት በአፋር ክልል ከጥንት ጀምሮ እስካሁን የቀጠለ የጨው ንግድ ዕለታዊ ትዕይንት ነው ብለዋል።

ይህንኑ የግመሎች ትዕይንት ዓመታዊ ፌስቲቫል የማድረግ ዕቅድ በክልል ደረጃ እንዳለ ጠቁመው ትዕይንቱ  የቱሪስት መስህብ በመሆኑ አመቺ ጊዜ ተለይቶለት ወደፊት ፌስቲቫሉን የማዘጋጀት ሐሳብ መኖሩን ጠቁመዋል።

ጉዞው የሲራራ ንግድን የሚያስታውስና የበረሃ ተጓዦቹ እንዴት እቃ ጭነው ረጅም ርቀት ይጓዙ እንደነበር በትዝታ መልሶ የሚያስቃኝ ሲሆን በጥቅሉ ጎብኚዎች ከዘመናት በፊት የነበረውን ግዙፍ የአጋሰሶች ጉዞ ኋልዮሽ የሚያዩበት ትዕይንት እንደሆነ ይጠቀሳል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy