NEWS

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አዲስ አበባ ገቡ

By Admin

February 23, 2017

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሶስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈራረሙም ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥቅምት ወር በጁባ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ ከፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረው ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

ሁለቱ ሃገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር፣ በሠላምና ፀጥታ፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም የጋራ ጥቅሞችን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል።