121ኛ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ዝግጅት መጠናቀቁን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ገለፀ
የካቲት 17፣ 2009
የፊታችን የካቲት 23 ለ121ኛ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ የሚከበረው የአድዋ የድል በዓል አከባበር ዝግጅት መጠናቀቁን የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
በዓሉ በዋናነት የታሪክ በተከወነበት አድዋ ከተማ ላይ በተለያዩ ዝግጅት በድምቀት እንደሚከበር በሚንስቴሩ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዘሃኝ አባተ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡
በዓሉ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የውጭ ሀገር ቱሪስቶችና የሀገሪቱ ዜጎች በበዓሉ ላይ ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡
ከየካቲት 23 በፊትም በዓሉን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የጥያቂና መልስ ውድድር፣ በብሔራዊ ሙዚየም የስዕል አውደ-ርዕይ፣ በብሔራዊ ትያትር የሙዚቃ ዝግጅት እና በኦሮሚያ ባህል ማዕከል የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
በዓሉን ለመዘከር በየዓመቱ የእግር ጉዞ የሚያደረጉ ሰዎች በቀኑ አደዋ ከተማ ይደርሳሉ፤ በመዲናዋም የአደባባይ ትርኢትን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ተመልክቷል፡፡
በዓሉ ህዝቡ በልማቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡