ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በመገልገል ከቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የተለያዩ ቅርንጫፎች የደንበኞችን ሲፒዮ በመጠቀም ከ3 ሚሊየን ብር በላይ አጭበርብረዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦች ከ10 እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
ተከሳሾቹ የባንኩ የመልዕክት ሰራተኛ የነበረው ፍጹም ደረጀ እንዲሁም ሄኖክ ደመቀ እና ዳዊት ፈለቀ የተባሉ በግል ስራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ናቸው።የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ ቤተሰባዊ ትስስራቸውን በመጠቀም በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት የተለያዩ ደንበኞችን ሲፒዮ ሰርቆ በማውጣትና ሃሰተኛ መታወቂያ አዘጋጅቶ በመጠቀም ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የደንበኞች ብርን ለግል ጥቅም አውለዋል።
ተከሳሾቹ አቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃን ማሰተባበል ባለመቻላቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ያላቸው ሲሆን፥ 1ኛ ተከሳሽን በ13 አመት ፅኑ እስራትና በ30 ሺህ ብር እና 3ኛ ተከሳሽ በ10 አመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
2ኛ ተከሳሸ ደግሞ በሁለት አመት ገደብና በ2 ሺህ ብር እንዲቀጣ ነው የወሰነው።
በግለሰቦቹ የባንክ ሂሳብ ውስጥ የሚገኝ ብር እና የ3ኛ ተከሳሽ ሶስት የቤት መኪናዎች እንዲወረሱም ወስኗል።