አገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከ16 የሚበልጡ የድርቅ ወቅቶችን አስተናግዳለች ። “ ኤልኒኖ ’’ ተብሎ በሚጠራው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ባለፈው ዓመት ያጋጠመን የድርቅ አደጋ ግን ከሁሉም የከፋ ነበር ።
10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ያጠቃው ድርቅ ወደ ረሃብና ሞት እንዳይሸጋገር ለማድረግ መንግስት ፣ ህዝብና የግል ባለሃብቶች እጅ ለእጅ ተያይዘው መክተውታል ። በድርቁ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት እንዳይጠፋ ማድረግም ተችሏል ።
የአምናው ድርቅ እንደ ሌሎች ድርቆች ሁሉ በሚፈለገው መጠን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ የተቸረው አልነበረም ። ለድጋፉ አለመገኘት ሁለት ምክንያቶች ነበሩ ። አንዱ ላለፉት 12 ዓመታት ተከታታይ እድገት ማስመዝገባችን ነው ። እድገቱ ካለ ድርቁም በራሳችሁ ተወጡት ዓይነት መሆኑ ነው ።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዓለማችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት ውጥንቅጧ ወጥቶ የተረጂ ቁጥር በእጅጉ የበዛበት ዓመት መሆኑ ነው ። የዓለም ማህበረሰብ ትኩረት የሳቡት ሶሪያና የመን የመሳሰሉ በጦርነትና በድርቅ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ነበሩ።
በመሆኑም ድርቁን የመመከት ቁልፍ ስራ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ላይ ወደቀ ። መንግስት የመሪነት ሚናውን በመውሰድ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብም ጭምር አስፈላጊውን ምላሽ ሰጥቷል ።
የተመደበው ከፍተኛ በጀት ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ያመነጨው ሀብት ነው ። ለልማት ቢውል ደግሞ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሊያስገነባ የሚችል መሆኑ እውነት ነው ።
ነገር ግን ድርቁ ሀብታችንን የበላ ቢሆንም ሀብት ግን አፍርተንበታል ። ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ድርቁን ለመቋቋም የተወሰደው እርምጃና የተገኘው መልካም ተሞክሮ ያስረዳሉ ።
ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የእለት ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 219 ወረዳዎችን ጨምሮ ለ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አስፈላጊውን ምላሽ በመስጠት አደጋውን መቋቋም ተችሏል ። በዚህም ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ችግር በውስጣዊ አቅሟ መቋቋም እንደምትችል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር አሳይታለች ይላሉ ።
ድርቁን ለመከላከል ሲባልም በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል ። ለዜጎች አልሚ ምግብ አምርተው የሚያቀርቡ 10 የማምረቻ ድርጅቶች ተፈጥረዋል ። የማምረቻ ድርጅቶቹ በቀን 7ሺህ 500 ኩንታል አልሚ ምግብ የማምረት አቅም አላቸው ።
ድርቁን የመከላከል ስራው ከወደብ ዕቃ የማንሳት አቅማችንን በእጅጉ አሳድጎታል ባይ ናቸው ። ከድርቁ በፊት ከጅቡቲ ወደብ ይነሳ የነበረው ዕቃ 7 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብቻ ነበር ። አሁን ግን ወደ 17 ሺህ 4009 ሜትሪክ ቶን አድጓል ። ምክንያቱ ደግሞ በአንድ በኩል የእለት ደራሽ እርዳታውን ቶሎ ለተረጂዎች ለማድረስ በሌላ በኩል ደግሞ በድርቁ ያጣነውን ምርት ለማካካስ የሚያስችል ማዳበሪያ ለተጠቃሚው ለማቅረብ የተደረገው ርብርብ ውጤት ነው ።
ሌላው ድርቁን በመከላከሉ ሂደት የተፈጠረው አቅም በመስኖ የእንስሳት መኖ የማምረት ተግባር ነው ። ይህ አሰራር በአገራችን የተለመደ አልነበረም ። አሁን ግን በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በ1ሺህ 400 ሔክታር መሬት የእንስሳት መኖ በመስኖ እየለማ ነው ።
የአዋሽ ወንዝ ፍሰትን ለማስቀጠልና ግድቦችን ለማጠናከርም ከሌሎች የውሃ አካላት በመጥለፍ የወንዙን መጠን ማሳደግ እንደተቻለ ኮሚሽነሩ ያስረዳሉ ።
ድርቁን በመቋቋም ሒደት ቀደም ሲል ግንባታቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ የመስኖ ተቋማት የሃይል አቅርቦት እንዲኖራቸውና አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ተደርጓል ።
የተፈጠረው አቅም ድርቁን ከመቋቋም ባሻገር ከዘላቂ ልማት ጋር እንዲቀናጅ መደረጉ ደግሞ ሰፊ ሀብት ከበላው ድርቅ ሀብት ማፍራት የቻልንበት መልካም አጋጣሚ ጭምር አድርገን ተጠቅመንበታል ።
አደጋውን መቋቋም ከቻልንባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የመንግስት የመሪነት ሚና ጎልቶ መታየቱ ነው ።
ኮሚሽነሩ እንደሚሉት ብሄራዊና ክልላዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴዎች በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ተንቀሳቅሰዋል ። የተረጂ ብዛት ቀድሞ በመተንበይም በቂ ዝግጅት አድርጎ ቆይቷል ።
በእርዳታ አቅርቦት የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በተቀናጀና ወጥነት ባለው አግባብ መግባባት ፈጥሮ መምራት መቻሉንም ለስኬት አብቅቶታል ። መንግስት ማንንም ሳይጠብቅ በቂ ሀብት መድቦ ተገቢው ምላሽ መስጠት መቻሉን ስኬታማ አድርጎታል ።
ሁለተኛው የስኬት ምክንያት በመደበኛ የልማት ፕሮግራም የተገነቡ የግብርና ፣ የውሃ ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ለእርዳታ አቅርቦቱ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉ ነው ።
የህብረተሰቡና የግል ባላብቱ ተሳትፎም ቢሆን ሌላው የስኬት ምክንያት ነው ። ህዝብ ለህዝብና ክልል ለክልል ባሳዩት ታላቅ ወገናዊ የመደጋገፍ ተግባር የድርቅ አደጋው ከመቋቋም አንፃር አኩሪ ባህላችን ያጎለበተ ነበር ። የግል ባለሃብቱም ቢሆን አቅሙን የፈቀደውን ሁሉ ለወገኖቹ ድጋፍ ማበርከቱን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ይናገራሉ ።
ከአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጡ የእርጥበት ዕቀባ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ተግባራትም ተከናውነዋል ።
ከመጠነ ሰፊው ድርቅ የመከላከል ስራችን አደጋ መቋቋም የሚቻለው በዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ማእቀፍ ውስጥ መሆኑን ተምረንበታል ባይ ናቸው ።የውጭ እርዳታ ቢኖርም ባይኖርም ህብረተሰቡንና የግል ባለሃብቱን በማስተባበር በአገር ውስጥ አደጋ መቋቋም የሚቻልበት አቅም መፍጠር ችለናል ። የአደጋ ስጋት ቅነሳ ( Disaster Risk Reduction) ስራ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር ሊሰራ እንደሚገባም ተምረንበታል ይላሉ ።
የአምናውን ድርቅ በብቃት መቋቋም ብንችልም ዘንድሮም ቢሆን ከድርቅ ስጋት አልወጣንም ። በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ መዝነብ የተበረበት ዝናብ በአገባቡ ፣ በመጠንና በስርጭት ያልተስተካከለ በመሆኑ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወገኖች ለእለት ደራሽ እርዳታ ተጋልጠዋል ።
ድርቁ የእንስሳት መኖና ውሃ እጥረት በመፍጠር ፣ የእንስሳት ሞት በማስከተል ፣ የሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት በመፍጠር ፣ በህፃናትና በእናቶች ላይ የተመጣጠነ ምግብ ችግር በማስከተል ፣ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ በማስገደድና ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ከአካባቢ ወደ ሌላ ቦታ መፍለስ የመሳሰሉ ችግሮች አስከትሏል ።
የፌዴራልና የክልል መንግስታት የአምናውን ተሞክሮ በመቀመር የዘንድሮውን አደጋ ለመቋቋም እየተረባረቡ ቢሆንም የአርብቶ አደር አካባቢ ነባራዊ ሁኔታ ስራው ፈታኝ አድርጎታል ።
ከአምና ጋር ሲነፃፀር በ44 በመቶ የቀነሰው ለዘንድሮ የተረጂዎች ቁጥር የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ 948 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ በጥናት ተረጋግጧል ።
ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በሰጠው የ2009 ዓ.ም የበልግ ትንበያ መሰረት በአርብቶ አደር አካባቢዎች የበልግ ዝናቡ ከመደበኛ በታች ስለሚሆን አሁን ያለውን ችግር የበለጠ ያባብሰዋል ተብሎ ይጠበቃል ። የባለፈው ዓመት ድርቅ ተሻጋሪ አሉታዊ ተፅእኖ ደግሞ አደጋው እጅግ የከፋ ያደርገዋል ።
በአርብቶ አደሩ ላይ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ ( Back to Back) መሆኑና የማገገሚያ (Recovery) ምእራፍ ያሳጣው መሆኑ ዋናው መተዳደሪያው በሆነው የእንስሳት ሀብቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ተብሏል ።
ድርቁን መንግስት ፣ ህዝብና የግል ባለሃብቱ የአምናውን ተሞክሮ በማዳበር ለመከላከል አስፈላጊው ዝግጅት አድርገው ወደ ተግባር ገብተዋል ነው የተባለው ።የእርዳታ አቅርቦቱ እንዳለ ሆኖ በእንስሳት ላይ ሊደርስ የሚችለውን እልቂት ለመከላከልና ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶቷል ።
የመጠጥ ውሃን በቦቴ ከማቅረብ ይልቅ ዘላቂ ጠቀሜታ የሚሰጡ የውሃ ጉድጓዶች መቆፈር አንድ አማራጭ ተደርጎ ተወስዷል ። የእንስሳት መኖን በተመለከተ ደግሞ በአፋርና በሶማሊ ክልል የተጀመረው መኖን በመስኖ የማልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ።የግብርናና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርትን መጠቀምና እንስሳትን ግጦሽ ወዳለበት ቦታ ማንቀሳቀስም የመፍትሄው አካል ነው ።
እንስሳቱን ለገበያ ማቅረብ ሌላው አማራጭ ነው ። አርብቶ አደሩ የእንስሳት ሀብቱን ከመጎዳታቸው በፊት ለገበያ አውጥቶ በመሸጥ ጥሪት እንዲቋጥር ይፈለጋል ። የተዳከሙና ለገበያ መውጣት የማይችሉት ደግሞ መንግስት እየተረከበ እንዲታረዱና ስጋቸው በቋንጣ መልክ እየተዘጋጀ የእርዳታው አካል ሆኖ እንዲከፋፈል የማድረግ እቅድ ተይዟል ።
አርብቶ አደሩ የእንስሳት ቁጥር ከማብዛት ይልቅ ምርታማ የሆኑ ጥቂት ምርታማ ዝሪያዎች የመያዝ አማራጭ እንዲከተልም የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት ይሰጠዋል እየተባለ ነው ። ኮሚሽነሩ እንዳሉት 33 የኢትዮጵያ ላሞች በቀን የሚሰጡት የወተት ምርትና አንዲት የእስራኤል ላም የምትሰጠው ምርት ተመጣጣኝ ነው ።
33 ላሞችን ከመመገብና ከመንከባከብ ይልቅ አንዲት ምርጥ ዝሪያ ያላት ላም መያዝ አዋጪ ይሆናል ማለት ነው ። በሌላ አነጋገር የወተት ላሞች እርባታችን ከእስራኤል ጋር ሲነፃፀር በጥቅም 33 በመቶ ዝቅ ያለ በጉዳት ደግሞ 33 በመቶ የላቀ ነው ማለት ይቻላል ።
ድርቁንና ድርቁን ተከትለው የሚከናወኑ ስራዎችና የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል የወገኖቻችን ህይወት ለመታደግ የሚደረገው ርብርብ ለማሳካት ወቅታዊነቱን የጠበቀ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ወሳኝ መሆኑን ሁሉንም ወገኖች ያግባባል ።
ኮሚሽነሩ እንደሚሉት የአገራችን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የድርቁ መንስኤና ያስከተለው ጉዳት ፣ በድርቅና በረሃብ መካከል ያለው ልዩነት ፣ መንግስት ድርቁን ለመቋቋም እያደረገ ያለው ጥረት አስመልክተው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፣ጥልቅ ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ መስራት አለባቸው ።
ሚዲያዎች የህዝብ አንደበት ሆነው በማገልገል በእለት ደራሽ እርዳታ አቅርቦት ወቅት በሚፈለገው መጠን ፣ ወቅቱን ጠብቆና ያለምንም ብክነት፣ ስርቆትና አድሎአዊነት መሰራጨቱን በማረጋገጥ ችግር ካለ ደግሞ በማጋለጥ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ።
ኮሚሽነሩ የሰጡትን ሃሳብ የበለጠ የሚያጠናክሩት ደግሞ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ናቸው ።
ኢትዮጵያ አሁን ያጋጠማትን ድርቅና ለወደፊቱ ሊከሰቱ የሚችሉት ድርቆችን በብቃት ለመከላከልና ለመቋቋም ዘላቂ ልማትን አጠናክሮ መቀጠል ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ሚኒስትሩ ይገልፃሉ ።
የሀገራችን የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ መላው ህብረተሰብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለዘላቂ ልማት ለማነሳሳት በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ መመገብ እንደሚገባውም አሳስበዋል ።
ባለፈው ዓመት አጋጥሞ የነበረው ከፍተኛ ድርቅ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ በራስ አቅም መቋቋም የተቻለው ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ያመነጨው ሀብት በመጠቀም በመሆኑ ለዘላቂ ልማት ትኩረት መስጠት ተገቢና ትክክለኛ መንገድ ነው ብለው ያምናሉ ።
የድርቁ መጠን ዘንድሮ ቢቀንስም በኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የገለፁት ሚኒስትሩ መንግስትና ህዝብ ለድርቅ ተጎጂዎች ፈጣንና ትክክለኛ ምላሽ መስጠት እንዲችሉ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ በማቀበል ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ያሰምሩበታል ።
ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ እቅዶችና ግቦች ማሳካት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ለስትራተጂው ስኬታማነት መላው ህብረተሰብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በማነሳሳቱ ሒደት ከሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ብዙ ይጠበቃል ።
ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቋቋም የውስጥ አቅም ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ በአንድ በኩል ኢኮኖሚያዊ እድገታችንን አጠናክሮ ማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ ከእድገቱ ጋር አብሮ የሚጓዝ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስርዓት ለመገንባት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል ።
ድርቅ ከማጋጠሙ በፊት አስቀድሞ ለመዘጋጀትም ሆነ ሲከሰት ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት መረጃ አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ነገሬ ድርቅ ያጋጠማቸው ዜጎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፉ ወቅቱን ጠብቆ ትክክለኛ መረጃ የማቅረብ ዘመናዊ አሰራር መከተል አለበት ብለው ያምናሉ ።
የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት ደግሞ ድርቅን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው ጥረትና ለአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ስኬት ተገቢውን ሙያዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን ብለዋል ።
የኦሮሚያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ በሰጡት አስተያየት በአንድ በኩል የክልሉ ህዝብ ለዘላቂ ልማት በበጋ ወራት የሚያካሄደውን የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል በሌላ በኩል ደግሞ የእርዳታ ስርጭቱን በትክክል ለተጎጂው ህብረተሰብ መድረሱን ለማረጋገጥ ሚዲያው ተቀናጅቶ ለመስራት ተዘጋጅቷል ።
የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሰሙ ንጉስ ሸኖ በበኩላቸው በክልሉ በ47 የብሄር ብሄረሰብ ቋንቋዎች በሚያስተላልፉ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ህዝቡ ለዘላቂ ልማት የበለጠ እንዲነሳሳ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በማቅረብ ሙያዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።
በድርቅ የተጎዳው ህዝባችን በዘላቂነት መልሶ እንዲቋቋም በዋነኛ መፍትሔው የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂው በስኬት መፈፀም ነው ያሉት በአፋር ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከፍተኛ ዶክሜንተሪ አዘጋጅ ወይዘሪት ሐዋ ዓሉ ናቸው ።
በመሆኑም ህዝባችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለዘላቂ ልማት እንዲነሳሳ መረጃ በማቀበል ድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል ።
እንዲህ ነች ኢትዮጵያ ! ብራቮ መንግስታችንና ህዝባችን ! ሀብታችንን የበላው ድርቅ ዋናው ሀብት የሆነውን ህዝብ ከመታደግ አላደናቀፈንም ። ድርቅን በዘላቂነት ማድረቅ የሚያስችለን አቅም ፈጥረንበታል ። ድርቅ በዘላቂነት በአረንጓዴ ልማት ስራተጂያችን እስከ ወዲያኛው ይደርቃል ። የዓለም ማህበረሰብም ከፅናታችን ብዙ ይማራል ብለን እንጠብቃለን ።(ኢዜአ)