Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁሉም ፓርቲዎች በውይይታቸው ህዝብንና ሀገርን ማዕከል ያድርጉ ! (ዘአማን በላይ) ዘአማን በላይ

0 373

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰሞኑን በገዥው ፓርቲና 21 በመሆኑ በተቃዋሚዎች መካከል ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ለማካሄድ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። ይሁንና ገና ዋነኛው ጉዳይ ሳይጀመር ከወዲሁ የልዩነት ሃሳቦች እየታዩና ቀጠሮ ሊያዝባቸው የማይገቡ ጉዳዩችም የቀጠሮ አጀንዳ እየሆነ እየተመለከትን ነው። የሀገራችን አርሶ አደር “ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ቂጢጥ” እንደሚለው፤ ፍሬ ነገሩ ሳይጀመር መስፋት የማይገባቸው ሃሳቦች የጉዳዩ እምብርት ሆነው መታየታቸው ትክክል አይመስለኝም።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ገዥው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች ለመወያየት፣ ለመከራከርና ለመደራደር የፈለጉት ከበስተኋላቸው ያለውን ህዝብ በመወከል የሀገራቸውን ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ይበልጥ ለማጎልበት ነው። ታዲያ በዚህ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ላይ የሚደረገው ውይይት በመቻቻል፣ ሰጥቶ በመቀበልና የሀገርን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ መሆን ይኖርበታል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገሚሶቹ ከመንገስት ጋር በጋራ እንነጋገራለን ሲሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ‘የለም እኔ ለብቻዬ ከገዥው ፓርቲ ጋር እወያያለሁ’ የሚሉ ከሆነ፤ ገዥው ፓርቲም በበኩሉ የራሱን መስፈርት የሚያስቀምጥ ከሆነ የዚህ ሀገር ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በሚፈለገው ፍጥነትና መንገድ የሚሄድ መስሎ አይታየኝም።

በድርድር ወቅት አንዳንዴ ሁሉንም ወገን ሙሉ ለሙሉ ሊያስደስት የሚችል ነገር ላይኖር ይችላል። ሆኖም ሁሉም ተደራዳሪዎች ግማሽ መንገድ ድረስ መጥተው በመቻቻል መንፈስ ሊቀራረቡና ለውይይቱ የሚሆን ጥርጊያ መንገድ ሊያበጁ ይገባል። ግሪካዊው ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ ‘የእጅግ መጥፎውና የእጅግ ጥሩው ወርቃማው አማካይ መንገድ (Golden Mean) መሃል ላይ ያለው ነው’ እንዳለው ዓይነት ማለቴ ነው። ምናልባት በፓርቲዎች መካከል “መጥፎ” የሚባል አሊያም “ጥሩ” የተሰኘ መንገድ ካለ፤ ተወያይ ወገኖች ከሁለቱም ፅንፎች ወደ አማካዩ ነጥብ በመምጣት ሰጥቶ የመቀበልን ጥበብ መካን ይኖርባቸዋል። እርግጥ ይህ መንገድ ሁሉንም ወገኖች ላያስደስትና ከፍ ሲልም የራስን ሃሳብ በመተው ለሌላኛው የመገዛት መስዋዕትነትን ይጠይቅ ይሆናል። ሆኖም ለህዝብና ለሀገር ሲባል ይህን ዓይነቱ የመደራደርና የመወያየት መንገድን መከተል እጅግ አስፈላጊ ነው።

በእኔ እምነት ተወያይ ፓርቲዎች ይህን ማድረግ ተስኗቸው የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማስፈፀም የሚሹ ከሆነ፤ ለሀገራቸው ዴሞክራሲ ማበብና ለመድብለ ፓርቲ መጎልበት የሚጫወቱት ሚና ይኖራል ብዬ አላስብም። ‘ለምን?’ ካሉ፤ ዴሞክራሲ በመወያየት፣ በመቻቻልና ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አኳያ አንደኛው ለሌላኛው ሃሳብ ተገዥ የሚሆንበት አውድ እንጂ፤ “የግድ የእኔን ተቀበሉኝ” በሚል ግትር አቋም ሃሳብን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት መድረክ ባለመሆኑ ነው።

ርግጥ ሁለቱም ተወያይና ተደራዳሪ ወገኖች መገንዘብ የሚኖርባቸው ለውይይቱና ለድርድሩ አነሳሽ የሆነውን ምከንያት ነው። በእኔ እምነት ይህን አነሳሽ ምክንያት ያወቀ ማንኛውም ፓርቲ የችግሩን ግማሽ ለመቅረፍ እንደተዘጋጀ ይቆጠራል። ተወያዩቹም ይሁኑ ጉዳዩን ከዳር ሆነን በጥሞና የምንከታተለው ወገኖች እንደምናውቀው ለውይይቱና ለድርድሩ መነሻ የሆነው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለህዝብ ተወካዩችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባን በከፈቱበት ወቅት ያሰሙት ንግግር ነው።

ፕሬዚዳንቱ የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማበልፀግ መንግስት የሚከተለውን አቅጣጫ “…ሀገራችን በምትከተለው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርዓት በመመራት ባለፉት 25 ዓመታት በድምሩ ለአስር ጊዜ ሀገራዊ፣ ክልላዊና ከባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች የብዙ ፓርቲዎች ተሳትፎ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የህዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ በሀገራችን ወሳኙ የስልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወከሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል። በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጐት ያላቸው ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ስርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በህግ ማእቀፍ በተደገፈ አኳኋን የህዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል።…” በማለት መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብትና እንዲሰፋ ከገዥው ፓርቲ የተለየ ምልከታ ያላቸውና የህዝብን ድምፅ ከሚወክሉ ፓርቲዎች ጋር ከቀጣዩ ምርጫ በፊት መድረኮችን ማስፋት የሚገባ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ይህን ሃሳብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ሰሞኑን ለፓርላማው ‘በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ዴሞክራሲውን እንዲሰፋና እንዲጎለብት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየን ነው’ ሲሉም ደግመውታል። እንግዲህ ከእነዚህ አባባሎች መረዳት የሚቻለው፤ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች የሚደራደሩት ዴሞክራሲን ለማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዲጎለብት ለማድረግ እንጂ ሌላ መነሻ የሌለው መሆኑን ነው።

እናም በእኔ እምነት ለውይይቱ የተለያዩ “የዳቦ ስሞች” በመስጠትና ከወዲሁ ለጥርጣሬ የሚጋብዙ ጉዳዩችን በመከተል የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ልህቀት ማምጣት አይቻልም። የዴሞክራሲው መጫወቻ ግብ በግልፅ ተቀምጦ ሲያበቃ፤ የማያግባቡ ሃሳቦችን ማንሸራሸርም ወደሚፈለገው የጋራ መግባባት አጀንዳ ሊያመጣ አይችልም። ስለሆነም ሁሉም ተወያይ ወገኖች ውጥናቸው ይሰምር ዘንድ የመወያያውን ግብና ድንበር በማወቅ ልዩነታቸውን አቻችለው ለሀገራቸው መስራት ይኖርባቸዋል።

ርግጥ በቅርቡ ተወያዩቹ ሊለያዩዋቸው የማይችሉ እጅግ ዝቅተኛ አጀንዳዎችን በይደር አቆይተው በቀጠሮ መለያየታቸው ይታወቃል። ለነገሩ ልዩነት እንኳንስ ለአንድ ሀገር ከሚሰሩ ፓርቲዎች ቀርቶ በግለሰቦች ውስጥም ሊኖር ስለሚችል ‘ለምን ተለያዩ?’ ማለት አይቻልም። እንዲያውም በሃሳብ መለያየት የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። ዴሞክራሲ ያለ ልዩነት ገቢራዊ ሊሆን አይችልም። ሁሉም ፓርቲ ምናልባትም ተመሳሳይ ምልከታን እንጂ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ላይዙ ይችላሉ። እናም የፓርቲዎቹ በሃሳብ መለያየት የነበረ፣ ያለና ወደፊትም ሊኖር የሚችል በመሆኑ እምብዛም የሚያሳስብ ጉዳይ አይመስለኝም።

እኔን የሚያሳስበኝ ግን ተወያይ ፓርቲዎች ‘የሀገራችንን ዴሞክራሲ እናጎልብት’ በሚል በትልቁ ጉዳይ ተስማምተውና ተግባብተው ሊያለያይ በማይችል ጥቃቅን ጉዳዩች መለያየታቸው ነው። በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በዋናው የመወያያና የመከራከሪያ ጉዳይ ላይ የራሱን አሉታዊ ጥላ ሊያጠላ ስለሚችል፤ ሁሉም ተወያይ ፓርቲዎች ግማሽ መንገድ አንዱ ወደ ሌላው መምጣትን መዘንጋት የለባቸውም። ይህን የሚያደርጉት ይዘውት የተነሱትን ትልቁን የሀገርን ዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጎልበት እንጂ የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አለመሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል።

ሁሉም ተወያይ ወገኖች በዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ አንድ ሃሳብ በሌላኛው እንደሚሸነፍና ምናልባትም አንዱ በሌላኛው ሃሳብ ተማርኮ የራሱን በመተው የዚያኛውን ወገን አስተሳሰብ የሚያራምድበት ጊዜ መኖሩም መዘንጋት የለበትም። ይህ የሚሆነውም ዴሞክራሲ ለመሪው ሳይሆን ለተመሪው የሞራል ግዴታ ያለበት በመሆኑም ጭምር ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ “እኩይ” እና “ሰናይ” ተብለው የሚፈረጁ የሞራል ዘውጎች አሉ። ዴሞክራሲ በማህበረሰቡ ዕይታ የተቃኘ በመሆኑ “ለሰናይ” ምግባሮች ቅድሚያ ይሰጣል—ተከታዩ ማህበረሰብ የሚፈልገውን የሞራል ፈርጅ ካልወገነ ሊከተለው የሚችለው ሊቅም ይሁን ደቂቅ የለምና። እናም ተደራዳሪ ወገኖች ህብረተሰቡ የሚፈልገውን “ሰናይ’ መንገድ መከተል ብቻ ሳይሆን መንገዱንም ለህብረተሰቡ በማሳየት ፋና ወጊ መሆንም አለባቸው። አሊያ ግን ሁሉንም ተግበራት በአንክሮ በሚከታተለው ህዝብ ዓይን ውስጥ ለትዝብት መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም።

ርግጥ ህዝብ ሁሉንም ነገር የሚያይ፣ ሚዛናዊና ለየትኛውም ወገን የማይወግን በመሆኑ፤ ማን ምን እንደሚሰራ፣ የትኛው ወገን ሀገሩንና እርሱን ማዕከል አድርጎ እንደተንቀሳቀሰ፣ የትኛውስ ከዚህ ውጭ ሆኖ ራሱን ብቻ በማዳመጥ እንደተንቀሳቀሰ ያውቃል። እናም በእንቅስቃሴው ልክ ይሰፍረዋል። በሰፈረው ልክም ወገንተኝነቱን ያረጋግጣል፤ በካርዱም ይሁንታን ይቸራል። እናም ሁሉም ተወያዩች ይህን የህዝቡን ሚና እና ሉዓላዊ የስልጣን ባቤትነት በአግባቡ በመገንዘብ ውይይታቸው ህዝብንና ሀገርን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲከናወን ከወዲሁ ሰጥቶ መቀበልንና “ወርቃማውን አማካይ መንገድ” መከተልን ሊመርጡ ይገባል።               

     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy