Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ሁሉ ዳኛ ሁሉ ተከሳሽ የሆነበት ኑሯችን

0 554

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ሁሉ ዳኛ ሁሉ ተከሳሽ የሆነበት ኑሯችን!”

በርእሴ ሁሉ ዳኛ ሁሉ ተከሳሽ የሆነበት ኑሯችን ያልኩት ግርም ስለሚለኝ ነው። ሁላችንም በራሳችን የተሾምን ዳኞች ሆንን ሌሎችን ፈራጆች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች እራሳቸውን ሾመው ዳኛ ሆኑ እኛ ደግሞ ተከሳሾች፤ የምን ፍርድ እና ክስ ነው ትሉኝ ይሆናል፤አዘውትረን ስለምንሰየምበት የዳኝነት ወንበር፤ መልሰን ደግሞ ስለምንቀመጥበት የተከሳሽ ወንበር ነው የማወራላችሁ፤

በዳኝነት ወንበራችን ሌሎች በራሳቸው ህይወት የሚወስኑትን ውሳኔ የኛን ህልውና ይነካ ይመስል፤ የራሳቸውን መንገድ ስለመረጡ ብቻ ሰዎችን እየጎተትን ባልተጻፈ የምናብ ህጋችን ለፍርድ እንገትራቸዋለን። አብዛኛዎቹ ጥፋታቸው በህሊና ሚዛን የተለካ ሳይሆን፤ በደመነፍስ የሚሰፈር ነው። ስራቸው ድንበር አልፎ የኛን ህይወት ባይነካም፤ እጣታችን ግን ድንበር አልፎ ይቀስርባቸዋል።

ሌሎችም እንደዛው በጓዳችን የሚገነፍለው ሽሮ የነሱን ጓዳ ያቆሽሽ ይመስል ጠዋት ከተሰየምንበት የዳኝነት ወንበር ጎትተው ለክስ ይጠሩናል። እርስ በርሳችን በነጻነት መኖር አልቻልንም፤ ምክንያቱም ሁሉም ዳኛ ሁሉም ተከሳሽ ነውና። ሰው ምን ይለኛል በሚል የኑሮ ስርዓት ለመኖር ተገደናል። እያንዳንዳችን ለምንወስነው ውሳኔ የሌሎችን ይሁንታ ማግኘቱ ከተከሳሽነት የሚያድነን ብቸኛው አማራጭ ነው።

ተፈራርተን እስከመቼ እንኖራለን? ሁሉም በህይወቱ የራሱ የሆነ ምርጫ አለው። ምርጫቸው ከኛ ጋር አልተስማም ማለት ህገ ወጥ አያሰኛቸውም። ምን አልባት የሰውን አፍ ባንፈራ ልናደርጋቸው የምንሻቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ግን ሁሉም ዳኛ ነውና ፍላጎታችንን ገታ ማድረጉ ግድ ይለናል። የራሳችንን ህይወት በአግባቡ ሳንቃኝ፤ የፍርድ ወንበር ላይ ቁጢጥ ማለቱ የሁላችንም ልምድ ሆኗል። እርግጥ ነው ሰዎች በህይወታቸው ስህተት ይሰራሉ፤ አንዳንዴ የሚደርስባቸው ቅጣት ግን ከስራቸው በላይ ነው፤ ለምን? ሁሉም ዳኛ ስለሆነ። የሚገርመው ደግሞ ዳኞቹም፤ በሌላ ሜዳ ተከሳሽ መሆናቸው ነው። ኑሯችን ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ፍርድ ቤት ነው። ነጻነታችንን እርስ በእርሳችን ተነጣጥቀን፤ ሁላችንም በአይናችን የተሸከምነውን ጉድፍ ትተን ለምን እጣታችን የሌላው አይን ይጎረጉራል? ብዙ ሰዎች ተሸማቀው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል ፤ ለያውም የሰሩት ስራ ከራሳቸው ህይወት ዘሎ የሌላውን ሳይነካ፤ ፍርዳችን ግን ድንበር ያልፋል። እኛን በሚመለከትና የኛን ህይወት፤ የማህበረሰቡን ህልውና በሚነኩ ጉዳዮች ለፍርድ መቆሙ ግዴታችን ነው። አለበለዚያ ግን በማይመለከተን የሰዎች ህይወት ውስጥ እየገባን፤ ሌሎችም በማያገባቸው በኛ ኑሮ እየገቡ፤ አንዴ ፈራጅ አንዴ ተከሳሽ እየሆንን ኑሮዋችን እስከመቼ እናቃውሳለን?

ሰዎች የራሳቸውን ኑሮ እንዲኖሩ እንፈቀድላቸው።ሌሎችም የራሳችንን ኑሮ እንድንኖር ይፍቀዱልን። ማንም ከስህተት የፀዳ የለም፤ መካሰሱን ትተን መተራረሙን ብንለምድ ይበጀናል። ለራሳችንም ሆነ ለሌላው ሰው ነጻነት ስንል የዳኝነቱን ወንበር እንልቀቅ። እስከነአካቴው ሳይሆን ቢያንስ በማይመለከቱን ጉዳዮች ለፍርድ አንቁም። በራሳችን እንዲደረግብን የማንፈልገውን ነገር በሰዎች ላይ አናድርገው::
መፅሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይላል “በወንድምህ ላይ አትፍረድ ይፈረድብሐልና”
@ ሚስጢረ አደራው

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy