Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝቡን በባለቤትነት መንፈስ ያነሳሳ ፕሮጀክት

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝቡን በባለቤትነት መንፈስ ያነሳሳ ፕሮጀክት (ታዬ ከበደ)

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጪው ወር ላይ ስድስተኛ ዓመቱን ይደፍናል። በዚህ ስድስት ዓመት ውስጥ በርካታ ተግባራት ተፈፃሚ ሆነዋል። በዋነኝነት ጎልቶ የሚወጣው ግን የግድቡ ሰሪና ጠባቂ የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። የሀገራችን ህዝቦች “አይሞከርም” በሚል በተለያዩ ሃይሎች ስም ሲሰጠው የነበረውን ይህን ግድብ ስጀምሩት ማንንም ተማምነው አልነበረም—የራሳቸውን አቅምና ችሎታ እንጂ።

እናም ቀደም ሲል “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” ብለው ተነስተው፤ በግድቡ ስድስተኛ ዓመት ዋዜማ ላይ ደግሞ “እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን” ብለው እንደነበር አይዘነጋም። በአሁኑ ወቅትም የግድቡ ግንበታ ከግማሽ በላይ ተጉዟል፤ 56 በመቶ ያህል። በስድስተኛው ዓመቱ ላይ ሆነውም ግድቡን ለመጨረስ ያላቸውን ፍላጎት ለመግለፅ “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ህብረ ዜማ! የህዳሴያችን ማማ!” በሚል መሪ ቃል በመጪው ወር በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።

ታዲያ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ በግድቡ ግንባታ ወቅት ባለፉት ስድስት ዓመታት በሁለንተናዊ መልኩ በግንባር ቀደምትነት የተንቀሳቀሰው የሀገራችንን ህዝብ ልናስታውሰውና ዕውቅናም ልንሰጠው ይገባል። በጉልበቱና በዕውቀቱ ለግድቡ ያደረጋቸው ገዳዩች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለይም እስካሁን ድረስ ግለቱ ያልቀዘቀዘው የቦንድ ግዥን ማውሳቱን መርጫሁ።

እንደሚታወቀው መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እውን ለማድረግ ቆርጦ በሚነሳበት ወቅት ዕቅዱ በራሱ አቅም ብቻ ግቡን ይመታል የሚል ድምዳሜ ይዞ አልነበረም፡፡ እንዲሁም የውጭውን ዓለም ድጋፍና  ዕርዳታ ጠብቆ ለማሳካት አስቦም አልተነሳም፡፡ ልማቱ የህዝብ እንደ መሆኑ መጠን፤ ስራውም በመላው ህዝብ ተሳትፎ  እንደሚሳካ ጽኑ እምነትን አንግቦ ነበር ወደ ግድቡ ስራ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባው።

ታዲያ  ይህም  ቢሆን  ህዝቡን  በመዋጮ  ለማጨናነቅ  አንዳች  ዕቅድ  አልነበረውም፤  አይኖረውምም፡፡ ህዝቡ ለራሱ ልማት በፍላጎቱ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ ሊደርስ  የሚችልበት ነጻነት ያለው መሆኑን በጥብቅ ስለሚያምንም፤ እንደ መንግስት ፍትሃዊ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚገባው በጥልቀት  ከመረመረ  በኋላ  ነበር— ህዝባዊ  ጥሪውን  ያስተላለፈው፡፡ ለዚህም ነው መንግስትን፣ ሕዝብንና በአጠቃላይ ሀገርን የሚጠቅም አማራጭ በመያዝ “ራሳችንን በራሳችን እናልማ” በማለት ይፋ መግለጫ የሰጠው።

ይህ በመንግስት የያዘው አማራጭ ይፋ ሲሆን ሕዝቡ የሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ለጉዳዩ ተገቢነት ብሎም በራሱ ለማደግ ያለው ቀናዒ ፍላጎት ምስክር ይሆናል፡፡ ሁኔታው  እያንዳንዱ ዜጋ  “ከኪሴም ጭምር  ማዋጣት  አለብኝ” የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደረገው መሆኑንም በገሃድ ያየነው ሃቅ ነው፡፡ ከደመወዝ ስጦታው ባሻገር፤ ዜጎች “ከመንግስት አምስት  ሳንቲም ትርፍ  አንሻም”  በሚል  በርካቶች  ከወለድ ነፃ  የቦንድ  ግዢ  ሲፈጽሙ የመቆየታቸው ምስጢርም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

በወቅቱ የነበረውና እስካሁን የቀጠለው የቦንድ ግዥ አማራጭ ከሃገርና ከዜጎች ዕድገት አንፃር ትክክለኛ መሆኑን የሚያስገነዝቡን በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው  ህዝቡ  በመዋጮ  የሚጎዳበት  አጋጣሚ  እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡ ይህም በራሱ ተነሳሽነት ሊያደርግ ከሚችለው መዋጮ ባሻገር፤ በመንግስት ደረጃ  “አዋጣ”  እየተባለ የሚገደድበት  ሁኔታ አለመኖሩን  በተጨባጭ  ያረጋገጠ ውሳኔ  ጭምር መሆኑን ለመገንዘብ  የሚከብድ አይደለም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ለልማቱ ቀናዒ የሆነን ህዝብ መንግስት ለመካስ መዘጋጀቱን ያረጋግጣል፡፡ ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደተሞከርኩት፤ መንግስት የቦንድ ሽያጭን ሊያደርግ  የቻለበት ብቸኛው ምክንያት የልማት ተግባሩን ስኬታማ  ለማድረግ  ነው፡፡ ከልማቱ  የሚጠቅመው  ህዝብና ሀገር መሆኑ ደግሞ አያጠያይቅም፡፡ ህዝቡ ቦንድ በመግዛት የሚያደርገው  አስተዋጽኦም የራሱን ልማትና ዕድገት ከማፋጠን አንፃር  የሚታይ ነው፡፡  

ለነገሩ ህዝቡ ለራሱ ልማት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ መንግስት ቀላል ግምት የሰጠው  አለመሆኑን  ቦንዱ  የሚያስገኘው  የወለድ  መጠን ያመላክታል፡፡ መንግስት  በቦንድ  ሽያጭ  ባገኘው ገንዘብ የግድቡን ስራ  በሚያጠናቅቅበት  ወቅት፤ ቦንድ ለገዛው  ዜጋ ሁሉ አበረታች ወለድ አክሎበት (በፍቃዳቸው  ወለዱን አንሻም ካሉት ውጪ) ገንዘቡን  ይመልሳል። ይህም ህዝቡ  ለልማቱ  ላደረገው ቀና  ትብብር  መንግስት ጠቀም ያለ ወለድ በመክፈል ለመካሱና ለማመስገን  ማሰቡን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ከመንግስት ልገሳን በቦንድ የመቀየር ልማታዊ ውሳኔ  ጋር ተያይዞ  ሌጤን  የሚገባው  ሌላኛው ጉዳይ፤ ውሳኔው የህዝቡን የቁጠባ ባህል ይበልጥ የሚጠናክር መሆኑ ነው፡፡ ዛሬም ላይ ህዝቡ ከግድቡ ግንባታ ለአፍታም እንዳይርቅ ያደረገ ነው። ቀደም ሲል  እንደገለፅኩት፤ ቁጠባ  የአንድን ሀገር ዜጎች  ህይወት  በመቀየርና ዕድገትን  በማፋጠን ረገድ ቁልፍ  ሚና ይጫወታል፡፡ ይህንም በምስራቅ ኤስያ ሀገራት አካባቢ ባለው ተሞክሮ  ብቻ ማረጋገጥ  ይቻላል፡፡

የቦንድ  ሽያጩን  ከሀገራዊ ልማት መፋጠን አንጻር  በምንመለከትበት ጊዜ መንግስት  ከእያንዳንዱ  የቦንድ  ሽያጭ የሚያገኘውን ገንዘብ ለግድቡ ስራ ያውለዋል፡፡ ይህም ስራው  በታቀደለት ጊዜ ውስጥ  እንዲከናወን  የሚያደርግ ይሆናል፡፡  የግድቡ  ስራም ሲጠናቀቅ በሀገራችን  ያለው የኃይል  አቅርቦት  አስተማማኝ  ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ አሁን እየታየ ያለው የኃይል መቆራረጥ ችግርንም ሙሉ ለሙሉ ይፈታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሀገሪቱ ለጎረቤትና አካባቢው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የምትችልበት አቅምን  ያጎናጸፋታል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘትና ሌሎች  የልማት  ስራዎችን ለማፋጠን እንድትችል ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላታል።

ይህን የመንግስት አካሄድ ከእያንዳንዱ ዜጋ የኑሮ ሁኔታ ለውጥና ዕድገት አኳያ ስንመለከተውም ፋይዳው እጅግ ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንደሚታወቀው ቁጠባ ለዜጎች ህይወት መለወጥ ወሳኝ ድርሻ አለው። እያንዳንዱ ሰው ከገቢው ቆጥቦ  የሚያጠራቅመው ገንዘብ በቀጣይነት ለማደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ያደርግለታል፡፡ ይህም ዜጎች  ከመንግስት ቦንድ ሲገዙ በአንድ በኩል ልማቱን እንዲደግፉ በሌላ ወገን ደግሞ ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ስለሚያደርግ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ያሳያል።

በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት በውሳኔው ለሰራተኛው ህዝብ ሁነኛ አጋር መሆኑን ማረጋገጡን በቀላሉ መመልከት ይቻላል። ሁላችንም እንደምንገነዘበው የመንግስት ሰራተኛው ከግድቡ ስራ ይፋ መሆን ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት የቻለና እያበረከተ የሚገኝ ነው። ሁኔታው ሰራተኛው ለመንግስት ልማታዊ ስራዎች አጋር መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳ ነው። መንግስትም ሰራተኛው በምን መልኩ አጋርነቱን እያሳየ እንደሚገኝ በውል ተረድቶታል። ከሚበላውና ከሚጠጣው ቀንሶ ለልማቱ ድጋፉን እንደሰጠም ተገንዝቧል። በመሆኑም የመንግስት ሰራተኛው እያደረገ ላለው አጋርነት የሚመጥንና ወቅታዊነቱን የጠበቀ ሽልማት በማበርከት መንግስት ያለውን ድጋፍ ለማረጋገጥ ወስኖ በመንቀሳቀስ ውሳኔ አሳልፏል።

በሁለተኛ ደረጃም ውሳኔው መንግስት ከህዝቡ ጋር አብሮ ለማደግ ፅኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ያረጋገጠ ነበር። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ህዝቡ ለልማት ካለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት በመነሳት ለግንባታ ስራው ስኬታማነት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ቆይቷል። በዚህም በማዋጣትና ቦንድ በመግዛት በሚያደርጋቸው ድጋፎች መንግስት የግድቡን ስራ እያካሄደ ስድስተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል። ለዕቅዱ ስኬታማነት የተጋን ወገን ለመካስ ማሰብ ደግሞ ከአንድ ህዝባዊ መንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው። ይህም መንግስት የዜጎችን ዕድገት የራሱ አድርጎ የሚመለከት መሆኑን የሚያመላክት ሃቅ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ለመንግስት በተለይም የህብረተሰቡ ውስጥ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር  ትኩረት የሰጠ መሆኑን ያስገነዝባል። እንደሚታወቀው ቦንድ አንድ የቁጠባ አይነት ነው። ቁጠባን ማዳበር የግለሰቦችን ብሎም የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑ አይታበይም። ታዲያ በዚህ ቁጠባ ተጠቃሚ የሚሆኑ  ዜጎችም በቦንድ ግዥ ያገኙትን ገንዘብ ከነ ወለዱ በጥሬው ለመረከብ የሚችሉት መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይሆናል።

በተለይም የቁጠባ ልምዱ የሌላቸው ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀበሉት ገንዘብ ፤ ቁጠባ ምን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን እንዲገነዘቡና አንዱ የህይወታቸው አካል አድርገውት እንዲንቀሳቀሱ መልካም አቅጣጫ የሚያሳያቸው አጋጣሚም ይሆናል። በእኔ እምነት እነዚህ ሶስት የቦንድ ግዥ ጠቀሜታዎች መንግስትንና ህዝቡን ያቆራኘ ከመሆኑም በላይ ህዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሮ በባለቤትነት መንፈስ እንዲነሳሳ ያደረገ ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል።

 

                                                

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy