Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህግና ተግባር ለየቅል

0 603

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) የሚመረተው ታዳሽ ካልሆነ የነዳጅ ድፍድፍ ዘይት ቅሪት ነው። አፈር ውስጥ ሳይበሰብስ ከ100 እስከ 200 ዓመታት መቆየት እንደሚችል ከአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በቆይታው በሚፈጥረው ኬሚካል በሰዎችና በእንስሳት ጤና እንዲሁም በከተሞች ውበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአገራችን የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ ህጎች ወጥተዋል።

የደረቅ ቆሻሻ አዋጅ 513/99 አንቀጽ8 ንዑስ አንቀፅ 1 እስከ 3 ያለው ክፍል ሁለት መሰረታዊ ድንጋጌዎችን ይዟል። ይሄውም «ስስ የሆኑ የፕላስቲክ ከረጢቶችና ማሸጊያዎች ውፍረታቸው 0ነጥብ 03 ሚሊ ሜትርና ከዚያም በታች የሆኑ፣ በስብሰው ከአፈር የሚዋሀዱና የማይዋሀዱ መሆናቸውን የሚገልፅ ምልክት ያልተደረገባቸውን በአገር ውስጥ ማምረት አይቻልም። ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡም ፈቃድ አይሰጥም» ይላል። ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ላይ እየዋሉ ያሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች ከህጉ ጋር ምን ያህል ተዛምደዋል? ስንል የዘርፉ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

የአካባቢ ጥናት ባለሙያው ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሄር የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) በተለያየ መልኩ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። «በአገራችን እየተመረተ ያለው አብዛኛው የፕላስቲክ ከረጢት ወደ አፈርነት የሚለወጥ ሳይሆን የማይበሰብስና አደጋ የሚያስከትለው ነው። በዚህ ዙሪያ አገሪቱ ያወጣችው ህግ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም» ይላሉ። ትናንሽ ፋብሪካዎችም ከህግ ውጪ በሀገር ውስጥ አምርተው የሚያሰራጩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የፕላስቲክ ከረጢቶችን በተመለከተ ህግ ሲወጣ ትኩረት የተደረገው ይዘታቸው ላይ ነው። ወፈር ያለ ከሆነ ዋጋውም ይጨምራል፤ ለተደጋጋሚ ጊዜ አገልግሎት ይሰጣል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ እንጂ በስብሶ ወደ አፈርነት የሚቀየር መሆን አለበት ከሚል አስተሳሰብ አልነበረም። በወቅቱ በዚህ ደረጃ እውቀቱም ሆነ ቴክኖሎጂው አልነበረም። ስለዚህ ከወቅታዊ ሁኔታው አንፃር ህጉ ሊቃኝ እንደሚገባ ይገልፃሉ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የአፈር ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዋሴ ኃይሌ የዶክተር ተወልደብርሃንን ሀሳብ ይጋራሉ። የፕላስቲክ ከረጢት ምርት በህጉ መሰረት እየተሰራበት ነው የሚል እምነት የላቸውም። ምክንያቱም አሁን አገልግሎት የሚሰጡት የፕላስቲክ ከረጢቶች ዋጋቸው ርካሽ፣ አንድ ጊዜ እንኳን አገልግሎት የማይሰጡ እና በጣም ስስ በመሆናቸው ወደ ብስባሽነት የማይለወጡ ናቸው።

መሬትን ከሚጎዱ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ፕላስቲክ በመሆኑ ብዙ ሀገሮች በፕላስቲክ አመራረት፣ በፕላስቲክ ምርቶች ቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ጠንካራ ህግ አላቸው። በመሆኑም በኢትዮጵያም የፕላስቲክ ምርት መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ መመቻቸት አለበት። በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ይናገራሉ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአናላይቲካልና ኢንቨይሮሜንታል ኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ አስተባባሪ ዶክተር አብረሃ ገብረኪዳን እንደሌሎቹ ባለሙያዎች ሁሉ ህጉ በትክክል ተግባር ላይ አለመዋሉን ይስማሙበታል። የፕላስቲክ አመራረትና አወጋገድ በህጉ መሰረት መስራት ካልተቻለና የትግበራ መንገዱም ቁጥጥር ካልተደረገበት በቀጣይ በአገሪቱ ምርታማነት ላይ ትልቅ ስጋት መሆኑን ይጠቁማሉ።

«የፕላስቲክ ምርቶች ከፔትሮ ኬሚካል የሚመረቱ በመሆናቸው ደጋግሞ በመጠቀምና በተፈራራቂ የሙቀት ኃይል ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎች ይፈጠራሉ። ይህም የተለያዩ የጤና ችግሮችን ያስከትላል። አፈር ላይ በሚጣሉበት ወቅት በአፈር ውስጥ ውሃ በቀላሉ እንዳይሰርግ፤ የአየር እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያደርጋሉ። በአጠቃላይ ኬሚካሉ ከአፈሩ ጋር ሲቀላቀል ምርትና ምርታማነት ይቀንሳል» ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ዶክተር አብርሃ፤ የሌሎች አገሮችን እርምጃ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። «ለምሳሌ የኬንያ መንግስት በአገሩ ውስጥ የፕላስቲክ ከረጢቶች እንዳይመረቱ ከልክሏል። ይሄ ለእኛ አገርም ትልቅ ነገር ያስተምራል። በመሆኑም ወደፊት የህጉን ትግበራ ማጠናከር፣ በወረቀት ከረጢት መተካት እንዲሁም በህጉ መሰረት የሚመርቱና አገልግሎት ላይ የሚውሉትን የፕላስቲክ ከረጢቶች በአግባቡ ሰብስቦ ወደ ነዳጅነት መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስራት ይገባል» ሲሉ በቀጣይ መሰራት ያለበትን የመፍትሄ ሀሳብ ያመላክታሉ።

በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የአደገኛ ቆሻሻ ህግ ማስከበር ባለሙያ አቶ ግርማ ገመቹ በበኩላቸው፤ የፕላስቲክ ከረጢቶች ከተመረቱ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡት ለአንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ አካባቢያዊ ውበትን ያሳጣሉ። በቆሻሻነት ሲወገዱ ደግሞ ሙቀት አማቂ ጋዝ እንዲመነጭ ያደርጋሉ። ይሄም በዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ላይ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። እንዲሁም በመሰረተ ልማት ላይም ተመሳሳይ ችግሮችን እንደሚያስከትል ይናገራሉ።

«እስካሁን ባለው ሂደት አገሪቱ ያወጣችውን ህግ ያላከበረ የፕላስቲክ ከረጢት ህጋዊ ሆኖ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ የለም» ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ሆኖም በአገር ውስጥ በህግ የተከለከለ የፕላስቲክ ከረጢት እየተመረተ መሆኑን በተለያየ ጊዜ በተደረገ ማጣራት ለማረጋገጥ መቻሉን ይጠቅሳሉ። ይህም በህገወጥ ተግባር የሚሰራው ህጋዊ አምራች ሆነው ፈቃድ በወሰዱና ለሌሎች የፕላስቲክ ምርቶች ማምረቻ በሚል ጥሬ እቃውን በህጋዊ መንገድ በሚያስገቡ ፋብሪካዎች ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 400 የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ሲገኙ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ጥናት 24ቱ በህገወጥ መንገድ እንደሚሰሩ ተረጋግጧል። እንዲሁም በአገሪቱ በ24 ከተሞች ላይ በተሰራው ጥናት ደግሞ በዓመት ከሚሰበሰበው ቆሻሻ ውስጥ ከ5 እስከ 9 በመቶ የሚሆነው የፕላስቲክ ቆሻሻ ነው። ይህንንም አደገኛነቱን የከፋ የሚያደርገው ተመልሶ ጥቅም ላይ የማይውል በመሆኑ ነው።

አቶ ግርማ፤ ከህጉ በተጨማሪም በድብቅ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ሰፊ የክትትልና የቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚገባ ይናገራሉ። የሚያስከትሉትን ጉዳት ህብረተሰቡ ከወዲሁ ተገንዝቦ የዘንባባ፣ የጨርቅ እንዲሁም አሁን ዓለም ላይ እየመጡ ያሉ የወረቀት ከረጢቶችን በአማራጭነት እንዲጠቀም ግንዛቤ ማስፋት መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ። አልማዝ አያሌው

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy