Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የመንግሥት የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት የቆሼ ጉዳት በምሳሌነት

0 874

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰው ልጅ በሕይወት ሲኖር ከተለያዩ ሕግጋት የሚመነጩ አለበለዚያም ጥበቃ ያገኙ ወይም ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች ይኖሩታል፡፡ እነዚህ መብቶችም ይከበሩለት ዘንድ በድጋሚ ሕግ ያዛል፡፡ ለመከበራቸው አጋዥ የሆኑ ተቋማትም ይኖራሉ፡፡ የመብት ጥሰት ባጋጠመ ጊዜ ማን ምን መደረግ እንዳለበትም ሕግ ይኖራል፡፡ የመብቶቹ ዓይነቶች መበራከት መብቶቹን የሚጥሱትና ጥበቃ ማድረግ ያለባቸው አካላትም እንዲሁ ሊበረክቱ ይችላሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ባለመብቶቹ ዜጎች፣ መብቶቹን የሚጋፋው ደግሞ መንግሥት በሚሆንበት ጊዜ ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት የተወሰኑ ነጥቦችን መዳሰስ ነው፡፡ በተለይም በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ መንግሥታዊ ተቋምም ይሁን ሹመኛው አሊያም ሠራተኛው በዜጎች ላይ ለሚያደርሳቸው ጉዳቶች ከውል ውጭ በሚመጣ ኃላፊነት ካሳ ሊከፈል የሚችልበትን ሁኔታ ማመላከት ነው፡፡

የዜጎችን መብት በተመለከተ መንግሥት የተለያዩ ግዴታዎች አሉበት፡፡ በተለይ ሰብዓዊ መብቶች ሲሆኑ ደግሞ የማክበር፣ የማስከበር እንዲሁም እንደነገሩ ሁኔታ የማሟላትም ግዴታዎችም አሉበት፡፡

የማክበር ግዴታ የሚመለከተው ራሱ መንግሥት የዜጎችንም ይሁን የሌሎች ሰዎችን መብት ከመጣስ መቆጠብን ነው፡፡ ከተቋማቶቹ አንዱ ወይም ሹመኛ አለበለዚያ ሠራተኞቹ የሌላን ሰው መብት በመጋፋታቸው ምክንያት ጉዳት ከደረሰም በየፈርጁ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር ወይም አስተዳደራዊ ዕርምጅ መውሰድ አለበት፡፡ ሌሎች አካላትም እንዲሁ ባለመንገድ የሌላ ሰውን የሚቃረን ድርጊት ከፈጸሙ የማስከበር ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ የተለያዩ መብቶችም ዕውን (የመማር፣ የጤና ወዘተ) ይሆኑ ዘንድ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ሲኖሩ ቢያንስ ሕግ በሚያዘው አኳኋን አቅም እንደፈቀደ ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

ነገሩ እንዲህ ከሆነ፣ የተለያዩ ምሳሌዎችን በማስቀመጥ መንግሥት ማክበር ሲሳነው የዜጎች ያላቸውን የፍትሐ ብሔር መብት እንመልከታቸው፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ዜጎች ካጋጠሟቸው የመብት ጥሰቶች ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ፡፡

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና አመፅ ምክንያት በፀጥታ ሠራተኞች ሕይወታቸው ያለፉና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ለሕልፈታቸውም ይሁን ለደረሰባቸው የአካል ጉዳት ምክንያቶቹ እጅግ በርካታና የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ የተወሰኑት ላይ ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል፣ እንበል፡፡ የተወሰኑት ላይ ደግሞ አስገዳጅ ሁኔታ ወይም ሕጋዊ መከላከል ነበር፣ እንበል፡፡ ዞሮ ዞሮ በሕይወት የመኖር ወይም የአካል ደኅንነትታቸው የመጠበቅ መብት የነበራቸው ዜጎች ላይ ጉዳት ደርሷል ወይም ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ዜጎች በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታና በመረጡት የሙያ ዘርፍ ተሠማርተው የመኖር ብሎም ሀብትና ንብረት የማፍራት መብታቸው በመፈናቀላቸው ምክንያት ተጥሷል፤ ጉዳትም ደርሶባቸዋል ማለት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ከተከሰቱት አሳዛኝ ድርጊቶች ውስጥ አንዱ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ፣ በመንግሥት ቁጥጥርና ኃላፊነት ሥር ከነበሩ ዜጎች ውስጥ የተወሰኑት ማረሚያ ቤቱ ሲቃጠል አብሮ ሕይወታቸው ማለፉ ነው፡፡ ቃጠሎውን የፈጸመው  ማንም ይሁን ማን በመንግሥት ጥበቃ ላይ እያሉ ግን በሕይወት የመኖር መብታቻው በዚያው ሁኔታ የተገታ ዜጎች ነበሩ፡፡

ሌላው፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ሳይሆን በሳለፍነው ሳምንትም ጭምር ከደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ልጆች ታግተው ተወስደዋል፡፡ ከብቶች ተዘርፈዋል፡፡ መንግሥት እነዚህ ዜጎች ላይ የውጭ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጉ ምክንያት የተፈጸሙ ጥሰቶችና ጉዳቶች መሆናቸው ናቸው፡፡

በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ጭምር ፓርላማ ላይ  እንደተናገሩት፣ በተወሰኑ ክልሎች መካከል በተነሳ ግጭቶች ሚሊሽያና ልዩ ኃይሎችም ጭምር በተሳተፉበት ሁኔታ የተወሰኑ የወረዳና የዞን አመራሮችም አጋዥነት በታከለበት ግጭቶች የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡ ሌሎች ጉዳቶችም ደርሰዋል፡፡

ሌላው እጅግ ዘግናኝ የሆነው ድርጊት ደግሞ በቅርቡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ በተባለው ሥፍራ ላይ የተፈጸመው ነው፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በላይ የተከማቸ ቆሻሻ ተንዶ 115 ሰዎችን ሲገድል፣ ሀብትና ንብረትንም አውድሟል፡፡ ቆሻሻውን የሚያጠራቅመው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡

እነዚህ ድርጊቶች የቀረቡት በናሙናነት ነው፡፡ ቁምነገሩ፣ ዜጎች የዜጎችን መብት እንደሚጥሱ ሁሉ መንግሥትም የዜጎችን መብት በሚጥስበት ጊዜ የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ከላይ የተገለጹትን የመብት ጥሰቶች መሠረት በማድረግ ሊኖር የሚችለውን ጥያቄ (የካሳና ሌላም) እንደምን አድርጎ ማቅረብ እንደሚቻል እንመልከት፡፡

ሰዎች በኑሯቸው የሚያደርጓቸው ድርጊቶች የሌላን ሰው መብት የሚጥሱ ሆነው በተገኙበት ጊዜ የወንጀል ወይም የፍትሐ ብሔር፣ እንደነገሩ ሁኔታ ሁለቱንም ኃላፊነቶች በጥምር ሊያስከትልባቸው ይችላል፡፡ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት (liability) በራሱ የውል አለበለዚያም ከውል ውጭ በሆነ ምክንያት ኃላፊነት ሊያመጣ ይችላል፡፡ መነሻው ውል የሆነ እንደሆነ የኃላፊነቱ ሁኔታና መጠን በውሉ ይታወቃል፤ እንደ ውሉ ይፈታል፡፡ ውል ያላደረጉ ሰዎች አንዱ ሌላው ላይ ኃላፊነት የሚያስከትል አድራጎት ካደረጉ ግን መፍትሔው ሊገኝ የሚችለው ከሕግ ብቻ ነው፡፡

ውል በሌላቸው ሰዎች መካከል ሊፈጠር የሚችለው ኃላፊነት መነሻቸው ሦስት ዓይነት ሊሆን እንደሚችል የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ላይ ተገልጿል፡፡ የመጀመሪያው አንድ ሰው በራሱ ጥፋት (fault based) ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ነው፡፡ ሁለተኛው የኃላፊነት መነሻ ደግሞ ጉዳት ፈጻሚው ሆን ብሎም ይሁን በንዝህላልነት ባያደርገውም እንኳን በሕግ ኃላፊ መሆንን (strict liability) እንደሚያስከትሉ ከተገለጹት አድራጎት ውስጥ የሚካተት ከሆነ ነው፡፡ ሦስተኛው የኃላፊነት መነሻው ደግሞ ድርጊቱን ለፈጸመው ሰው ሌላ ሰው ኃላፊነትን የሚወሰድበት ሁኔታ (vicarious liability) ነው፡፡ ሦስቱንም በየተራና ከላይ ካነሳናቸው የመብት ጥሰቶች አንፃር እንመልከታቸው፡፡

የመጀመሪያው አንድ ሰው በራሱ ጥፋት ምክንያት ሌላን ሲጎዳ ነው ብለናል፡፡ በዚህን ጊዜ የተፈጸመው ድርጊት ጥፋት መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም፣ ይህ ጥፋት የሆነው አድራጎት ሌላ ሰው ላይ ካሳ ሊያስከፍል የሚችል ጉዳት ያስከተለ መሆን አለበት፡፡ ጥፋት ብቻ መፈጸሙ ሳይሆን ጥፋቱን ተከትሎ የመጣ ጉዳት መኖር አለበት፡፡ እንዲህ ያደረገው ሰው በጥፋቱ ምክንያት ያደረሰውን ጉዳት ማሰተካከል ወይም ማቃናት ወይም ካሳ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

ጉዳት ያደረሰው አካል ደግሞ የግድ በተፈጥሮ ሰው የሆነ ብቻ ሳይሆን ተቋማት፣ መንግሥታት፣ ድርጅቶች ወዘተ ሊሆንም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ያመጣ ጥፋት መፈጸሙ ላይ ነው፡፡ ጥፋት የሚባለው ደግሞ የግድ ወንጀል መሆን የለበትም፡፡ በሕግ የተገለጸን አሠራር መጣስ፣ መልካም ጠባይን የጣሰ ወይም አሠራርን የሚቃረን እስከሆነና አፈጻጸሙ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት መሆኑ ብቻ ይበቃል፡፡

ሙያተኛ የሆነ ሰው ሙያው ከሚያዘው ውጭ በመሥራቱ ጥፋትና ጉዳት ከመጣ ኃላፊ መሆንም አይቀርም፤ ይከተላል፡፡ ሙያተኛ ሲባል እንግዲህ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ፖሊስ፣ የቆሻሻና ፍሳሽ አወጋገድ ባለሙያ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥፋተኛ ለማለትም ይሁን ላለማለት መመዘኛው የየሙያዎቹ ደንቦች ናቸው፡፡ በሙያዎቹ ደንቦች ሲመዘን ጥፋት ከሌለበት ኃላፊነት አይኖርበትም ማለት ነው፡፡

በሕግ ላይ በግልጽ የተቀመጠን አሠራርን የጣሰ ካለ ኃላፊነቱ ያለው የጣሰው ሰው ላይ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሕግ የሚባለው በግልጽ ተለይቶ ስላልተቀመጠ ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ አዋጆች፣ ደንቦች እንዲሁም መመርያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የማንም ሰው አድራጎት ሕግን የጣሰና በመጣሱም ምክንያት ጉዳት እስከደረሰ ድረስ ኃላፊነትን ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡

ከእነዚህ አኳያ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አገሪቱን ከውጭ ወራሪም ይሁን ጥቃት መከላከል በሕግ የተጣለበት ግዴታው ነው፡፡ የክልል ልዩ ኃይል ፖሊሶችም ይሁኑ ሚሊሻዎች የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ የሕግ ግዴታ አለባቸው፡፡ የማረሚያ ቤት አስተደዳደርም በታራሚነትም ይሁን ፍርደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጠብቆ የማቆየት በሕግ የተጣለበት ግዴታው ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የተጣለባቸውን ግዴታ ባለመወጣታቸው ምክንያት ልክ ጋምቤላ አካባቢ እየተፈጸመ እንዳለው አድራጎት ዜጎች ላይ ጉዳት ከደረሰ ተጎጂዎች እዚህ ተቋም ላይ ክስ ከማቅረብ የሚከለክላቸው ሕግ የለም፡፡

ተቋሙ ግዴታውን ባለመወጣቱ ሕግ ስለጣሰ (ሕጋዊ ግዴታውን ስላልተወጣ) እና ወይም ጠረፍ ስላልጠበቀ፣ የልዩ ኃይል ፖሊስም ይሁን ሚሊሻዎች በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን እንደተቋም አልፈው የሌሎች ክልል ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ካደረሱም እንዲሁ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2035 መሠረት የሕግ አለመከበር ያው የሕግ መጣስ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳት የደረሰው በፖሊሶቹም ይሁኑ በሚሊሻዎቹ በግላቸው ከሆነ ተጠያቂነቱ በግል ብቻ ይሆናል፡፡ የቆሼውን በተመለከተ፣ ስለደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድና የሚመለከተው አካል በሕግ ተለይቶ የተቀመጠ አካል ካለ የተሰጠውን መንግሥታዊ ድርሻ ባለመወጣቱ ምክንያት ጉዳቱ ደርሷል ማለትም ይቻላል፡፡ ተግባርና ኃላፊነቱ ቆሻሻ የሚወገድበትንና አካባቢውን ጤናማ ማድረግ ከሆነ ይህንን ባለመፈጸሙና ቆሻሻው ሊናድና ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ባለመንገሩ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ሕጉ አልተከበረም ማለት ነው፡፡

አገሮች ከባድ ዝናብ ወይም ማዕበል የሚነሳበትን ወቅት ለማስታወቅና ለሌላም ዓላማ ሲሉ የሜቲሪዎሎጂ፣ ስለመሬት መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራ ደግሞ የመሬት ጥናት (Geological Institute) ተቋማት ያቋቁማሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ለኅብረተሰቡ ሳያሳውቁ በፊት ከባድ ዝናብና ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ ማዕበል፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተ ገሞራ ቢከሰትና ጉዳት ቢደርስ ተጎጂዎች መንግሥት ላይ ክስ በማቅረብ ካሳ መቀበል ነገር የተለመደ ነው፡፡ በበርካታ አገሮችም ይኼው ሁኔታ ተዘውትሯል፡፡ በኢትዮጵያ ሲሆን ግን በደቡብ ኦሞና በድሬዳዋ ጎርፍ ላደረሳ፣ በቆሼ የቆሻሻ ናዳ ላደረሰው ጉዳት ዜጎች እንደ መብት ከመንግሥት ካሳ ሲቀበሉ አልተስተዋለም፡፡ መንግሥትም የተለያዩ ቁሳዊ እገዛዎችን ሲደርግ ከመብት አንፃር ሳይሆን በችሮታና በበጎ አድራጎት መልክ ነው፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆነ ባለሥልጣኑ አንድን አድራጎት በሥልጣን አላግባብ በመጠቀሙ ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰም ኃላፊነቱ ያደረሰው ሰው ራሱ ስለሆነ ጉዳቱን ማስተካከል ወይም ካሳ መክፈል አለበት፡፡ በሥልጣን ያለአግባብ ባይገለገልበትም እንኳን ሕጉ ከሚያዘው ውጭ ከተፈጸመ እንዲሁ ተጠያቂነቱ የመንግሥት አይሆንም፡፡ ነገሩን በምሳሌ ለማስረገጥ፣ ፖሊስ በሕግ የተቀመጠውን አሠራር በመተላለፍ የእጅ እልፊትና ድብደባ አድርሶ ከሆነም ተጠያቂነቱ የፖሊሱ ነው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን የተጠያቂነት አሠራር የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡

ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ እንደተገለጸውና ኢትጵያም እንዳፀደቀችው ሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚኖርበት ጊዜ የማስተካከል ግዴታን አለባት፡፡ ለደረሰውም ጉዳት ካሳ መክፈልም ቢሆን ተጨማሪ ግዴታ ነው፡፡ ስለሆነም አላግባብ ለታሰሩ ሰዎች፣ የመዘዋወር ነፃነታቸው ከሕግ ውጭ ለተገታባቸው ካሳ የመክፈል መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ሰነድ መብትንም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

ሁለተኛው የኃላፊነት መነሻ ደግሞ ጉዳት ፈጻሚው ሆን ብሎም ባይፈጽመውም በሕግ ኃላፊ መሆንን እንደሚያስከትሉ ከተገለጹት አድራጎት ውስጥ አንዱን እስከፈጸመ ድረስ ኃላፊ የሚሆንበት ነው፡፡ ጉዳት ከደረሰና መንስዔው በሕግ ላይ ከተቀመጡት ውስጥ አንዱ ከሆነ እነዚህን ሁለት መሥፈርት በማስረዳት ብቻ ኃላፊ የሆነው ሰው ካሳ እንዲከፍል ሊገደድ ይችላል፡፡ በዚህም ጊዜ ቢሆን ጉዳት አድራሹ ድርጅት፣ መንግሥት ወይም ተቋም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ያሉት ድርጊቶች በግልጽ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ስለተቀመጡ ሌላ መጨመር አይቻልም፡፡ ምናልባት ሌሎች ሕጎች ላይ በእንዲህ ያለ አኳኋን ካልተገለጹ በስተቀር፡፡ የቤት እንስሳቶች ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሲያደርሱ፣ የመኪና መግጭት ወዘተ በዚህ ሥር የሚወድቁ ናቸው፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2069 ደግሞ በርካታ ኃላፊነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ዘርዝሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የመሬትን የተፈጥሮ መልክ በመቀየር ጉዳት ያመጣ ሰው ካለ ኃላፊ ሊሆን የሚችልበት ነው፡፡ ይህንን ተግባር ፈጻሚው መንግሥትም ቢሆን እንኳን ኃላፊነት አለበት በማለት በድጋሚ አጠንክሮታል፡፡

ከላይ ከገልጽናቸው ምሳሌዎች ውስጥ ቆሼ ላይ የተፈጠረውን በአብነት ብንወስድ ከምድር ወለል በታችና በተወሰነ ጥልቀት ላይ ቆሻሻው ቢከማችም ከወለል በላይ ደግሞ ከአሥር ሜትር ባለፈ በመቆለሉ ምክንያት መሬቱ ቀድሞ ከነበረው የተለየ መልክ እንዲኖረው ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ከአሥር ሜትር በላይ ቆሻሻ መከመሩ በተፈጥሮ የነበረውን የመሬቱን ቅርጽ ወይም መልክ ቀይሮታል ከተባለ ደግሞ ይህንን አድራጎት በመፈጸሙ ምክንያት የቆሻሻው ክምር ሲቆይ በመብላላቱ ተንዶ ጉዳት ደረሰ፡፡ ማለትም፣ ከ115 ሰዎች ሕይወት ጠፋ፡፡ ንብረትም ወደመ፡፡

ሕጉ፣ የመሬቱን መልክ የቀየረው (የቆሻሻ ክምር ወይም መለስተኛ ተራራ የፈጠረው) አካል ኃላፊ ይሆናል ስለሚል ከ50 ዓመታት ላላነሰ ጊዜያት ይህንን ድርጊት የፈጸመው መንግሥት ለጉዳቱ የፍትሐ ብሔር አለበት ማለት ይቻላል፡፡ ቆሻሻ መከመሩ በየትኛውም መስተዳድር (በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግ፣ ወይም በኢሕአዴግ) መሆኑ መንግሥትን (state) ከኃላፊነት ነፃ ሊያደርገው አይችልም፡፡ ለምሳሌ አምባገነኑ ፊርዲናንድ ማርቆስ አገዛዝ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያጋጠማቸው ከ4000 ሰዎች በላይ በጋራ በቅርቡ የፊሊፕንስ መንግሥትን ካሳ እንዲከፍላቸው መጠየቃቸው ካነሳነው መከራከሪያ ጋር የተስማማ ነው፡፡ በደርግ ዘመን በነበሩ ባለሥልጣናት አማካይነት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም እንደፊሊፒንሱ ሁሉ መንግሥትን የመጠየቅ መብት የላቸውም ማለት ሦስተኛው የኃላፊነት መነሻው ደግሞ ድርጊቱን ለፈጸመው ሰው ሌላ ሰው ኃላፊነትን የሚወሰድበት ሁኔታ እንደሆነ ከላይ ገልጸናል፡፡ አካለ መጠን ላልደረሰው ልጅ ድርጊት ሞግዚቱ፣ ለሠራተኛው ደግሞ አሠሪው ኃላፊነት የሚወስዱበት አካሔድ ማለት ነው፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚ 18 ዓመት ያልሞላው ወይም ደግሞ ሥራውን በቀናነት ደፋ ቀና እያለ የሚሠራ አንድ ለፍቶ አዳሪ የሠራው ሥራ አማካይነት ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካስከተለ ኃላፊነቱ የልጁ ወይም የሠራተኛው ሳይሆን የሞግዚቱ ወይም የአሠሪው ነው፡፡ አሠሪ በሚባልበት ጊዜ የግል ድርጅት፣ መንግሥታዊ የሆነ ወይም ያልሆነ ሊሆን ይችላል፡፡

አንድ የመንግሥት ሹመኛ ወይም ሠራተኛ የሥራው አካል ባልሆነ፣ ወይም የሥራውም አካል ቢሆን እንኳን ከቅን ልቦና ውጭ ያደረገው ከሆነ፣ ወይም ሥልጣኑን በአግባቡ ባለመጠቀሙ የመጣ ኃላፊነት ካልሆነ በስተቀር መንግሥት ኃላፊ እንደሆነ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የግል ጥፋት የግል ኃላፊነትን ያስከትላል እንጂ የመንግሥት አይሆንም፡፡

ይሁን እንጂ ከቅን ልቦና ውጪ ስለመሆኑ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ የሕጉ ግምት የተሠራው በቀና ልቦና እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ መንግሥትም ስለጉዳቱ ያልፍበታል፡፡ መንግሥት ማለት የፌደራል፣ የክልል እንዲሁም ከዚያ በታች ያሉ መዋቅሮችና መሥሪያ ቤቶችንም ይጨምራል፡፡ ጉዳት አድራሹ ድርጊቱን ለመፈጸሙ ምክንያት የሆነው የበላይ ትዕዛዝ ቢሆንም ከመጠየቅ አያድነውም፡፡ ኃላፊነት ላይኖርበት የሚችለው ፈጻሚው ወታደር ወይም ተመሳሳይ ሙያ ያለው ሆነ ከአለቃው ጋር ስለጉዳዩ ለመወያየት የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የበላዩ ኃላፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2136 መሠረት ግን ምንም እንኳን የመጨረሻ ኃላፊ የሚሆነው ሠራተኛው ቢሆንም መንግሥትን ከተጠያቂነት አያድነውም፡፡ በአንድነትና በነጠላ ሊያስጠይቅ ይችላል፡፡ ኋላ ላይ ግን በመዳረግ (መልሶ ሠራተኛውን የመጠየቅ) ክስ የማቅረብ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ጉዳቱን ያደረሰው የመንግሥት ሠራተኛ ለይቶ ማመልከት ካልተቻለም ግን ፍርድ ቤቶች እንዳለ ስብስቡ ላይ ሊወስኑ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም በርካታ ሆነው በአንድነት ባሉበት ሁኔታ ማን የተባለ ፖሊስ ወይም ወታደር ወይም የፀጥታ ሠራተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አለመታወቁ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ካሳ ከማግኘት አያግደውም፡፡ መሥሪያ ቤቱን ወይም ስብስቡንም ከኃላፊነት ነፃ አያደርገውም፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ በሥራቸው ምክንያት ያለመከሰስ መብት የተሰጣቸው ለንጉሡ፣ ለመንግሥቱ አባላት፣ ለፓርላማ አባላትና ለዳኞች ነው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ (ከንጉሡ በስተቀር) ግን በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ከሆነ ላደረሱት ጉዳት እንዲጠየቁ ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ ያለመከሰስ መብት የተሰጣቸው በመወላወል ሥራን በመሸሽ መንግሥታዊ ግዴታቸውን ባለመወጣት ሕዝቡን ሳያገለግሉ ባለመሥራት እየበደሉ እንዳይኖሩ ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡

ከላይ በተገለጹት ከሦስቱ በአንዱ አኳን ጉዳት የደረሰበት ሰው ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ጉዳቱ የደረሰበት ሰው በከፊል የራሱ ጥፋት ቢኖርበትም እንኳን እንዲሁ በከፊል ካሳ ሊያገኝ ይችላል እንጂ ሙሉ በሙሉ አይነፈግም፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በሚጣሱበት ጊዜ ስለሚሆነው ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡፡

ከውል ውጭ በሆነው መልኩ የመጣው ኃላፊነት በግልጽ በፍትሐ ብሔር ላይ ተገልጾ ከሆነ ዕዳው ገብስ ነው እንዲሉ ነገሩ በፍርድ ቤት የተዘወተረ ስለሆነ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የተዘወተረው ተራ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ብቻ ናቸው፡፡ በስተቀረ ከላይ የገለጽናቸውን ምሳሌ በመሳሰሉ ጉዳዮች ጉዳት ሲመጣ ያው ‹‹ሰማይ አይታረስ፤ ንጉሥ አይከሰስ›› ነገር ይሆናል፡፡

የሚከፋው ድሮ የማይከሰሰው (በሕግ ላይ እንደተቀመጠውም) ንጉሡ እንጂ ሌላው ባላባት፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪው፣ ራስ ወዘተ አይደለም፡፡ እንደውም ተከሳሾች ውስጥ ባላባቶች ካሉ ዳኞች ለባላባት አዳላ እንዳይሏቸው ፍርዱም ውስጥ ላይ ይሉኝታን ይጨመሩበታል፡፡ በመሆኑም እጅግ በጣም የተዋጣላቸው ፍርድን ይሰጡ እንደነበር ፈረንሳዩ ተጓዥ፣ አንቷን ሚሼል ዳባዲ፣ በ1840 በኢትዮጵያ የነበረውን ሁኔታ በመገንዘብ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ የ1948 ሕገ መንግሥትም ደግሞ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችና ሹመኞችም ጭምር ላይ ክስ ማቅረብ ይቻል ዘንድ በግልጽ ተደንግጎ ነበር፡፡

ካልተዘወተሩት ሁኔታዎች ሌላው ሕገ መንግሥታዊ ወይም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ላይ የተቀመጠው መብቴ በመጣሱ ጉዳት ስለደረሰብኝ ካሳ ይገባኛል የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ በተገለጹት የመንግሥት ድርጊቶች አማካይነት ለተፈጸሙ ተግባራት መንግሥትን ወይም ሠራተኞቹን ኃላፊ እንዳይሆኑ መከታ የሚሆናቸው ሕግ እስካሁን አልወጣም፡፡ ወደፊት ካልወጣ በስተቀር፡፡ በሌላ ሕግ በዝርዝር አለመውጣትም ለመንግሥት መልስ አይሆንም፡፡

ለእንዲህ ዓይነት ሁኔታ አገሮች  የተለያዩ ተሞክሮ አላቸው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ወይም ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ መፍትሔ ሊሆን የሚችል በሌላ ዝርዝር ሕግ የተብራራ ነገር ካለ የኃላፊነቱን ሁኔታ የሚወሰነው በዚህ ሕግ ይሆናል፡፡ ሌላ ሕግ ከሌለ ግን፣ ራሱን ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ካሳ መጠየቅ በበርካታ አገሮች ከተዘወተረ ቆይቷል፡፡ አሜሪካና ካናዳ ፍርድ ቤቶቻቸው በሰጡት ትርጉም መነሻነት ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጣሱ ለደረሰ ጉዳት ካሳ ይጠየቃል፡፡ በእርግጥ ካናዳ የሰብዓዊ መብት ኮድ የብቻው ለይታ በማውጣትና የተለየ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት በማቋቋሟ እንዲሁም የጣሰው በገንዝብ ካሳ የመክፈል አሠራር መዘርጋቷን ልብ ይሏል፡፡

አንዳንድ አገሮች (ለምሳሌ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ስሎቬኒያ፣ ፖላንድ) የሰብዓዊ ወይም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በመጣሳቸው ምክንያት ዜጎች ላይ ጉዳት ከደረሰ ለጉዳቱ የመካስ መብትን ሕገ መንግሥታዊ መብት አድርገውታል፡፡ በተለይ ሰብዓዊ መብት በብዛት የሚጥሰው መንግሥት በመሆኑ በመፍትሔነት በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ኢስቶኒያ ለደረሰው ጉዳት የገንዘብ ካሳ ሊከፈልባቸው የሚችሉትን በሙሉና በገንዘብ ከማይተመኑት ደግሞ የተወሰኑትን ቀጥታ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል ሕገ መንግሥቷ ይገልጻል፡፡ ብራዚል ደግሞ የማይጣሱና የማይገሰሱ የሰብዓዊ መብቶችን መንግሥት ከጣሰ ጉዳት የደረሰበት ሰው ካሳ የማግኘት መብት እንዳለው ሕገ መንግሥታዊ አድርገውታል፡፡

እዚህ ላይ ሌላ ልብ መባል ያለበት ቁም ነገር የሰብዓዊ መብቶቹ ዓይነት በራሳቸው ለካሳ አከፋፈልና ግምት የሚመቹና ቀላል የሆኑ እንዳሉት ሁሉ አስቸጋሪና ውስብስብም መኖራቸው ነው፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የባህል መብቶች አንፃር የመብቶቹን ጥሰት በገንዘብ በመተመን መካስ ይቻላል፡፡ አቅም እንደፈቀደና እያደር ዕውን የሚሆኑ መብቶችን ግን በአንዴ መካስ አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ለዘመናት በአንድ ቡድን ላይ የተፈጸመን ኢፍትሐዊ ተግባር በገንዘብ መካስ የተለመደ ነው፡፡ ገንዘቡ ለቡድኑ አባላት ለእያንዳንዳቸው ወይም በጥቅሉ ለቡድኑ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በተለይ በመገለላቸው ምክንያት በብዙ መልኩ ከሌሎች ወደኋላ የቀሩ፣ እንዲሁም ሀብታቸውን የተበዘበዙ ነባር ሕዝቦችን ይመለከታል፡፡

አገሮች ስለሰብዓዊ መብቶች የካሳ ሁኔታ በሕገ መንግሥታቸው ባያስቀምጡም እንኳን ጉዳዩ የሕግ የበላይነት ጋር አብሮ ተሰናስሎ የሚኖር ስለሆነ (የጣሰውን እየተው የሕግ የበላይነት ስለማይኖር)፣ የሰብዓዊነት ክብርና እኩልነት የሚመለከት በመሆኑ የካሳ ጉዳይ መለመድ ያለበት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ይሁን የክልሎቹ አንቀጽ 13 ላይ እንደገለጹት ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚው እንዲሁም ተርጓሚው የሰብዓዊ መብቶችን ከመጣስ በመቆጠብ ማክበር እንዳለባቸው ተቀምጧል፡፡ እነዚህ ተቋማት በሕግ ከተባለው በተቃራኒው በመጓዝ ሰብዓዊ መብቶችን ካላከበሩ፣ ብሎም ባለማክበራቸው የማይጠየቁና ላደረሱትም ጉዳት ኃላፊነት ከሌለባቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት መብቶች በአንድ ሌላ ተራ መጽሐፍ ላይ ከተዘረዘሩ መብቶች ልዩነት አይኖራቸውም፡፡

ከላይ በአጭሩ ለመቃኘት የተሞከረው ዜጎች የሰብዓዊ ወይም ሌሎች መብቶቻቸውን መንግሥት በተቋማቱ ወይም በሠራተኞቹ አማካይነት በሚጥስበት ጊዜ ሊኖር የሚችለውን የፍትሐ ብሔር መፍትሔ ነው፡፡ ይህንን አሠራር መከተል ሕግን ማክበር ነው እንጂ ብዙም ፖሊሲና ሌላ ነገር አያስፈልገውም፡፡ ሕግን ማክበር በራሱ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ፣ ጉዳት አድራሻዎችን ለመቅጣት ወይም ላለማበረታታት እንዲሁም ዜጎች በሕግ ላይ የሚኖራቸውን አመኔታን ለመጨመር ይረዳል፡፡

ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy