Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለኤርትራ መንግስት አዲስ ፖሊሲ?

0 1,232

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለኤርትራ መንግስት አዲስ ፖሊሲ? (ዳዊት ምትኩ)

የኤርትራ መንግስት ቀጠናውን አዋኪነት ከጎረቤቶቹ አንስቶ እስከ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድረስ በሚገባ የሚታወቅ ነው። በዚህም የተነሳ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁለት ጊዜ ማዕቀብ ጥሎበታል። እነዚህ ማዕቀቦች የኤርትራን መንግስት ከህዝቡ ነጥሎ የጎዱት ቢሆንም፤ አሁን ግን ከአረቦች ጋር በሚያደርገው ሽር ጉድና ወደቡን ለረጅም ጊዜ ማከራየቱን ተከትሎ ኪራይ ሰብሳቢ እጆቹ እየተንቀሳቀሱ ነው።

በዚህም ሳቢያ ከኤርትራ ጋር ድንበር የሚጋሩት የትግራይና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ህዝቦች ሻዕቢያ በሚያሰማራቸው ሰርጎ ገቦች ጋር በሚያደርጉት ግጭት መስዋዕት ይሆናሉ፣ ይቆስላሉ፣ ንብረታቸውም ይወድማል። እርግጥ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ለፓርላማ እነዚህን ህዝቦች አስመልክቶ “እጅግ ላመሰግናቸው እወዳለሁ” ብለዋል።

እንዲህ ዓይነቱ የመንግስት ዕውቅና እነዚያ ህዝቦች ከሻዕቢያ ሰርጎ ጎቦች ጋር በየጊዜው ላደረጉት ተጋድሎ ተገቢና ትክክል ነው። ሆኖም እነዚህ ህዝቦች ከሻዕቢያ ሰርጎ ገቦች ጋር በሚፈጥሩት ግጭት የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖርና የጀመሩትን ዕድገት ሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች በአስተማማኝ ሰላም ውስጥ ሆነው እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ለእኔ የዚህ ችግር ዋነኛ አሰማሪ የሆነው የኤርትራ መንግስት አደብ እንዲገዛ መደረግ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ሻዕቢያ የሀገራችን ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ያወጀውና በተግባርም ያሳየው ዛሬ አይደለም። ላለፋት አስራ አስራ ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ ይዞ ተንቀሳቅሷል፤ በቀጥተኛ ወረራ በመፈፀም፣ በሌላ በኩልም ይህ አልሳካ ሲለውም የሽብር ግንባር ፈጥሮ በመንቀሳቀስ። እነዚህ ሁሉ ልፋቶቹ ግን አንዳች ፍሬ አላስገኙለትም።

እንዲያውም እየተንኮታኮተና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተገለለ እርቃኑን እንዲቀር አድርገውታል። ያም ሆኖ ግን የአስመራው መንግስት በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት በሀገራችን ላይ “ከቁልቋል የተጠጋ አጋም” ሆኖ፤ ተጎራባች ክልሎቹን እያደማ ይገኛል። ሰላምን ሁሌም መርሁ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት በእነዚህ ጊዜያት አቅሙ ቢኖረውም እንኳን ‘የኤርትራው ቡድን ተስፋ ቆርጧል፤ ከዓለምም ተገልሏል’ በሚል ለወረራ አልተነሳሳም። ይህን ያላደረገው ደግሞ አስታዋሽ ስላልነበረው አልያም ተቀባይነትን አጣለው ብሎ በመስጋት አይደለም። ተቃዋሚዎች ከምንም በላይ መንግስት በኤርትራ ላይ ዘመቻ እንዲያካሄድ ሲወተውቱት ቆይተዋል። በሻዕቢያ ላይ ዘመቻ ለማካሄድ ተጨባጭ ምክንያት ስለሌለው ታቅቦ የኖረ አለመሆኑም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአካባቢዎቹ ባደረጉት ጉብኝትም ህዝቡ የኤርትራ መንግስትን የኢፌዴሪ መንግስት አደብ እንዲያስገዛለት ጠይቋል።

ሆኖም መንግስት ሻዕቢያ አሸባሪ በመሆኑ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሃገሩ ህዝብ አይጠቅምም፤ ይህን መንግስት ልጨርሰውና እፎይታን እናግኝ ብሎ አልተንቀሳቀሰም። ግና ከማተራመስ  እንቅስቃሴው እንዲታቀብ የዲኘሎማሲያዊ ስራዎች ላይ አተኩሮ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በዚህ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት አጋጣሚ ዝግ እስካልሆነ ድረስ፤ ይህ አማራጭ ከምንም በላይ ተመራጭነት የሆነ ፖሊሲ ነው ብሎ ተንቀሳቅሷል። መንግስትም ለሰላማዊ ድርድሮች ቅድሚያ መስጠቱ ታጋሽነቱንና አርቆ አሳቢነቱን የማያሳይ ነው። ይሁንና ሻዕቢያ ትንኮሳን በየጊዜው እያካሄደ፤የኢትዮጵያ መንግስት ሁሌም በዚሁ ሁኔታ መቀጠል ያለበት አይመስለኝም። ይህን ስል ግን መንግስት አስመራ ሄዶ የአስመራውን የሽብር አለቃ መንግስት ያስወግድ ማለት አይደለም።

እንደ መንግስት ፍላጎት በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ቢቻል ሌላው የኤርትራ ህዝብ ፍላጎትና ውሳኔን የሚጠይቅ ብቻ ይሆናል። ይህም ማለት የኤርትራ መንግስት በሃገራችን ላይ ከሚያካሄደው የሽብር ዘመቻ መታቀብ ከቻለ፤ ኢትዮጵያ በኤርትራ የውስጥ ጉዳይ የሚመለከታት ጉዳይ አይኖርም። ሻዕቢያ በራሱ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ከልክ ያለፈ በደል የማስቆም፣ ስርዓቱን የመቀየርና መንግስቱን የማስወገድ ወዘተ፡ ተግባር የህዝቡን ውሳኔ ብቻ የሚጠይቅ ነው።

ይህ የመንግስት ፍላጎትና አቋም ደግሞ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን የፀና ይመስለኛል—ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “የተመጣጣኝ እርምጃው ፖሊሲ ካላስኬደ ሌላ ፖሊሲ የምንከተል ይሆናል” በማለት እስከገለፁበት ጊዜ ድረስ። እርሳቸው እንዳሉት አዲሱ ፖሊሲ በጥናት ላይ ስለሆነ ከወዲሁ ምንም ማለት ባይቻልም፤ የአጎራባች ክልሎችን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ የሚደግፍና ሻዕቢያንም አደብ የሚያስገዛ ሊሆን ይገባዋል።

የኤርትራ መንግስት በተለያዩ ወቅቶች በአጎራባቾቹ ክልሎች ላይ ጉዳት ማስከተሉን ተከትሎ እስካሁን መንግስት የወሰደው አቋም በግልፅ የሚያመለክተው ነገር፤ የአንዲትን ሉዓላዊት ሀገር ድንበር በመጣስ በኤርትራ ላይ ወረራን ለመፈፀምም ሆነ የዚያችን ሀገር አምባገነኖች እስከመጨረሻው ለመደምሰስ ፍላጎት የሌለው መሆኑን ነው። ምክንያቱም ካለፉት ተሞክሮዎቹ ስንመለከተው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፍ ህግን ተመርኩዞ የሚመራና ለዚህም በፅናት የሚሰራ ስለሆነ ነው ።

ይህ ማለት ግን የአቶ ኢሳያስ ሽብርተኞችን መሪ መንግስት እያደረሰ ላለው ጥፋት ተመጣጣኝ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ ይላል ማለት ግን አይደለም። ሻዕቢያ በማን አለብኝነት የሀገራችንን ሰላምና የተጀመረውን ፈጣን ልማታዊ ዕድገት በማደናቀፍ ሲቀጥል፤ መንግስት በተመጣጣኝ እርምጃው ተገቢውን ቅጣት እየሰጠው መጥቷል። ይህም የኤርትራ መንግስት ቢያንስ ከትንኮሳው ለተወሰኑ ወቅቶች እንዲታቀብ አድርጎታል።

መንግስት ሻዕቢያ ለሚፈጽመው ጥቃት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱ፤ በእርምጃው የዚያችን ሀገር ዜጎች ሉዓላዊ መብት በመጋፋት የአቶ ኢሳያስን ቡድን ለማስወገድ ያሰበበት ጊዜ የለም፡፡ ድርጊቱ ተደጋጋሚና በልማት ስራዎች፣ በመልካም ገፅታችን ብሎም በሕዝብ ሰላም ላይ የተደቀነ አደገኛ አደጋ ስለሆነ የኤርትራው መንግስት ለፈፀመው ጥፋት ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት የሚል ሚዛናዊ እሳቤን ተንተርሶ ተመጣጣኝ ቅጣቱን የተከተለው ለዚሁ ይመስለኛል።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራን ህዝብ ተክቶ ሻዕቢያን ሊያስወግደው አይችልም፤ ፍላጎትም የለውም። ከዴሞክራሲያዊ እሳቤ አኳያም ሁኔታውን ስንመለከተው፤ ሻዕቢያ እንዲቀጥልም ሆነ እንዲወገድ ወሳኙ የኤርትራ ህዝብ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አይደሉም። እናም በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰበ የሚመራ መንግስት በአንድ ሀገር ውስጥ ጣልቃ በመግባት የመንግስት ሿሚና ሻሪ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ዓይነት መንገድ ወንድም የሆነውን የኤርትራን ህዝብ የማይገሰስ መብት የሚጋፋ ነው። የዓለም ህዝብም አይደግፈውም።  

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለ በዴሞክራሲያዊ መርህ የሚመራ አገር እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ አይከተልም። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በገለልተኝነት መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑም፤ በኤርትራም ይሁን በየትኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም። ይህ መርህም እካሁን ድረስ ሀገራችን በኤርትራ መንግስት ላይ የምትከተለውን የተመጣጣኝ እርምጃ ፖሊሲን አጠንክራ እንድትቀጥል አድርጓታል። ያም ሆኖ የሻዕቢያ አጎራባች ክልል ህዝቦች ‘ሻዕቢያ እያደማን ነው’ እያሉ ነው። ይህ የህዝብ ጥያቄ ደግሞ በተገቢው መንገድ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጥናት ላይ የሚመሰረተውንና ሌላ መንገድ እንከተላለን ያሉትን አዲስ ፖሊሲ በመንደፍ ለፓርላማ ለማስፀደቅ የሚያቀርቡበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል ብዬ አላስብም። ሰላም!   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy