Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለ12 ዓመታት በጅምር ቀርቶ ከጥቅም ውጪ የሆነው ኮንዶሚኒየም

0 533

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ በጀመረበት 1997 .ም ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ በተለምዶ ኳስ ሜዳ በሚባለው አካባቢ የስምንት ብሎኮች ግንባታ ተጀምሮ የሰባቱ ግንባታ ተጠናቆ ለልማት ተነሽዎች ተላልፏል። የአንደኛው ህንፃ ግንባታ ግን ከመጀመሪያው ወለል የዘለለ ግንባታ ሳይከናወንበት ተቋርጧል። ይህ በጅምር የቀረው ኮንዶሚኒየም አስታዋሽ አጥቶ እነሆ ለ12 ዓመታት እንደቆመ ቀርቶ በፀሐይና ዝናብ ከጥቅም ውጪ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይኸው ጅምር ኮንዶሚኒየም ባለበት ግቢ ውስጥ የሚገኘው የሳይት 1 የጋራ መኖሪያ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ በርሄ ሰይድ እንደተናገሩት፣ ወደ ኮንዶሚኒየም ከገቡ ጀምሮ አንዱ ህንፃ በጅምር ቆሞ በዝናብና ፀሐይ ከጥቅም ውጪ ሆኗል። የወረዳው ነዋሪዎችም ለአስተዳደሩ በተደጋጋሚ ምክንያቱ ምን እንደሆነና ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄ ቢያቀርቡም «ተቋራጩ ጠፍቷል»

እና «አያገባችሁም» ከሚል ያለፈ ምላሽ አላገኙም። የቤት ችግር መንግሥትና ህዝብን መተንፈሻ ባሳጡበት በአሁኑ ወቅት ይሄ በጅምር የቀረ ኮንዶሚኒየም መዘንጋቱና ከጥቅም ውጪ መሆኑ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነው።

«በጅምር ቆሞ ከጥቅም ውጪ የሆነው ህንፃ «የእኔ ነው» የሚል አካል እስካሁን አልቀረበም። መንግሥትም ዝም ብሏል። የወረዳው አስተዳደርም እስካሁን ኃላፊነቱን አልተወጣም። ይህ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ነው፤ እኛ የአቅማችንን አድርገናል እናንተን የሚሰማ ካለ ለህዝብ አሰሙ» ብለዋል አቶ በርሄ።

ሌላኛዋ የማህበሩ አባል የሆኑት ወይዘሮ የሱነሽ አዱኛ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ እርሳቸውና ሌሎች የግቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ጅምሩ ህንፃ እንደቆመ አለ። የህንጻው የመጀመሪያ ወለል በሌቦችና በተለያየ ምክንያት ፈርሶ ብረቱ ተሰርቋል፡፡ ለአካባቢው ወረዳ አቤት ቢሉም ምንም መፍትሄ አልተገኘም፡፡

«ለነዋሪዎች የሚያገለግል የሸማቾች ሱቅ ለማዘጋጀትና ለሌሎች አገልግሎቶች በጋራ እንጠቀምበት የሚል ጥያቄ ለወረዳ ብናቀርብም ከልክሎናል፡፡ የግቢው ነዋሪም ህንጻውን የከሰል ማስቀመጫና መፀዳጃ አድርገውታል። ለነዋሪዎች ደህንነትና ጤናም አስጊ ሲሆን፣ በጭቅጭቅ ሰው እንዳይገባበት ታጥሯል፡፡ ለእነዚህን ያህል ዓመታት ብዙ ጥቅም መስጠት የሚችል ቤት አስተዋሽ በማጣቱ ባክኖ ቀርቷል» ብለዋል ወይዘሮ የሱነሽ።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተመስገን ኃይለማርያም፣ ህንፃው በ1997 .ም የኮንዶሚኒየም ግንባታ ጋር አብሮ መካሄድ እንደጀመረ፤ ነገርግን ዲዛይኑ ተቀይሮ ለንግድ እንዲውል ተወስኖ ግንባታው መጀመሩን ይናገራሉ። «እኛ የምናውቀው ተገንብቶ መቆሙን እንጂ፣ ማን ሲገነባ እንደነበር፣ ለምን እንደቆመ፣ ባለስንት ወለል ህንጻም እንደነበረ የምናውቀው ነገር የለም» ብለዋል።

ከህዝቡ የሚነሳውን አቤቱታ በመያዝ ስለህንፃው ብዙ ጊዜ ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና በዚህ አካባቢ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሆኑት የምክር ቤት አባል ችግሩን እንዳሳወቁና እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሄ እንዳልተሰጠው አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

የህንፃው ግንባታ የቆመው ከይዞታ መረጋገጥ ጋር ተያይዞ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት እንዳላቸውም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በግቢው ውስጥ ካሳ የተከፈላቸውም ያልተከፈላቸውም ነዋሪዎች እንደሚገኙ አንስተው፣ ይህ እልባት ባለማግኘቱና አነስተኛ ሳይት በመሆኑም የተረሳ እንደመሰላቸው ገልጸዋል።

እንደ አቶ ተመስገን ገለጻም፣ ወረዳው ችግሩን ከማሳሰብ ውጪ መፍትሄ መስጠት አይችልም። ችግሩን ለመፍታት የሚችለው የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ነው። ህንፃው አሁን ባለው ሁኔታ በፀሐይና በዝናብ ምክንያት ከጥቅም ውጪ ስለሆነ ግንባታውን ማስቀጠል አይቻልም።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽፈት ቤት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ ጋሻው ተፈራ ጉዳዩን ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄውን ካቀረበ በኋላ ከክፍለ ከተማውና ከጽህፈት ቤቱ የተውጣጣ ቡድን ለማጣራት መሞከሩን ተናግረው፤ በዲዛይኑ መሰረት ህንፃው መገንባት ያለበት በኤል ቅርጽ ስለሆነና የተወሰነ የህንፃው ክፍል የሚገነባበት ቦታ ላይ ነዋሪዎች ካሳ ቢከፈላቸውም ስላልተነሱ ግንባታው በጅምር መቅረቱ ተረጋግጧል ብለዋል።

እንደ አቶ ጋሻው ገለጻም፤ በዲዛይኑ መሰረት በዚያው ግቢ ውስጥ መገንባት የነበረባቸው ሌሎች አምስት ህንጻዎችም ከዚሁ ከተነሽዎች ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት ሳይገነቡ ቀርተዋል። የተገነቡትን፣ በጅምር የቀረውንና ሌሎች ካሳ ተከፍሎባቸው ያሉትን ቦታዎች ባሉበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ግንባታውን ሲያከናውን ከነበረው ከጂቲዜድ ርክክብ አድርጎ ወጥቷል። ስለሆነም ተጠያቂው ፕሮጀክት ጽፈት ቤቱ ሳይሆን በወቅቱ ግንባታውን ያካሄደው ጂቲዜድ ነው።

በቀጣይ ከክፍለ ከተማው ጋር በመሆን ካሳ የተከፈላቸውንና ያልተከፈላቸውን በማጣራት ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን። የቤቶቹን ግንባታም እናስቀጥላለንሲሉም ነው አቶ ጋሻው የተናገሩት። addiszemen

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy