Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልማታዊ ባለሀብቶችን በአግባቡ በማስተናገድ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን ይገባል… የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር

0 869

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልማታዊ ባለሀብቶችን በአግባቡ ከማስተናገድ ባለፈ እውቀትና ልምድ በመቅሰም የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።የክልሉ ምክር ቤት በስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ የዛሬ ውሎው በአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ ሪፖርቱን አጽድቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጉባኤው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ባለፉት ወራት በድርጅትና በመንግስት የተካሄደው የተሃድሶ ንቅናቄ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር አስችሏል።

የተፈጠረው አደረጃጀት በክልሉ ለሰላም መታጣትና አለመረጋገት ምክንያት የነበረውን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ፈጥኖ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ወደክልሉ ለልማት የሚመጡ ባለሀብቶችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ገዱ፣ በዚህም ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ እውቀትና ልምድ በመቅሰም የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሂደት መሰረተ ሰፊና አገር በቀል ኢንዱስትሪ ለመገንባት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶችን ውጤታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

“ልማታዊ ባለሀብቶችን ፈጥነው የማያስተናግዱ አመራሮችና ባለሙያዎች ካሉ እያደናቀፉ ያሉት የህዝቡን የመልማት ፍላጎት፣ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራና የገቢ እቅምን በመሆኑ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል” ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በየዓመቱ ውስን ሞዴል አርሶአደሮችን ከመቁጠር ባለፈ በርካታ ሞዴሎች በየዘርፉ እንዲኖሩ የቀጣይ ተግባር መሆን እንዳለበትም አቶ ገዱ አሳስበዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ባህል እየሆነ የመጣውን የቅንጅት፣ የነቃ ተሳትፎና በስፋት መተግባር ወደ ዘላቂነትና ሕዝባዊ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር የምክር ቤት አበላት የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አቶ ገዱ እንዳሉት፣ በክልሉ ምዕራባማ ወረዳዎች የሚስተዋለው ሰፊ የደን ጭፍጨፋ የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትል በመሆኑ ለማስቆም ተገቢ ርምጃ ይወሰዳል።

ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የካሳና መሰል ችግሮችን ለመፍታትም አርሶአደሩ የመሬት ባለቤትነት መብቱ እንዲረጋግጥለት መንግስትን መጠየቅ እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በከተሞች የሚስተዋለው ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዲገታም ህጋዊ አማራጮችን በማስፋት ለሕገወጦች የማይደራደር የከተማ አመራር ለመፍጠር ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የወረዳና ቀበሌ ይከፈልልን እንዲሁም የከተማ ደረጃ ይደግልን በሚል ወደምክር ቤቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች “የክልሉ መንግስት ባለፈው ዓመት በጥናት ላይ ተመስርቶ ተገቢ ምላሽ በመስጠቱ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ አይቻልም” ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው፣ የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚ አካሉ ባቀረበው ዕቅድ መሰረት መፈጸም አለመፈጸሙን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሕብረተሰቡ ከዕቅድ ውጭ ጥያቄዎችን ሲያነሳም ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመሆን ከክልሉ አቅም ጋር እየተገናዘበ በሂደት የሚፈታ መሆኑን ማስረዳት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በከሰዓት ውሎው የዳኝነት አካሉን ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን በነገው ዕለትም የተለያዩ ሹመቶችንና አዋጆችን በማጽደቅ እንዲሁም ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy