Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹መታገል ያለብን ራሱን ለመጥቀም የሚሠራውን አመራር ነው››

0 1,516

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቶ ዘነበ ኩሞ፣ የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

ቀድሞ የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ ተብሎ ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 372/2008 ሁለት ቦታ ተከፍሏል፡፡ ተጠሪነቱ ለከተማ ልማት ሚኒስቴር የሆነው የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲም በደንብ ቁጥር 374/2008 ተቋቁሟል፡፡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ማኑፋክቸሪንግ ኤጀንሲ ሁለተኛው ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ አቶ ዘነበ ኩሞ የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአካውንቲንግ በኋላም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ በኤጀንሲው ከሰኔ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እያገለገሉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት ነበሩ፡፡ በሲዳማ ዞን በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት እርከኖች በኋላም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተወዳድረው በመመረጣቸው ለሁለት ዙር የፓርላማ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን የሚመሩት ኤጀንሲ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ ነው፡፡ ከ10 ዓመት ወዲህ በተጀመረው የሥራ ዕድል ፈጠራ በአገሪቱ ካሉት ሥራ አጥ ወጣቶች ውስጥ መድረስ የተቻለውን በተለያዩ የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ማሰማራት መቻሉ ይነገራል፡፡ በመንግሥት በኩል በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በምርትና በአገልግሎት ዘርፍም ሥራ አጥ ወጣቶች ተሰማርተው እንዲሠሩ ድጋፍ ቢደረግም፣ በአንዳንዶቹ አሠራሮች ላይ ክፍተትና ኪራይ ሰብሳቢነት መታየቱ በተለያዩ መድረኮች ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ በአንዳንድ ሥፍራዎች ከ2008 ዓ.ም. ኅዳር ጀምሮ በ2009 ዓ.ም. መስከረም መገባደጃ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከታወጀበት ድረስ ለነበረው አለመረጋጋት፣ ለጠፋው ንብረትና ለተመዘገበው ሞት እንደ አንድ ምክንያት የተነሳው የሥራ አጥ ወጣቶችን ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህም ጥልቅ ተሃድሶን ጨምሮ በተለያዩ የመወያያ መድረኮች ተነስቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የወጣቱን የሥራ ዕድል ለማስፋትና ለመደጐም ያስችለኛል ያለውን የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀድቋል፡፡ ከዚህ በፊት በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ያጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ምን ተደርጓል? የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድርስ እንዴት ለወጣቱ ለማድረስ ታስቧል? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምሕረት ሞገስ ከአቶ ዘነበ ኩሞ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በበጀት ዓመቱ ምን ያህል ሥራ ፈላጊዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ ነው ወደ ሥራ የተገባው?

አቶ ዘነበ፡- ለሥራ አጦች በየትምህርት ደረጃቸውና አካባቢያቸው፣ ቤት ለቤት እየተካሄደም ጭምር ምዝገባ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ለተመዘገቡት ሥልጠና እየተሰጠ ተለይተው በተቀመጡት አምስት ዕድገት ተኮር ዘርፎች በምርጫቸው በኢንተርፕራይዝ እንዲደራጁ ይደረጋል፡፡ ኢንተርፕራይዝ የሚመሠርቱት ባለቤቱንና ተቀጣሪውን ጭምር ይዘው አምስት በመሆኑ ነው፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ካፒታሉ 50 ሺሕ ብር ሲሆን፣ በኢንዱስትሪው እስከ 100 ሺሕ ብር ካፒታል ማንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ ይህ ታሳቢ ተደርጐ በበጀት ዓመቱ ይፈጠራል ተብሎ የታቀደው የሥራ ዕድል ለ2.1 ሚሊዮን ዜጎች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ2009 በጀት ዓመት ለ2.1 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መነሻው ምን ነበር?

አቶ ዘነበ፡- ቁጥሩን የያዝነው ዝም ብለን በይሆናል ሳይሆን፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየአምስት ዓመቱ የሚሠራቸውን ትንበያዎች መነሻ አድርገን ነው፡፡ የስድስት ወራትን የሥራ አፈጻጸም በዘርፍ ጉባዔ እንደገመገምነው 940 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም ትልቁን ድርሻ ይዞ የሚገኘው ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ነው፡፡ መሆን የሚገባው ግን ቋሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?

አቶ ዘነበ፡- መንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አሉት፡፡ በእነዚህ ለአምስት ወይም ለስድስት ወራት ብቻ የሚሠሩ ይኖራሉ፡፡ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች በጊዜያዊ የሥራ ፈጠራ ተካተዋል፡፡ በመንግሥት ግዙፍ ግንባታዎች ውስጥ አንዳንዱ በጉልበት ሲሰማራ፣ ሰብ ኮንትራት ወስደው የሚሠሩ ኢንተርፕራይዞችም አሉ፡፡ የኤሌክትሪክ፣ የቧንቧ ውኃና የባቡር መስመር ዝርጋታና የልሰና ሥራ አለ፡፡ ፕሮጀክቱ እስኪያልቅ በጊዜያዊነት በእነዚህ ይሰማራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት በጊዜያዊነት የተሰማሩት ናቸው ብለዋል፡፡ ምን ያህል ይሆናሉ? ወደ ቋሚነት ለማሸጋገርስ ኤጀንሲው ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዘነበ፡- ወደ 60 በመቶ ያህሉ ጊዜያዊ ናቸው፡፡ ይህ ወደ ቋሚነት እንዲመጡ መሥራት እንዳለብን ያሳያል፡፡ ስለሆነም ኤጀንሲው የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ያገኙትን ሀብት እንዲቆጥቡ የማድረግ ሥራ አለው፡፡ የብድር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ የሥልጠናና የቦታ ድጋፎች ይሰጣል፡፡ ትልቁ ሥራ አድርገን የምንንቀሳቀሰውም ጊዜያዊዎቹን ወደ ቋሚ ለማምጣትና ለማደራጀት ነው፡፡ ለምሳሌ በኮብልስቶን ማለትም በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና ጠረባ የሚሰማሩ አሉ፡፡ ይህ ጊዜያዊ ነው፡፡ ከዚህ የሚያገኙትን ገንዘብ ቆጥበው እንደ እርሾ እንዲይዙና በኋላም ከመንግሥት በሚያገኙት ተጨማሪ ድጋፍ ወደ ሌላ እንዲሸጋገሩ ነው፡፡ ፅዳትና ውበት ላይ የሚሰማሩም ቢሆኑ እንዲሁ፡፡ ትልቅ ፈተና ቢሆንም ትኩረት ሰጥተን እየሠራንበት ነው፡፡ እንደ ክፍተትም የገመገምነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብድር ማመቻቸት ላይ ከዋስትና ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክፍተቶች አሉ፡፡ የሚደራጁ ወጣቶች እርስ በርስ እንዲዋዋሱ ቢቀመጥም፣ እውነታው ይህ አይደለም፡፡ ዋሶችም የቅጥር መታወቂያ ያላቸው እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም አልፎ የቤት ካርታና የመኪና ሊብሬ ድረስ ይሄዳል፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐንም ቅድመ ቁጠባ ለምሳሌ 50 ሺሕ ብር ለመበደር 10 ሺሕ ብር ቀድመው እንዲቆጥቡ ይጠየቃሉ፡፡ ይህን ማድረግ የማይችሉ ስለመሆናቸው በተለያዩ መድረኮች የተገኙ ወጣቶች ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች እንዴት እያያችኋቸው ነው?

አቶ ዘነበ፡- ከስትራቴጂው ስንነሳ ሥራ ፈላጊ የሆኑ ዜጎች በየደረጃው ተደራጅተው ሥራ የሚገቡ ከሆነ ቢያንስ 20 በመቶ ቅድመ ብድር ቁጠባ መቆጠብ አለባቸው ይላል፡፡ ይህ ግን ዜሮ ቁጠባንም አይዘጋውም፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ የወላጆች አቅም ይታወቃል፡፡ ሥራ ለመፈለግ የሚደራጀውን ወጣትም ሆነ የሌላውን ኅብረተሰብ ክፍል አቅም የምናውቀው ነው፡፡ ስለሆነም ያለምንም ቅድመ ብድር ቁጠባ ወደ ሥራ የሚሰማሩበት መስክ ተለይቷል፡፡ መሠረታዊው ነጥብ ምንም መቆጠብ የማይችሉትን ለይቶ አምስቱ የዕድገት ተኮር ዘርፎች ካልናቸው ያለምንም ቅድመ ቁጠባ መሥራት በሚችሉባቸው መስኮች ለማስገባት የተሄደ ርቀት ቢኖርም እዚህ ላይ ችግር ያለ መሆኑ ነው፡፡ የአገልግሎት፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የከተማ ግብርና፣ የተቀናጀ የከተማ ተፋሰስና ልማት እንዲሁም የአረንጓዴ ፅዳትና ውበት አምስቱ ዘርፎች ናቸው፡፡ ጌጠኛ ድንጋይ እንዲሁም የተቀናጀ የከተማ ተፋሰስና ልማት ውስጥ ተደራጅቶ ያለምንም ቅድመ ቁጠባ መሥራት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የጌጠኛ ድንጋይ ጠረባና ንጣፍን ስናይ የአመለካከት ችግር ነበር፡፡ ሆኖም እዚህ ላይ ተሰማርተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ አሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ያልተጠቀሙ አሉ፡፡ ሌላው ችግር እነዚህ መቆጠብ አይችሉም ተብለው የተለዩ ዜጎች መቆጠብ በማይጠበቅበት ዘርፍ እንዳይገቡ፣ ቀድመው የገቡት እዚያው መቆየታቸውና ያለመሸጋገራቸው ነው፡፡ በትግራይ በጌጠኛ ድንጋይ ጠረባና ንጣፍ የሚቆዩበት ጊዜ ትልቁ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ነው፡፡ መቶ በመቶ ይቆጥባሉ፡፡ ሌላ ሥራ መሥራት ያለበት ዜጋ አለ የሚለው ላይ የአስተሳሰብ ሥራ ስለተሠራ ያገኙትን እንደ መነሻ ይዘው ወደ ብድር ሥርዓት ይገባሉ፡፡ ሆኖም የማይሸጋገሩና የማይቀየሩም አሉ፡፡ ይህ ወደ ዜሮ ቁጠባ የሥራ ዕድል ለመግባት አንዱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን አይተናል፡፡

ሌላው በስትራቴጂው ላይ ምንም መቆጠብ ለማይችል ተብሎ በተቀመጠው መሥፈርት ሥራ አጡን ከማሰማራት ይልቅ፣ ጥራትን እንደ ምክንያት በማንሳት ኮንትራክተር ቀጥረው በኮንትራት የሚያሠሩ አካባቢዎች መኖራቸውን ኤጀንሲው ባደረገው ምርመራ አረጋግጧል፡፡ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብም እንደ አንድ መንቀሳቀሻ ተደርጐ የሚወሰድ ሲሆን፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በዚህ ተሰማርተው ሀብት ያፈሩ አሉ፡፡ የዜሮ ቁጠባ ዕድል ቢኖርም በአግባቡ አለመጠቀማችን እንደ ክፍተት ታይቷል፡፡ ከብድር ጋር ለተያያዘው መሠረታዊ ጥያቄ ማይክሮ ፋይናንስ ለኢንተርፕራይዞቹ የብድር ተቋማት ናቸው፡፡ የዓለም ልምድ የሚያሳየው ማይክሮ ፋይናንሶች ከመነሻው የሚቋቋሙት ምንም ማስያዝና ዋስትና ማቅረብ የማይችሉ እንዲጠቀሙበት ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን አሠራሩ እንደዚህ ነው ወይ ቢባል አይደለም፡፡

ይህንን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የብሔራዊ ባንክ ገዢው ባሉበት ታይቷል፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች የተቋቋሙት ኢንተርፕራይዞች ያቀረቡት የንግድ ዕቅድ መነሻ ተደርጎ የጠለፋ ዋስትና ገብተው እንዲበደሩ ነው፡፡ የሚደረገው ግን በተገላቢጦሽ የመኪና ሊብሬና የቤት ካርታ ማስያዝ ነው፡፡ እኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችና ሥራ ፈላጊ ወጣቶች፣ እንዲሁም ወላጅም ዘንድ ስንቀርብ የመኪና ሊብሬና የቤት ካርታ ካለን ለምን ወደማይክሮ ፋይናንስ እንሄዳለን? ባንክ መሄድ እንችላለን ያሉበት ጊዜም አለ፡፡ ስለሆነም አሠራሩ ከዓለም አቀፍ ደረጃም አንፃር የማይሄድ ስለሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አቅጣጫ፣ ማይክሮ ፋይናንሶች የሥራ ፈላጊዎችን የሥራ ዕቅድ ገምግመው፣ አዋጭነቱን አይተውና እገዛ ተደርጎላቸው የቡድን ወይም የጠለፋ ዋስትና እርስ በርስ ገብተው ብድር እንዲሰጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ በመመርያ ወርዷል? ምክንያቱም በቅርብ ቀናት ውስጥ ሌሎችን ዋስ አድርገው ብድር ያገኙ የኢንተርፕራይዝ አባላት አግኝተናል፡፡

አቶ ዘነበ፡- ይህ ባለፈው ዓርብ [የካቲት 10 ቀን 2009 ዓ.ም.] የብሔራዊ ባንክ ገዢው ባሉበት ነው የተባለው፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ፈቃድ ሲያገኙ የሚገቡት ውል አለ፡፡ ሆኖም በውሉ የመሥራት ክፍተት አለ፡፡ አሁን ግን ከወጣቶች የ10 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ጋር ተያይዞ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ እስካሁን የሄድንበት ርቀት ግን ትክክል አልነበረም፡፡ ባንኮችም ማይክሮ ፋይናንሶችም ከስረው ወደ ቤት መግባት የለባቸውም፡፡ በሌላ በኩል ሥራ ፈላጊዎች መቆጠብ ካልቻሉ የከተሞች አስተዳደሮች የብድር ዋስትና የሚገቡበት ሥርዓት አለ፡፡ ሆኖም የከተሞችን የብድር ዋስትና ፈንድ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩ ተገምግሟል፡፡ እያንዳንዱ ከተማ የብድር ዋስትና ፈንድ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ይህ ምንም መቆጠብ ለማይችሉ የከተማ አስተዳደሩ በተለይ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይ ለምሳሌ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ዋስትና ገብቶ ብድር እንዲገኝ እንዲያደርግ ስትራቴጂው ላይ ተቀምጧል፡፡ ትልቁ ክፍተት ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ያነሳሽው ጥያቄና እኛም ያወቅነው፣ ማወቅም ብቻ ሳይሆን መስተካከል አለበት ብለን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርገንበታል፡፡ አሁን ግን አቅጣጫ ስለተቀመጠ ይገዛናል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶች ሲደራጁና ሲሠሩ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ነው፡፡ ሆኖም በአምስት ወይም በአሥር ተደራጅተው ሥራውን በራሳቸው ብቻ ይሠራሉ፡፡ ሌሎችን እንዲቀጥሩና ሥራቸው ተመጋጋቢና ተቀባባይ ሆኖ ወደ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት ለማድረስ ምን ታቅዷል?

አቶ ዘነበ፡- ዕድገት የሚኖር ከሆነ የእሴት ሰንሰለቱን የማርዘም ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ሌሎች አገሮች እየሄዱበት ያለው ሁኔታም ይህንኑ ያሳያል፡፡ አሁን የተጀመረውንም ስናይ ለምሳሌ ጫማ በማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አሉ፡፡ ሶሉም፣ ቆዳውም፣ ማሰሪያውም [ከተለያየ ቦታ የሚገዛ ቢሆንም] አንድ ቦታ ነው ተገጣጥሞ የሚያልቀው፡፡ ሆኖም የእሴት ሰንሰለቱ ስትራቴጂው ላይ አለ፡፡ ይህን መነሻ አድርገን ስናይ ለምሳሌ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በጅምላ ስንሄድ ነበር፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ በነበረ ጊዜ ጥቃቅኑንም፣ አነስተኛና መካከለኛውንም ነበር የሚሠራው፡፡ አሁን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከእኛ ኤጀንሲ ካፒታላቸው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ወደ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በፊት ሲሸጋገሩ ይሸጋገራሉ እንጂ ያንን ሽግግር ይዘው ወደሚቀጥለው ሊመራቸው የሚችል ባለቤት አልነበረም፡፡ ከተሸጋገሩም በኋላ ወደ ኋላ የሚመለሱበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከጥቃቅን ተነስቶ ወደ ታዳጊና መካከለኛ ካፒታል ሲሸጋገር እዚህ ጋ ተቀብሎ የሚደግፈው ባለመኖሩ የመጨረሻ ውጤት ላይ ክፍተት መኖሩን መንግሥት ገምግሟል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህንን በባለቤትነት ሊከታተል የሚችልና ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሆነ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጀንሲ ማኑፋክቸሪንጉን ይዞ እንዲሠራ አቋቁሟል፡፡

ሪፖርተር፡- ሲሸጋገሩ ማለት ነው?

አቶ ዘነበ፡- አዎ፡፡ እኛ ከታች እናመጣለን፡፡ ካሸጋገርን በኋላ ቀጥሎ ያለውን ድጋፍ አንሰጥም፡፡ ክትትሉም ምን እንደሆነ አይታወቅም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ነው ልጆቹ መጀመሪያ ከተደራጁበት መሸጋገር የማይፈልጉት?

አቶ ዘነበ፡- አይፈልጉም፡፡ ይህም ችግር በጥናት ተጠንቶ ምላሽ የተሰጠበት ነው፡፡ ከአሁን በኋላ የእኛ ኤጀንሲና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን የሚመራው እየተመጋገብን በጋራ እንሠራለን፡፡ የጋራ ዕቅድም አለን፡፡ ወደሚቀጥለው ደረጃ የምናሸጋግረው በጋራ ገምግመን፣ በጋራ ድጋፍ አድርገን፣ ኦዲት ተደርጐ ብቁ ናቸው ስንል ነው፡፡ ስትራቴጂው ላይ የተቀመጠው የመንግሥት ድጋፍ በጥቃቅን ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ለአምስት ዓመት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መሸጋገር አለባቸው፡፡ አሁን ያለው መሸጋገር ሳይሆን ቦታውንም ይዘው የመቆየትና ካፒታላቸውን የመደበቅ ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ በበቂ ሁኔታ ስላልደገፍናቸው መሸጋገር የማይችሉም አሉ፡፡ ችግር ነው፡፡ ችግር ሆኖ መቀጠል ግን የለበትም፡፡ ባለቤት ተበጅቶለት ይህ ባለቤት ወደሚቀጥለው ደረጃ ሲሸጋገሩ ከልማት ባንክም ጭምር የሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየክልሉ እየሄደበት ነው፡፡ አሁን ሲደራጁ ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ ያለውንም ደረጃ እንዲያውቁ ጭምር በሥልጠና የማገዝ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ጠንክረን ከሠራን ለውጥ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሼድ ያላቸው ሲሸጋገሩ ስለሚለቁ መሥሪያ ቦታ አናገኝም ብለው ይፈራሉ፡፡ ማኑፋክቸሪንጉን የሚይዘው ኤጀንሲ ይህንንም ችግር ይፈታዋል?

አቶ ዘነበ– ትክክል ነው ይፈራሉ፡፡ ኤጀንሲው ይህንንም ይፈታል፡፡ ሲሸጋገሩም የት እንገባለን ብለው አያስቡም፡፡ ወደሚቀጥለው ደረጃ ሲሄዱ የተገነባ ሕንፃ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሙሉ ፓኬጅ ይጠብቃቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሙሉ ፓኬጅ ፕሮጀክት መቅረፅን ጨምሮ ዘርፉ ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች የሚገጥማቸውን ችግር የሚቀርፍ ነው? ምክንያቱም ልማት ባንክ ለብድር ሲደርሱ የተዋጣለት የንግድ ፕሮፖዛል ይዘው ካልሄዱ ተቀባይነት አያገኙም፡፡ ሊዝ ፋይናንስ ጊዜ የሚፈጅና አሰልቺ ምልልስ ያለው ነው፡፡ ኤጀንሲውም ሆነ ፓኬጁ ይህንን የሚያቃልል ይሆናል?

አቶ ዘነበ፡- በዋናነት ወደ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሸጋገሩ ብቻ ሳይሆን፣ እኛ ጋም ሲጀምሩ የንግድ ዕቅድ ይሥሩ ቢባል ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁትም ቢሆኑ ንድፈ ሐሳቡን እንጂ በተግባር ስለማያውቁት ይቸገራሉ፡፡ በእኛ በኩል በማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ያሉ ባለሙያዎቻችን ይህንን አገልግሎት መስጠት አለባቸው ብለናል፡፡ በመሆኑም በአገር ደረጃ ወደ 1,500 የሚጠጉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ ተደራሽ ናቸው እያልኩ አይደለም፡፡ እነዚህ በያሉበት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚሰጡ የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ ግን ማዕከሎቻችን ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለን የዳሰሳ ጥናት ስናደርግ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከዚሁ ጐን ለጐን የንግድ ዕቅድ ኮፒ ተደርጐ የሚሸጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ከእኛ መጀመር አለበት፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የመጣም ቢሆን የተዋጣለት የንግድ ዕቅድ ያዘጋጃል ማለት አይደለም፡፡ ስለሆነም አስቀድመን የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ክልሎች የንግድ ዕቅድ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት በአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ያሉ ባለሙያዎችን እንዲያሠለጥኑ ከማድረግ አኳያ እየሠራን ነው፡፡ የንግድ ዕቅድ ኮፒ ተደርጐ የሚሸጥበት ሁኔታ መኖር የለበትም ብለናል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ የንግድ ዕቅድ ለማግኘት የተደራጁ ወጣቶች ከአምስት ሺሕ እስከ 20 ሺሕ ብር እንደየቦታውና እንደየዘርፉ ይጠየቃሉ ይባላል፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ ዘነበ፡- አይጠየቁም አይባልም፡፡ ያሉበት ሁኔታም እሱን ነው የሚያሳየው፡፡ የገንዘቡ መጠን ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ እየሠራን ያለነው ወደ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ የሚሸጋገሩትን ለመደገፍ ነው፡፡ እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ በራሱ የንግድ ዕቅድ ማዘጋጀት እስከሚችልበት ማድረስ አለብን፡፡ ግቡም በየጊዜው የንግድ ዕቅድ እየተሠራለት የሚጓዝ ኢንተርፕራይዝ መፍጠር ሳይሆን፣ የተወሰነ ሥልጠና ሰጥቶና ድጋፍ አድርጐ ራሱን ማስቻል ነው፡፡ በራሳቸው በክልሉ የሥራ ቋንቋ ለልማት ባንኩ የንግድ ዕቅድ ሊያስገቡ በሚችሉበት ሁኔታም መታገዝ አለባቸው፡፡ ልማት ባንኩም ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ወጣ ብሎ እንዲሠራ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ሥራው የሚመራው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተገመገመ ስለሆነ አሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ያህል ኢንተርፕራይዞች አሉ?

አቶ ዘነበ፡- የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲጠናቀቅ ከ700 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ መረጃ አሳይቷል፡፡ አሁን ግን በጣም ወደ ተጨባጭነት ተጠግተን ማቀድ አለብን ብለን ነው የሄድነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 560 ሺሕ አባላት ያሉዋቸው 160 ሺሕ ኢንተርፕራይዞች ለማደራጀት ዕቅድ ይዘናል፡፡ አሁን በአፈጻጸም ያለውን ስናይ ወደ 56 ሺሕ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዋል፡፡ ይህ ከዕቅዳችን አኳያ ብዙ መሥራት እንዳለብን ያሳያል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ከተደራጁት ኢንተርፕራይዞች ምን ያህሉ ተሸጋግረዋል?

አቶ ዘነበ፡- ሽግግሩ በየዓመቱ መጨረሻ ነው የሚታወቀው፡፡ ከተጠቀሱት ከ700 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ በ2008 ዓ.ም. 1,586 ኢንተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ የተሸጋገሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቁጥር ላይ ጥልቅ ተሃድሶው ያሳየን እነዚህ ቁጥሮች መሬት ላይ ያሉ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ነው፡፡ ቁጥር መናገር ላይከብድ ይችላል፡፡ ግን ተዓማኒነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የመረጃ ሥርዓታችን ማኑዋል ነው፡፡ ዛሬ ያለው ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል፡፡ እንደ ኤጀንሲ እያንዳንዱ ክልል ይህን ያህል ኢንተርፕራይዝ አለ ብሎ በሪፖርት ከመላክ ባለፈ ኦዲት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ላይ በጣም ተጋኖ ከነበረው የኢንተርፕራይዞች ቁጥር ኦዲት ያሳየው 25 ሺሕ ኢንተርፕራይዞች አካባቢ ነው፡፡ በኦሮሚያም እንደዚሁ፡፡ ሽግግሩ ከጀማሪ ወደ ታዳጊ ብሎም መካከለኛ የሚሉ ደረጃዎች አሉት፡፡ ከተሸጋገሩት የመጨረሻ የሆነው ታዳጊም መካከለኛም ስንል አሉ ወይ? የሚል ጥያቄ አለ፡፡ በእኛ ደረጃ ካሉት ክልሎች ጋር ከሁለት ወራት በፊት በቢሾፍቱ በነበረው ስብሰባ የተነጋገርነው እያንዳንዱ በእጁ ምን ያህል ኢንተርፕራይዞች አሉት? የተሸጋገሩትስ ስንት ናቸው? የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ተነስተው ክልሎች በትክክል እጃቸው ላይ ምን ያህል ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ እየቆጠሩ ነው፡፡ ውጤቱንም እየጠበቅን ነው፡፡ ክልሎች ኦዲት እያደረጉ ስለሆነ የጠራ መረጃ ሲመጣ እንገልጻለን፡፡ ከኢንተርፕራይዞቹ ጋር ተያይዞ ያለው መረጃ የጠራ ስላልሆነ ይህን ያህል ነው ብሎ መስጠት ከቁጥር ያለፈ ሊሆን ስለማይችል፣ በቀጣይ አጥርተን በሚኖረን ስብሰባ እናነሳዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ 10 ቢሊዮን ብር አፅድቋል፡፡ ወደዚህ የተገባው ለምንድን ነው?

አቶ ዘነበ፡- የ10 ቢሊዮን ብሩን በሚመለከት በዋናነት ወደዚህ የወሰደን መነሻው ምንድን ነው የሚለውን ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ በኤጀንሲው ደረጃ ሥራ ፈላጊ የሆኑ ወጣቶችን መነሻ በማድረግ፣ ከብድር አቅርቦትም አኳያ ታይቶ ችግሩን እንዴት ነው የምንፈታው የሚለው አስቀድሞ ተጠንቶ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል፡፡ አሁን ያለውን ችግር ከመፍታት አኳያ በቀስታ ጉዞ የምንሄድ ከሆነ የወጣቱን ጥያቄ መመለስ አንችልም በማለት ነው፣ መንግሥት የ10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድን በአዋጅ ያፀደቀው፡፡ ከዓላማው አኳያ እንደ ኤጀንሲያችን ትልቅ አጋዥ አግኝተናል እንላለን፡፡ የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም፣ ከዚህ የሚብስ ችግር የለም ብሎ ገንዘቡን መመደቡ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ገንዘቡም ተሰልቶ ለክልሎች ተመድቧል፡፡ በየክልሉ ያለው ወጣት ምን ያህል ነው የሚለው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም. ትንበያ መነሻ ተደርጐና እያንዳንዱ ክልል ምን ያህል ወጣት አለው የሚለው ታይቶ፣ ወደ እያንዳንዱ ክልል ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የየክልሎች ድርሻ ምን ይመስላል?

አቶ ዘነበ፡- የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ታሳቢ ያደረገው ከ18 እስከ 34 ዓመት ያሉትን ነው፡፡ በአፋር 618,827 ወጣቶች ሲኖሩ፣ የገንዘብ ድርሻውም 206 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በትግራይ 1,578,463 ወጣቶች አሉ፡፡ የተመደበላቸውም ገንዘብ 527 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በአማራ 8,024,773 ወጣቶች ሲኖሩ 2.679 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያሉ ወጣቶች 1,806,539 ናቸው፡፡ 603 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ኦሮሚያ 10,314,270 ወጣቶች ሲኖሩ የደረሰው ገንዘብ 3.439 ቢሊዮን ነው፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 338,433 ወጣቶች ሲኖር 113 ሚሊዮን ብር ደርሶአቸዋል፡፡ ደቡብ 5,643,731 ወጣቶች አሉ፡፡ ከፈንዱም የ1.882 ቢሊዮን ብር ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በጋምቤላ 150,414 ወጣቶች ሲኖሩ፣ 50 ሚሊዮን ብር ደርሷቸዋል፡፡ ሐረሪ 80,259 ወጣቶች ከፈንዱ ድርሻቸው 27 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ አዲስ አበባ 1,255,486, ወጣቶች አሉ፡፡ የደረሳቸውም 419 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ድሬዳዋ 164,762 ወጣቶች ሲኖሩ 55 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ገንዘብ ለየክልሉ ተከፋፍሏል? ለወጣቶቹ መድረሱን እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት? ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ባለሀብቶችም ብሩን ይወስዳሉ ተብሎ በየስብሰባው ሲነገር ተሰምቷል፡፡ ተደራጅቶ ብድር መውሰድም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ነበር፡፡ ያም ሆኖ ወጣቱ የሥራ ዕድል አልተፈጠረለትም፡፡ ከመንግሥት ጋር ያልተግባባውም ለዚህ ነው ተብሏል፡፡ የመጀመሪያው ራሱ በትክክል ለወጣቱ ውሎ ነበር? በትክክል ገምግማችሁታል? ለ10 ቢሊዮን ብሩስ ምን ዓይነት የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግታችኋል?

አቶ ዘነበ፡- መጀመሪያ የነበረውን አሠራር መንግሥትም አንዱ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ብሎ የለየው ነው፡፡ ዘርፉም ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ ነው፡፡ እዚያም እዚህም የምናያቸው ነገሮች አሉ፡፡ እስር ቤት የገቡም አሉ፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ላይ ሲሠሩ የነበሩ፣ በሌላ ኢንተርፕራይዝ ስም የሚመስላቸውን አስገብተውና በብድር ተጠቃሚ ሲሆኑ ተይዘው በፍርድ ቤት የተቀጡ አሉ፡፡ ጥሩም እንዳለ ሁሉ መጥፎም አለ፡፡ መንግሥት ግን በየትኛውም ምዕራፍ ሲደርስ ያለምሕረት እየገመገመ ከአመራሩ እስከ ፈጻሚ ጭምር ወደ ሕግ እያቀረበ ነው፡፡ ለዚህም ነው እንደ ገቢዎችና ግዥ ፈጻሚዎች ሁሉ አነስተኛና ጥቃቅንን ዘርፍ የኪራይ ሰብሳቢዎች ምንጭ ነው ብሎ መንግሥት የለየው፡፡ ከዚህ በፊት የወሰድነውን ልምድ ተንተርሰን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ወደ ወጣቱ ከመድረሱ በፊት ቅድመ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ አደረጃጀት መፍጠር ዋናው ሲሆን አደረጃጀቱ በፌዴራል ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት አባል ሆነዋል፡፡ በክልል ደረጃ በርዕሰ መስተዳድሮች ይመራል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፣ ገንዘቡ በትክክል ለባለቤቱ ደርሷል ወይ የሚለው እየተገመገመ የሚሄድበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡

ገንዘቡን በተመለከተ ለተበዳሪው የተለያዩ አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ ወጣቱ ከተደራጀ በኋላ ወደ ሥራ ሲገባ ለምሳሌ የሚሠራው በማሽን ከሆነና የማሽን ግዢ ከፈለገ በጥያቄው መሠረት ማይክሮ ፋይናንሶች ያስተናግዳሉ፡፡ ብሩ ለወጣቱ ዝም ብሎ ቢለቀቅ እንዴት እንደሚያስተዳድረው ችግር ሊገጥመው ስለሚችል፣ ከሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ውጪ በዓይነት የሚገዙትን ራሱ በመረጠው አግባብ የሚሄድበት አሠራር አለ፡፡ ዋናው ግን ባለቤት የሆነው ወጣቱ፣ ወላጆችና ኅብረተሰቡ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ ሆኖም አደረጃጀት ስለተፈጠረ ብቻ ችግር አይፈጠርም ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡ ገንዘቡ ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዳይውል ከማድረግ አኳያ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት፡፡ በመሆኑም አሠራሩ እየተገመገመ ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚቀርብበት ሁኔታ አለ፡፡ ከነበረው የተሻለ ተጠቃሚ የመሆን ዕድል ይኖራል ብለንም እናምናለን፡፡ ሕዝቡም ወጣቱም መጠቀም የሌለባቸው አካላት እንዳይጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት ስላለበትና አሠራሩም በየአደረጃጀቱ እየተገመገመ ስለሚሄድ፣ ችግሩ ዜሮ ይሆናል ባንልም በአብዛኛው ይቀረፋል እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ኢንተርፕራይዝ እስከ ስንት ብር መበደር ይችላል? ወለዱስ?

አቶ ዘነበ፡- አንድ ኢንተርፕራይዝ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ማግኘት ይችላል፡፡ ወለዱ እስካሁን ከነበረው ያነሰ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ማይክሮ ፋይናንሶች ሲያበድሩ ከ10 በመቶ እስከ 18 በመቶ ወለድ ያስከፍሉ ነበር፡፡ አንዳንዱ ንግድ አደጋም ስላለው የወለድ ምጣኔው ይህንን ታሳቢም ያደርግ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን እንደ አጠቃላይ የተወሰነው ስምንት በመቶ ወለድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእፎይታ ጊዜውስ? በእፎይታ ጊዜ ወለድ ይታሰባል?

አቶ ዘነበ፡- አንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ አለው፡፡ በእፎይታ ጊዜውም ወለድ አይታሰብም፡፡

ሪፖርተር፡- የበለጠ የሚበረታታው ዘርፍ የቱ ነው?

አቶ ዘነበ፡- የመንግሥት አቅጣጫ በዋናነት ማኑፋክቸሪንግ ቢሆንም፣ በተለይ የ10 ቢሊዮን ብሩ ተዘዋዋሪ ብድር የሚሰጠው በአብዛኛው በጥቃቅን ለሚደራጁ ነው፡፡ የብድሩ ጣሪያ አንድ ሚሊዮን ብር የተደረገው ለአብዛኛው ወጣት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው፡፡ 10 ቢሊዮን ብሩ ለመንግሥት ካለበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ትልቅ ቢሆንም፣ ካለው ሥራ ፈላጊ ወጣት ሲነፃፀር ትልቅ አይደለም፡፡ ለትልልቅ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ገንዘቡን እንስጥ ካልን አብዛኛው ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ከ50 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ባለው ብድሩ ይሰጣል፡፡ ብዙው የሚያርፈውም መሀል ላይ ነው፡፡ ማበረታታትም ያለብን ሥራ ፈላጊው ከትንሽ እንዲነሳ በማድረግ ነው፡፡ ልምድ ይዘውና የገንዘብን አጠቃቀም አውቀው እንዲሸጋገሩ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከ10 ቢሊዮን ብር ፈንድ ለወጣቶች ማበደር ተጀምሯል?

አቶ ዘነበ፡- አሁን ብር ወደመቁጠሩ ሳይሆን ወደዚያ የሚያደርሰው የአደረጃጀት ሥራ ተበጅቷል፡፡ ንግድ ባንክ ለማይክሮ ፋይናንሶች ብሩን ያስተላልፋል፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች ከጠለፋ ዋስትና ውጪ አንድም ዋስ ሳይጠይቁ የንግድ ዕቅድና የእርስ በርስ ዋስትና ተቀብለው ብድር እንዲሰጡ የጋራ ስምምነት ተደርሶ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ብድሩ ትልቅነት ብዙ መቆጠብ የሚጠበቅባቸው አሉና ቅድመ ቁጠባውስ ተነስቷል?

አቶ ዘነበ፡- በዚህ መልኩ የሚታይ አይሆንም፡፡ እዚህ ላይ ሊታይ የሚገባው ብድር አለ፣ ቁጠባ አለ የሚለው ነው፡፡ እንደ ኤጀንሲ ያየነው ከቆጠቡ በኋላ ያለውን ቢሮክራሲ ማስወገድን፣ የወለድ መጠንን ወደ ስምንት በመቶ ማድረስን ነው፡፡ የንግድ ዕቅድ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ጭምር ሠርተው፣ ወጣቶችም ሥልጠና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ ለንግድ ስም ስያሜ ለማግኘት ከዞኖች በፋክስ ወደ ማዕከል እንዲላክ ተወስኗል፡፡ ጋዜጣ ማሳወጅም ቀርቷል፡፡ ገንዘቡም በተቀመረው መሠረት ለክልሎች ወርዷል፡፡ እስከታች እስከ ወረዳ ድረስ ገንዘቡን ለወጣቶቹ የማድረስ ሥራው እንደ ክልሎች ፍጥነት ይወሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም በማይክሮ ፋይናንሶችም ሆነ በጥቃቅንና አነስተኛ በሚባሉት የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑ የበለጠ ቅድሚያ ያገኛሉ ተብሎ ይወሳ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ ዘነበ፡- የፖለቲካ አመለካከት የሚለው ትልቁ ጉዳይ አይደለም፡፡ አባል ሆነውም ተጠቃሚ ሳንሆን ቀረን ብለው የሚናገሩ አሉ፡፡ ዋናው ችግር ኪራይ ሰብሳቢነትና ፍትሐዊ አለመሆን ነው፡፡ ገዢ የሚሆነውና መታገል ያለብን ራሱን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራውን አመራር ነው፡፡ ታግለን ለማሸነፍ ራሳችንን ለመጥቀም የምንሠራውን ማቆም አለብን፡፡                   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy