Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግስት ሳዑዲ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ሁኔታዎችን አመቻችቷል

0 374

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

የሳዑዲአረቢያ መንግስት ከዛሬ ጀምሮ ባሉት 90 ቀናት በአገሪቷ የሚገኙ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የየትኛውም አገር ዜጎች እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የአገሪቷ መንግስት በነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ፣ በቀጣናው ባለው ያለመረጋጋትና በውስጥም በውጭም ባሉ ችግሮች ምክንያት ለዜጎቹ ደህንነት ሲል ነው ይህን አስቸኳይ ውሳኔ በዚህ ሳምንት ይፋ ያደረገው።

ለስራ ዛምቢያ ሉሳካ የሚገኙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር እንዳስታወቁት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ይኖራሉ። ስለሆነም መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ መግለጫው ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው።

ከአገሪቷ መንግስት ጋር በመነጋገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመው፤ ዜጎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።

በአገር ውስጥ ጉዳዩን የሚያቀናጅ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ብሔራዊ ግብረ-ሃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ በስሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሂደቱን እየተከታተለ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዜጎች የሚያገኙትን መረጃና ምክር በአግባቡ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያመለከቱት ዶክተር ነገሪ፤ “ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የይለፍ ሰነድ አግኝተው መጉላላት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ” ብለዋል።

ቀደም ሲል ይህን ዓይነት ውሳኔ በመወሰን በርካታ ዜጎች ከአገሪቷ መውጣታቸውን አስታውሰው፤ በወቅቱ በተሳሳተ መረጃ ዜጎች በአገሪቷ እንዲቆዩና ችግር እንዲደርስባቸው ያደረጉ አካላት እንደነበሩም ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅትም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በአገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችም ይሁን በስፍራው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዜጎች የሚያገኙትን መረጃ በአግባቡ በመጠቀም በተባለው ጊዜ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ዜጎች በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ የሚያገኙበት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመው፤ በስፍራው ከሚገኘው ኤምባሲና ቆንስላዎች ባሻገር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በኩል በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር መረጃው ተደራሽ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግስትም ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲወጡ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ቃል መግባቱን ዶክተር ነገሪ ገልጸዋል።

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ቤተሰቦቻቸውና ሃብትና ንብረታቸውን ይዘው ወደ አገር ለሚገቡ ዜጎች ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባለፈ በአገራቸው ሰርተው ገቢ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy