Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማንሰራራቱን የሚያስተዋውቅለት የናፈቀው ዘርፍ

0 502

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኢትየጵያ ከወራት በፊት በኦሮሚያና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ሁከት የቱሪስቶችን ፍሰት በማስተጓጎል በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎ መቆየቱ ይታ ወቃል። አለመረጋጋቱ የሆቴሎች ገቢ እንዲቀንስ አድርጎ እንደነበርም ሆቴሎች ይገልጻሉ ፡፡

እንደ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት መረጃ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት የጎብኚዎች መጠን ካባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ0.82 በመቶ ቀንሶ ነበር።

የጌት ፋም ኢንተርናሽናል ሆቴል የሴልስ እና ማርኬቲንግ ማኔጀር አቶ ሚኪያስ ተስፋዬ እንደሚሉት፤ በሁከቱ ሳቢያ የሚጠበቀውን ያህል ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ አለመምጣቸው የሆቴሉ ገቢ እንዲቀንስ አድርጓል። ሁከቱ የፈጠረው ስጋት አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተወገደም፡፡

አቶ ሚኪያስ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ሰላምና መረጋጋቱ ወደ ነበረበት ቦታ መመለሱን አስመልክቶ የማስተዋወቅ ሥራ መከናወኑን ይጠቅሳሉ።ይህ ግን በቂ ነው አይደለም፡፡ ሆቴሉም የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት እንዲመለስ የማስተዋወቅ ሥራዎችን ማከናወኑን እና ቀስ በቀስ በሆቴሉ ገቢ ላይ መሻሻል መታየቱንም ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁንም በቅርቡ የተካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና የውጭ ጎብኚዎች የሰጡት በጎ አስተያየት የተካተቱባቸው ቪዲዮዎችን ለባለድርሻ አካላት እና በጉባኤ ለሚሳተፉ ዓለም አቀፍ አቀፍ ድርጅቶች በመላክ የሀገሪቱ ሰላም ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱን ለማስገንዘብ ጥረት እየተደረገ ነው።

«የሀገሪቱን የቱሪስት መስህቦች የማስተዋወቅ ሥራዎች ከሁከቱም በፊት በሚገባ አልተከናወኑም» የሚሉት አቶ ሚኪያስ፣ የጎብኚዎችንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ቀልብ በመሳብ የጎብኚዎችን መጠን ከፍ ለማድረግ እንደ ሲኤን ኤን እና ቢቢሲ የመሳሰሉትን ግዙፍ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን መጠቀም እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡ መሰል የማስተዋወቂያ ሥራዎች አገሪቷ በቱሪዝም ተፎካካሪ ከሆኑ አገራት ጋር ለመወዳደር እንደሚያስችላትም ይገልጻሉ።

የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የሽያጭና ማርኬቲንግ ማኔጀር ወይዘሮ ናርዶስ ታደለ አለመረጋጋቱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። በሆቴሎች ገቢ ላይም ጉዳት ማስከተሉን በመግለጽ የአቶ ሚኪያስን ሃሳብ ይጋራሉ።

ሰላምና መረጋጋቱ ወደ ቦታው ስለመመለሱ ለጎብኚዎች ሆቴሉ እያስተዋወቀ ነው የሚሉት ወይዘሮ ናርዶስ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተቋማት የተለመደውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚጋብዝ ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ በአዲስ አበባ ሆቴሎች ማህበር የተዘጋጀውን ጋዜጣዊ ደብዳቤ ለሆቴሉ ደንበኞችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

ወይዘሮ ናርዶስ እንደሚሉት፤ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር እየተሻሻለ መጥቷል፡፡

«ይህን ዓይነት ችግር በሦስተኛ ዓለም አገራት ላይ ያጋጥማል። በመሆኑም ቱሪዝሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል» ያሉት ወይዘሮ ናርዶስ፣ አሁን ሰላም ስለመስፈኑና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምን ለማስጠበቅ መውጣቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ደጋግሞ ማስተዋወቅ ቢችል መልካም ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው እንደሚሉት፤ በገፅታ ግንባታ በተከናወነው ሥራ የዘንድሮው በጀት ዓመት ሁለተኛ ሩብ ዓመት የጎብኚዎች ቁጥር ከ2008 በጀት ዓመት ሁለተኛ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

የቱሪስት ፍሰቱን ወደነበረበት ለመመለስ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተቋማት ቅንጅት የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሀገሪቱ ስለተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የውጭ ሀገር አስጎብኚ ኩባንያዎችን ለማሳወቅ በየጊዜው መግለጫዎች እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይህም የጎብኚዎች ቁጥር መቀነስን በመቀልበስ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በግብረ ኃይሉ ከሚሰጡ መግለጫዎች በተጨማሪ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የሀገሪቱ ሰላም ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱን ድርጅቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ከቢቢሲ ጋር በተደረገ የአስራ አምስት ደቂቃ ቃለ-መጠይቅ ተጨባጩን ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስገንዘብ መቻሉን አቶ ጌትነት ይገልጻሉ፡፡ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ የጉዞ እገዳ የጣሉ ሀገሮችም ውሳኔዎቻቸውን እንዲያጤኑና ማስጠንቀ ቂዎቻቸውን እንዲያነሱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደሚሉት፤ የገጽታ ግንባታ በማከናወን የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲያገግም ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ሰርተዋል።

ሁከቱን እንደ ምክንያት በመጥቀስ በተለይ 11ኛው ዓለም አቀፍ የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ በኢትዮጵያ ስለመካሄዱ ጥርጣሬዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ገዛኸኝ፣ የፀጥታ ችግር አለመኖሩን የማስገንዘብ ጥረት በመንግሥት ልዑካን ቡድን እና በኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች አማካኝነት መካሄዱን ይገልጻሉ። በዚህም ከአንድ ሺ በላይ የውጭ ዜጎች የተጋበዙበትን ጉባኤ ለማዘጋጀት መቻሉን ይናገራሉ፡፡ በቅርቡም 39ኛውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጉባኤ በስኬት መካሄዱን ይጠቅሳሉ።

የቱሪዝም መዳረሻዎችን የጎበኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ስለሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ለሌሎች ጎብኚዎች ያስተላልፉትን መልዕክት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች እንዲቀረፅ በማድረግ ኢትዮ ትራቭል በሚለው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ድረ-ገጽ እንዲወጣ መደረጉን ይገልጻሉ።

ከዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶም የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄ ዳቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በእንግሊዝ ከሚገኙ አስገብኚ ድርጅቶች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያካሄዱትን ውይይት ነው።

«ቱሪዝሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ ለየት ባለ መንገድና ተከታታይ ባለው መልኩ የማስተዋወቅ ሥራ እየተካሄደ ነው» የሚሉት አቶ ገዛኸኝ፣ የሀገሪቷን ገፅታ ለመገንባት እና ጎብኚዎችን ለማበረታታት ብሎም የቱሪስት ፍሰቱን ለማጎልበት በቅርቡ ቡድን ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን እንዲጓዝ መደረጉንም ጠቅሰዋል። በቅርቡም በኳታር የኢትዮጵያ ባህል ሳምንት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።( በሪሁ ብርሃነ)

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy