Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቋንቋ እና ብሔራዊ መግባባት

1 2,183

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በ1987 .ም ከፀደቀበት ወቅት አንስቶ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት መብት ተጎናፅፈዋል፡፡ የሥራ ቋንቋ የመወሰን ነፃነትን ለራሳቸው ለክልሎች የሚቸረው ሕገ መንግሥቱ፤ በአንቀፅ 5 ቁጥር 2 ላይ «አማርኛ የፌዴራሉ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል» ሲል ይደነግጋል፡፡ ከህገ መንግስቱ መጽደቅ በኋላ አማርኛን ጨምሮ ሌሎችም ቋንቋዎች በክልል የሥራ ቋንቋ ሆነዋል። አማርኛን ጨምሮ በ 51 ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።

በአገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሂደትም ወደ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመምጣት የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ምሁራን ይገልጻሉ። በታሪክ አጋጣሚ በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ጋራ መግባቢያ አሁን ደግሞ በተወሰኑ ክልሎች እና በፌዴራል መንግሥት በሥራ ቋንቋነት የሚያገለግለው አማርኛ የተጠቀሰውን ሚና የመወጣት ዕድል ቢኖረውም በተጨባጭ ግን ክፍተቶች መኖራቸውን ያመለክታሉ።

ምሁራኑ እንደ አብነትም አማርኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸው ያልሆኑ ከተለያዩ ክልሎች ለሥራ ወይም ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ዜጎች በፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ በሚገባ ለመግባባት መቸገራቸውን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎችም ከተለያየ ስፍራ በሚመጡት ተማሪዎች ዘንድ የተግባቦት ውስንነት መኖሩን ይጠቅሳሉ። ለመሆኑ የብሔራዊ መግባቢያ አንድ መሣሪያ የሆነው የቋንቋ ጉዳይ በአገሪቱ ምን ገጽታ አለው?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ተመራማሪና የሥነ ልሳን ባለሙያ ዶክተር ዮሐንስ አድገ፤ አማርኛ በሕገ መንግሥቱ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ሆኖ ቢደነገግም ለማስፋት በቂ እንክብካቤ የተደረገለት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲቀላቀሉ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባሻገር አማርኛ የመናገር ብቃታቸው አነስተኛ መሆኑን በማሳያነት ያስቀምጣሉ፡፡

ይሄ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዜጎች የጋራ አስተሳሰብ፣ አመለካከትና አገራዊ ራዕይ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ራሱን የቻለ ተግዳሮት ይፈጥራል፡፡ ብሔራዊ መግባባትን በማጎልበት የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ እፈጥራለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ አገር፤ ዕቅዱ የሚቀለጣጠፍበት አንዱ መንገድ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ዮሐንስ፤ ሆኖም ይሄ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በሚመጡ ተማሪዎች ዘንድ ከተግባቦት አንጻር መሠረታዊ ችግር እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ማህበራዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ተመሳሳይ ይሆናሉ ተብሎ ባይጠበቅም የጋራ የቤት ሥራ ለመስራት የሚያበቁ መሠረታዊ መሣሪያዎች ሊኖሩ እንደሚገባ የሚናገሩት ዶክተር ዮሐንስ፤ ከእዚህ መካከልም የጋራ የመግባቢያ ቋንቋ አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ እያካሄዱ የሚገኙትን ጥናት ጠቅሰው፤ ከተለያዩ ክልሎችና ብሔር ብሔረሰቦች የሚመጡ አብዛኞቹ ተማሪዎች የፌዴራሉን የሥራ ቋንቋ በአግባቡ እንደማይጠቀሙበት ይገልጻሉ፡፡ ተማሪዎቹ ከአማርኛ ውጪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስተማሪያ የሆነውን እንግሊዝኛ ቋንቋንም ቢሆን አቀላጥፈው አለማወቃቸው ሌላው ችግር ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ዘነበ በየነ፤ ይሄን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባቸው አገሮች በጋራ የሚያግባባ አንድ ቋንቋ መኖር በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፡፡ «አንዳችን ስለ አንዳችን ባሕል፣ ታሪክ፣ አመጣጥ፣ ሥነልቦና እንዲሁም ፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች እንረዳበታለን» የሚሉት ዶክተር ዘነበ፤ ከምንም በላይ አገራዊ አጀንዳዎችን በጋራ ለማራመድ የሚያስችል መሣሪያ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

በመሆኑም ይላሉ፤ ምንም እንኳን በታሪክ አጋጣሚ አማርኛ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ቢሆንም የሁሉም ቋንቋዎች እኩልነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የጋራ የመግባቢያ ድልድይ የሆነውን ይህን ቋንቋ በተሻለ ደረጃ ሁሉም ዜጋ ቢያውቀው ጥቅሙ የአገር መሆኑን ያብራራሉ፡፡

አፍ መፍቻቸው አማርኛ ባልሆኑ አካባቢዎች የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ በአግባቡ ላለማደጉ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የሥነ ልሳን ባለሙያው ዶክተር ዮሐንስ፤ በክልሎች የቋንቋው ትምህርት አሰጣጥ ወጥ አለመሆኑን እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ፡፡ ትምህርቱ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሆኖ አለመሰጠቱ ሌላኛው እክል መሆኑን በመግለጽ፤ ከተማሪዎች ሥነልቦና አንፃር እውቀታቸውን በውጤት ስለሚለኩ ጠንክረው እንዲማሩ ስላላደረጋቸው ጉድለት አስከትሏል የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአፍ መፍቻና እንግሊዝኛ ቋንቋ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታያቸው አያሌው ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፡፡ የብሔራዊ ፈተና አለመኖር በተማሪዎች የቋንቋ ክህሎት አለማደግ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አያሳድርም፤ አማርኛ ትምህርት ጠንክረው የሚማሩት ውጤትን ብቻ ታሳቢ በማድረግ ከሆነ በአመለካከትና ግንዛቤ በኩል አሁንም ቀሪ ሥራ መኖሩን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡ ይልቅስ መከራከሪያው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን ማዕከል ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ። ፖሊሲው ተማሪዎች ከአፍ መፍቻቸው ባሻገር በፍላጎታቸው ላይ ተመስርቶ አንድ የአገር ውስጥና ሌላ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ ማጥናት እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲው በአስቀመጠው አቅጣጫ ትምህርቱ በተሟላ ሁኔታ እየተሰጠ መሆኑን መፈተሽ ተገቢ ነው።

አፍ መፍቻቸው አማርኛ ባልሆኑ አካባቢዎች የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ በአግባቡ ላለማደጉ የግልና የጋራ የቋንቋ መብቶችን በተመለከተ ድንጋጌ እንደሚያስቀምጥ የሚጠበቀው የቋንቋ ፖሊሲ አለመጽደቁ ሌላ ምክንያት መሆኑን የስነልሳን ምሁሩ ዶክተር ዮሐንስ ያነሳሉ፡፡ በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል ዕሴቶች ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው ግን በሌሎቹ ችግሮች ቢስማሙም «የቋንቋ ፖሊሲ አለመኖር የፈጠረው ክፍተት ትልቅ ነው ተብሎ አይታሰብም» ይላሉ፡፡

ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የቋንቋ ፖሊሲ ረቂቅ ምንም እንኳን እስካሁን ባይጸድቅም፤ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው የቋንቋ ጉዳይ የተካተተ በመሆኑ ክፍተቱ በቀጥታ ከቋንቋ ፖሊሲ አለመኖር ጋር አይያያዝም ባይ ናቸው፡፡

አቶ አለማየሁ ችግሩ በስፋት መኖሩን ግን ይስማማሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች በፍጥነት አንብቦ የመረዳት አቅም ሲመዘን «ውጤቱ አስደንጋጭ ነበር» በማለት፡፡ ለእዚህም ሦስት ክፍተቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ አማርኛ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የቋንቋ ትምህርቶች ውጤት ላይ የተመሰረተ የትምህርት አሰጣጥ አለመኖሩ እንዲሁም የአሰልጣኞች ብቃት ማነስ ቀዳሚዎቹ ችግሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ በሁሉም ክልሎች በእኩል ደረጃ የትምህርትና ሥልጠናው ፖሊሲው ባስቀመጠው አቅጣጫ ልክ አለመተግበሩ ተጨማሪ እክል ነው።

የአፍ መፍቻና እንግሊዝኛ ቋንቋ ልማት ዳሬክተሩ አቶ ታያቸው በበኩላቸው፤ በተለያዩ ወቅቶች የቋንቋ ክህሎቶችን ለመመዘን የተደረጉ ጥናቶች ቢኖሩም የተገኙት ውጤቶች «አስደንጋጭ ነው» በሚለው አይስማሙም፡፡ ይልቁኑም በአፍ መፍቻም ሆነ በሁለተኛ ቋንቋ ዙሪያ የግንዛቤ ለውጥ ይታያል፡፡ ነገር ግን ይላሉ፤ ሚኒስቴሩ ባደረጋቸው መሰል ጥናቶች መሠረት አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች ወደ ፌደራል ተቋማት ሲመጡ የተግባቦት ችግሮች እንዳሉ ተገንዝቧል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ፤ ከሦስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተለምዷዊ ከነበረው የትምህርት አሰጣጥ በተሻለ መልኩ በአዲስ አቀራረብ ለማስተማር ሥርዓተ ትምህርቱ ተከልሷል፡፡ ክለሳውም በዋናነት ከአቀራረብ ባሻገር ተማሪዎች የአፍ መፍቻቸውን፣ ሁለተኛ ቋንቋቸውን እና የሥራ ቋንቋውን እንዴት መማር ይገባቸዋል? በሚለው ፍልስፍና የተቃኘ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ መጻሕፍት እየታተሙ ሲሆን ክልሎች ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብት ባልተጋፋ መልኩ ተቀራርቦ ይሰራል፡፡

የተከለሰውን ሥርዓተ ትምህርት በማስተግበር ሂደት ውስጥ ዋናዎቹ ተዋንያን መምህራን በመሆናቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ግንዛቤ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ እንዲሁም የማስተማር ሥነ ዘዴ ላይ ሥልጠና እንደሚሰጥ አቶ ታያቸው ይገልጻሉ፡፡ ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል አማርኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ከስድስት ሺ በላይ መምህራን ሥልጠና ወስደዋል፡፡

ዶክተር ዮሐንስ ሥርዓተ ትምህርቱን ከማሻሻል ባሻገር የፌዴራሉን የሥራ ቋንቋ በሚገባ ለማሳደግ በየክልሉ የቋንቋ ተግባቦትና ክህሎትን ማበልፀግ የሚችሉ ማዕከላት ቢዘጋጁ የሚል የመፍትሔ ሃሳብ ይጠቁማሉ። እንደ አገር ሁሉንም ዜጋ የሚያግባባ የቋንቋ ፖሊሲ አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት በመስጠት፤ የሌሎች በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የሆኑት አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ተጨማሪ ሌሎች ሁለትና ሦስት ቋንቋዎች ተመርጠው የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ቢሆኑ የሚል ምክረ ሃሳብም አላቸው፡፡

ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው ቋንቋ ስላላቸው አማርኛ መናገር ላይገደዱ ቢችሉም፤ አንድ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ለመግባባት የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ቢኖር ተመራጭ መሆኑን ምሁራኑ ይስማማሉ፡፡ ከአንድ ቋንቋ ባሻገር ሌሎቹንም እንደ ጋራ መግባቢያነት ማጎልበት እንደሚገባ ይመክራሉ። አለዚያ ግን ብሔራዊ መግባባትን በማሳደግ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው አገራዊ ጥረት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ስጋት አላቸው።

 ብሩክ በርሄ

 

  1. Mulugeta Andargie says

    Guys!!! Let me give my opinion: Language is a communication voice. Through this, culture, literature, religions, science and technology etc could be expressed and developed deeply. The developed and undeveloped; the exercised and could expressed, the well developed and the unmoveable, the mixable and the untouchable, the thrown and the held languages are enormous in the world. Among them, Amharic is our national language. Amharic is a language which couldn’t grow up in any side. Any language which you want develop should be conjugate or borrow words and mixed and make a size large. For instance, verbs could play a big role. But Amharic couldn’t get that chance while it was not. In general, you can’t develop it at all. All the languages of Ethiopia couldn’t grow up at all. Verbs are the main role which could play to invent or develop the language. Mechanical terms, medical terms, philosophy words, etc etc needs to develop the language. Our Amharic is poor by chance!!! A calf could graze and grow up with in year Alfa Alfa. Amharic cant grow even if you borrow from Promo, Tigrigna or Geez or any else. The second language is A fan Promo!!! It is the same!!! In a short, let us find other language which makes a sense. English is the best!!! Bangladesh, India, Malessya, etc etc are our teachers. Let us follow them!!! We are building our country for our kids!!!! Let us not make mistakes!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy