በሻሸመኔ ከተማ የመኖሪያ ቤት በመከራየት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ሲልኩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ግለሰቦቹ በሻሸመኔ ከተማ አዋሾ ክፍለ ከተማ 01 ቀበሌ የተከራዩትን ቤት የጫት መቃሚያ በማስመሰል ህገ-ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ ነበር ተብሏል ፡፡
የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወረዳ ሁለት ፖሊስ ፅህፈት ቤት ከነዋሪዎች ከደረሰው ጥቆማ በመነሳት ባደረገው ኦፕሬሽን፥ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ፣ 47 ፓስፖርቶችን፣ የህክምና ማስረጃዎችን ፣ ፎቶዎችን እና የሺሻ እቃዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሁለት ግለሰቦች ሌላ ሁለት ያመለጡ ሲሆን ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ መሆኑን፥ የፅህፈት ቤቱ የአካባቢ ፀጥታና የወንጀል መከላከል የስራ ሂደት ረዳት ሳጅን ሙህዲን ማህመድ ገልፀዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ የተላኩ ሰዎች አሉ የሚል ጥቆማ ስለደረሰንም ምርመራችንን አጠናክረን ቀጥለናል ብለዋል ረዳት ሳጅን ሙህዲን፡፡ FBC