Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአነስተኛ ቀዶ ህክምና (LEEP) የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን መከላከል ይቻላል

0 2,945

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓለም የጤና ድርጅት እ..አ በ2012 ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው ፡በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ለሴቶች ሞት ዋነኛው ምክንያት ነበር ፡፡ እድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ዓመት ያሉ ሴቶች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው ። በጥናቱ ከተካተቱ 22 ሚሊዮን ሴቶች መካከል 795ቱ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የተገኘባቸው ሲሆን፣ 4732 በችግሩ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በርካታ እናቶችን ሲጎዳና ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሲሆን ከመቆየቱም በላይ ለበሽታው ህክምና ለማግኘትም ጥሪታቸውን ሲያሟጥጥ ቆይቷል ፡፡

በሽታውን ለመከላከል የሚመደበው የገንዘብ መጠን አናሳ መሆን፣ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሞያዎች በበቂ ሁኔታ ያለመገኘትና የህከምና መሳሪያዎች ውስንነት፣ የቅድመ መከላከል ግንዛቤ አናሳ መሆን ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያቶች በመሆንም ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ በቅድመ ካንሰር ህክምና በተለይም በመከላከል ስራው ላይ የመጡትን ለውጥ ማስቀጠልንና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋትን ያለመ ስልጠና ሰሞኑን በተከሄደበት ወቅት እንደተጠቆመውም ፤ ካለፉት 6 ዓመታት ወዲህ ግን በማሕፀን በር ጫፍ ህክምና ላይ ለውጦች መታየት ጀምረዋል ፡፡

በተለይም ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ከአሜሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ችግሩ ከታየባቸው በአፋጣኝ ስር የሚሰድ መሆኑን በመገንዘብ በቅድመ መከላከል ሂደት ለማስቆም ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል፡፡

አነስተኛ የጤና ግብዓት ባለባት ኢትዮጵያ ችግሩን ከግምት በማስገባትና በአንድ ጊዜ ምርመራ ብቻ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ያለባቸውን ሴቶች የመለየትና በተመረመሩበት ወቅት ወዲያውኑ ህክምናውን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ውጤቶች እየታዩ ነው፡፡

«ሊፕ» የተሰኘውን የቅድመ ካንሰር ህክምና አገልግሎት ለማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት በተካሄደበት በዚህ ስልጠና ላይ የተገኙት የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ግርማ እንዳሉት ፤በክልሉ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ዓመታትን አስቆጥሯል ፡፡ ይሁንና አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው በኦሮሚያ ክልል አሰላ ላይ ብቻ ነበር ፡፡

ከዚህ በፊት የህብረተሰቡ ግንዛቤ ውስን ስለነበር ሰዎች በበሽታው ቢያዙም ወደ ህክምና ተቋም የሚመጡት በጣም ከባሰባቸው በኋላ ነበር፡፡ ይህም የቅድመ ካንሰር ህክምናውን በጣም አስቸጋሪ አርጎት ቆይቷል። በተሰራው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አሁን በአብዛኛው እናቶች ለመመርመር ወደ ሆስፒታል እየመጡ ናቸው ፡፤ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ባለሞያዎችን በማሰልጠን አገልግሎቱን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ፡፡

‹‹ በአገር አቀፍ ደረጃ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ገዳይ ነው›› የሚሉት ዶክተር አለማየሁ፣ በክልሉም ቢሆን በስፋት እንደሚታይ ነው የጠቆሙት ፡፡ በቀጣይ በመከላከል ስራው ላይ የመጡ ለውጦችን ለማስቀጠልና ለማስፋት ስልጠና መሰጠቱ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡

የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር መንግስቱ አስናቀ እንደሚሉት፤ የቅደመ ካንሰር መከላከል ፕሮግራሙ ከስድስት ዓመት በፊት ሲጀመር ‹‹አዲስ ተስፋ›› በሚል ነበር፡፡ የቅደመ ካንሰር /የመጀመሪያ ደረጃ / የመከላከል ሂደቱም ክትባትን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ አገልግሎቱን በኢትዮጵያ ለመጀመር የሙከራ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አሁን እየተሰራ ያለው ሁለተኛ ደረጃ የካንሰር መከላከያ ዘዴ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ሁለተኛው የቅደመ ካንሰር መከላከል ህክምና ክራዮቴራፒ /cryotherapy/ የሚባል ሲሆን ፤ ህክምናው የካንሰሩን ምልክት በመለየት በቀዘቀዘ ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመጥረግ ወደ ካንሰር እንዳይለወጥ ማድረግ የሚያስችል ነው ፡፡ ካንሰሩ በእዚህ አይነት መንገድ ካልታከመና ጠጣርነት ካለው «ሉፕ» በተሰኘው መሳሪያ አማካኝነት /Loop Electrosurgical Excision Procedure/ መለስተኛ ቀዶ ህክምና በማድረግ ማከም የሚቻል መሆኑን ነው ያብራሩት ፡፡

እንደ ዶክተር መንግስቱ ገለጻ፤ የቅድመ ካንሰር መለየት ስራው በአምስት ሆስፒታሎች ላይ ተጀምሮ ወደ 14 ሆስፒታሎች እንዲያድግ ተደርጓል ፡፡ከዚህ በተገኘው ውጤትም አገልግሎቱ ዛሬ ላይ በትልቅ ፕሮግራምነት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አመራር ሰጪነት ከ118 የጤና ተቋሞች በላይ ተስፋፍቶ እየተሰራበት ነው ፡፡

‹‹ በፕሮግራሙ በአነስተኛ ዋጋ ለውጥ ማምጣት ችሏል›› የሚሉት ዶክተር መንግስቱ፤ በቅድመ ካንሰር መከላክል ብቻ ተጨማሪ ወጪዎችን ማዳን አንደተቻለ ይናገራሉ፡፡ ለውጥ በሚያመጡ ፕሮግራሞች ላይ በድፍረት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፡ በአምስት ሆስፒታሎች ብቻ ተጀምሮ የነበረውን የሉፕ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ለመስጠትና ወደ አስር ሆስፒታሎች ለማሳደግ ታቅዷል፤በዚህ «ሉፕ» በተባለው የህክምና መሳሪያ አማካኝነት የሚደረገው የቀዶ ህክምና ከክራዮቴራፒ በተሻለ ውጤታማ ያደርጋል ፡፡

እነዚህ የክራዮቴራፒ አገልግሎት የሚሰጥባቸው አስር ሆስፒታሎች ደግሞ በአካባቢያቸው ላሉ የጤና ተቋማት እንደ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲያገለግሉም ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

እያንዳንዱ የጤና ተቋም ላይ ይህንን አገልግሎት መስጠት አስቸጋሪ ነው፤በዚህ ምክንያት ደግሞ ሉፕን በመጠቀም የቅድመ ካንሰር ህክምናውን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ወጪ የሚያገኙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው የሚሉት ዶክተር መንግስቱ አገልግሎቱን ከሚሰጡ የጤና ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከተሰራ ግን የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚቻል መሆኑን ነው የሚገልፁት፡፡

ዶክተር መንግስቱ የሰለጠኑ ባለሞያዎች በአጭር ጊዜ ከስራቸው የሚነሱበት ሁኔታ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት ፡፡ ይህም ፕሮግራሙን በማስፈፀም ሂደት ያጋጠመ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ህክምና ተወካይ ሲስተር ታከለች ሞገስ በበኩላቸው አንዲት ሴት ወደ ሆስፒታል በመሄድ በቶሎ ህክምናውን ማግኘት ከቻለች መቶ በመቶ እንደምትድን ይገልጻሉ፡፡ ከቦታ ርቀት፣ ከትራንስፖርት ችግር፣ከገንዘብ አቅም ማነስና ከግንዛቤ እጥረት ጋር በተያያዘ ብዙዎች እየተጎዱ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ህክምና፤ የቅድመ ካንሰር ህክምና አገልግሎቱን ለማስፋት በተለይም 14 ሆስፒታሎች ውስጥ ሲሰጥ የነበረውን የሊፕ ህክምናን 10 በመጨመር ወደ 25 ሆስፒታሎ ች ለማሳደግ ከፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝም ነው ሲስተር ታከለች የገለጹት ፡፡

አገልግሎቱን ውድ የሚያደርገው ነገር እንደሌለም ሲስተር ታከለች ይናገራሉ ፡፡ አንዲት እናት የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ህክምናውን በክራዮቴራፒ ካልተከታተለች በሊፕ መታከም እንደምትችልም ነው የሚናገሩት ፡፡ ስለሆነም እነዚህን የሊፕ ማሽኖችን በክልል ከተሞች ላይ በሚገኙ ሆሲፒታሎች ውስጥ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማሉ ፡፡

እንደ ሲስተር ታከለች ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የሊፕ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አምስት ሆስፒታሎች ላይ ብቻ ነው የሰለጠኑ ባለሞያዎች የሚገኙት፡፡ በቀጣይ ከፓዝ ፋይንደር ኢንተር ናሽናል ጋር በመሆን በአስሩም ሆስፒታሎች ላይ ለማሕፀንና ፅንስ ባለሞያዎች እንዲሁም ለመካከለኛ ደረጃ ነርሶችና አዋላጅ ነርሶች ስልጠናውን ለመስጠት ታቅዷል ፡፡ በተጨማሪም 10 ሆስፒታሎች ላይ ስልጠናውን ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ሂደትም የማሕፀን ካንሰሩን በግማሽ እንቀንሳለን ብለን እናምናለን ይላሉ፡፡ አስናቀ ፀጋዬ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy