Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎችና ዓለምአቀፍ ተቋማት የሃዘን መልዕክት እያስተላለፉ ነው

0 951

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ ያወጀው ብሄራዊ የሃዘን ቀን መተግበር ተጀምሯል።

የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም በሁሉም የሃገሪቱ ግዛቶች፣በኢትዮጵያ መርከቦች፣በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ነው።በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማትም በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የተሰማቸውን የሃዘን መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በደረሰው አደጋ ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው በድረ-ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡

የኮሚሽኑ ጊዜያዊ ዋና ፀሃፊ አብደላ ሃምዶክ ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የሰው ህይወት በመጥፋቱ ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸውና ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአደጋው የዜጎች ህይወት መጥፋቱ እንዳሳዘነው በድረ-ገጹ ላይ ባሰፈረው የሃዘን መልዕክት ገልጿል፡፡

በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማትረፍና ህይወታቸው ያለፉ ዜጎችን አስከሬን ለማውጣት እንዲሁም በቤት ንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በመርዳት መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነትም ህብረቱ አድንቋል፡፡

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በዚህ የሃዘን ወቅት ህብረቱም ከጎኗ መሆኑንና ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ መጽናናት መመኘቱን ባስተላለፈው የሃዘን መልዕክት አስታውቋል፡፡

germany_flag.jpg

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ በበኩሉ በደረሰው መሪር ሃዘን ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው አስታውቋል፡፡

የጀርመን መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ሃዘን ጎን መቆሙን ለማመላከትም የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲም በተወካዩ ፒተር ቭሮማን በኩል ባስተላለፈው የሃዘን መግለጫ በአደጋው ለተጎዱ ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል፡፡ የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግም የአሜሪካ ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጎን የሃዘኑ ተካፋይ መሆኑን አመልክቷል፡፡በአደጋው እስካሁን ድረስ የ72 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡

የኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ሃዘን ገልጾ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን መመኘቱ ይታወሳል።

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ የዜጎች ህይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀው ለተጎጅ ቤተሰቦችና ለመላው ህዝብ መጽናናትን መመኘታቸው ይታወቃል፡፡ብሄራዊ የሀዘን ቀኑም ከዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy